“ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 20 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ጦርነት ሞተዋል” አሜሪካ

ዩክሬን አዲስ የጸደይ መልሶ ማጥቃት ትጀምራለች

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, 80 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ደግሞ ቆስለዋል

ካለፈው ታኅሣሥ ወር ወዲህ በሩሲያ እና በዩክሬን ኃይሎች መካከል በተካሄደው ውጊያ 20 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ሳይገደሉ እንዳልቀረ አሜሪካ ገምታለች።

ሌሎች 80 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል ብላለች።

የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንዳሉት ከሟቾቹ ግማሾቹ ከቫግነር ተዋጊ ቅጥረኛ ቡድን ናቸው።

ይህ ቅጥረተኛ ተዋጊ ቡድን አሁን ላይ ምሥራቃዊቷን ባኽሙት ከተማን ለመያዝ እልህ አስጨራሽ ጦርነት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ሩሲያ ይቺን ባኽሙት የተሰኘችውን ትንሽ ከተማ ለመያዝ ካለፈው የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ቢሆንም እስከአሁን የተመኘቸውን ያህል አልተሰካላትም።

በእርግጥ ሞስኮ የባኽሙት ከተማን ሰፊ ቦታ የያዘች ቢሆንም፣ አሁንም ግን የዩክሬን ወታደሮች ምዕራቡን የከተማውን ክፍል እንደተቆጣጠሩ ናቸው።

የባኽሙት ከተማን ሙሉ በሙሉ ለመያዝ የሚደረገው ጦርነት አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የዩክሬን ጄኔራሎች እንደሚሉት ደግሞ አሁን እየተጠቀሙበት ያለው ስልት በሁሉም ጦርነቶች በተቻለ መጠን በርካታ የሩሲያ ወታደሮችን በመግደል የሩሲያን የተዋጊዎች አቅም በቁጥር ማመናመን ነው።

“ሩሲያ ባኽሙት ከተማን ለመያዝ በዶንባስ አውራጃ በኩል ያደረገችው መጠነ ሰፊ ጥቃት ከሽፏል” ብለዋል ቃል አቀባዩ ኪርቢ።

ጨምረውም፣ “ሩሲያ አንድም ይህ ነው የሚባል ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ቦታን ለመያዝ አልቻለችም” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እኚህ የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ግን አገራቸው አሜሪካ ሰፊ ድጋፍ በምትሰጣት አጋር አገር በዩክሬን በኩል የደረሰውን ጉዳት አልጠቀሱም።

ለምን የዩክሬንን ሙት እና ቁስለኛ ቁጥር እንደማይጠቅሱ ሲጠየቁ፣ “ዩክሬን ተጠቂ ናት፣ ሩሲያ ወራሪ ናት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ቢቢሲ ቃል አቀባዩ የሰጡትን አሃዛዊ መረጃ ከገለልተኛ አካል ማጣራት አልቻለም።

ሩሲያም ቢኾን በዚህ አሃዝ ዙርያ ያለችው ነገር የለም።

ለሩሲያ ባኽሙት ከተማን መያዝ የዶኔስኪ አውራጃን ሙሉ በሙሉ በእጇ ለማስገባት ያስችላታል።

ዶኔስክ አውራጃ ሩሲያ ባለፈው መስከረም በሕዝበ ውሳኔ ወደ ራሷ ከጠቀለለቻቸው አራት አውራጃዎች አንዱ ነው።

የጦር ተንታኞች እንደሚሉት ባኽሙት በርካታ ነፍስ እየጠፋባት ቢሆንም በወታደራዊ ስትራቴጂ መለኪያ ከታየ ይቺ ከተማ ያላት ጠቀሜታ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ነገር ግን ሁለቱም ተዋጊ ወገኖች በዚህ ከተማ ከባድ እና የተራዘመ ጦርነት እያደረጉ ነው።

በተለይ ቫግነር የቅጠረኛ ተዋጊ ቡድን በዚች ከተማ ላይ በሚደረገው ትንቅንቅ ቁልፍ ሚናን እየተጫወተ ይገኛል።

ይህ ቡድን ብዙውን ጊዜ በወንጀል ተከሰው ረዥም ዘመን የተፈረደባቸውን እስረኞች በወታደርነት መልምሎ በመቅጠር ከሩሲያ ወገን እንዲሁም ከቀጣሪዎቹ ወገን ሆኖ በመዋጋት ይታወቃል።

የዚህ ቡድን አባላት አሁን በጦርነት እየታመሰች ባለችው ሱዳን፣ ቻድ እና ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ እንዲሁም በሊቢያ ተዋጊዎችና የጦር አሰልጣኞች አሉት።

ቡድኑ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም በሕገ ወጥ የወርቅ ንግድ ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።

የዚህ ቅጥረኛ ቡድን ዋና መሪና መሥራች ይቬጌኒ ፕሪጎዚን ሰሞኑን በሰጠው አንድ ያልተለመደ ቃለ ምልልስ በቂ ትጥቅ እና ስንቅ ካልቀረበለት ሠራዊቱን ጠቅልሎ ከባኽሙት ከተማ ሊያስወጣ እንደሚችል ዝቷል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር በቂ ጥይት እያቀረበልን አይደለም ሲል ፍጹም ባልተመለደ ሁኔታ ጠጠር ያለ ትችት ክሬምሊን ላይ አቅርቧል።

ይህ የቫግነር መሪና መሥራች “የሩሲያ መከላከያ ሠራዊት መሪዎችና የሩሲያ ሚዲያ የሩሲያ ሕዝብን መዋሸት ማቆም አለባቸው” ሲልም ተናግሯል።

ይህ በእንዲህ ሳለ ከምዕራቡ ዓለም ላለፉት ወራት ሰፊ የጦር መሣሪያ ሲጎርፍላት የነበረችው ዩክሬን በሩሲያ ጦር ላይ የፀደይ ወራት መጠነ ሰፊ መልሶ ማጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀች መሆኑ ተሰምቷል።