የጎዳና ላይ ነጋዴ የነበረው ፓስተር ተከታዮቹን እንዴት በረሃብ እንዲሞቱ ማሳመን ቻለ?

ፓስተር ማኬንዚ (ከመሃል) ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፓስተር ማኬንዚ (ከመሃል) ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ

ባለፉት አሥርታት ብዙ አስደናቂ ሰባኪዎች ታይተዋል። የኬንያው ፓስተር ማኬንዚ ግን ይለያል።

ተከታዮቹን፣ በፍጥነት በረሃብ ሙቱና ኢየሱስን አግኙት ብሎ ያሳምናቸዋል። ያላቸውን ሳይጠራጠሩ ያደርጋሉ።

ብዙዎቹ ተከታዮቹ ታዲያ ከገጠሪቱ ኬንያ የመጡ፣ ችግር ያቆራመዳቸው ናቸው።

ያለቻቸውን ጥሪት፣ የእርሻ መሬት እና ጎጆ ለእርሱ ቤተክርስቲያን ተናዘውለት ይቺን ዓለም ይሰናበታሉ።

ፓስተሩ በአስተምህሮው ርህራሄን አያውቅም። ሕጻናት ጭምር በረሃብ እንዲሞቱ ያበረታታል።

ልጇ ‘ኢየሱስን እንዲያገኝ’ የጓጓች እናት የምትወደውን የአብራኳን ክፋይ በረሃብ ጠብሳ ሕይወቱ እንድታልፍ ታደርጋለች።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ምን ብሎ ምዕመኑን ቢሰብክ ነው ነፍሳቸውን ለእርሱ የሚሰጡት? በምን ጥበብ ነው የምዕመንን አእምሮ በዚህ ደረጃ ማጠብ የሚቻለው?

የፓስተሩን የኋላ ታሪኩን ከመመርመር እንጀምር።

ከጎዳና ላይ ንግድ ወደ ጎዳና ላይ ስብከት

ፓስተር ማኬንዚ በኬንያ በኪሊፊ አውራጃ፣ የወደብ ከተማ በሆነችው ማሊንዲ ውስጥ አነስተኛ ነገሮችን እያዞረ የሚሸጥ ነጋዴ ነበር።

የተወለደው በሱልጣን ሐሙድ ሰፈር ማኩዊኒ አውራጃ በ1960 (እአአ) ነው።

ማኬንዚ የተማረው እስከ 12ኛ ክፍል ነው።

ከዚያ ኑሮ ተጭኖት በጎዳና ላይ ንግድ ፍዳውን አይቷል። ሕይወት ዘመኑን ደንብ አስከባሪ ሲያሳድድው ነው የኖረው።

እርሱም በተራው የዋህ ምዕመናንን ማሳደድ ጀመረ። ይህንንም ከጎዳና ላይ ስብከት ነው የጀመረው።

ከጊዜ በኋላ የብሥራት ዜና ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን (Good News International Church) ብሎ የእምነት ቤት ከፈተ።

የስብከቱን ማጠንጠኛ የመጨረሻው ዘመን መቃረቡን ብቻ የተመለከተ እንዲሆን ወሰነ።

ብዙዎቹን ስብከቶች ከአሜሪካው ዝነኛ ሰባኪ ዊሊያም ብራንሃም የተቀዱ እንደሆኑ ይነገራል።

“ፓስተር ማኬንዚ የምዕመኑን አእምሮ ማጠብ የቻለው የዊሊያም ብራንሃምን አስተምህሮ በመጠቀም ነው፤ የመጨረሻው ዘመን መቃረቡን በማወጅ ሰዎች ቀድመው ተርበው በመሞት ኢየሱስን እንዲያገኙት ለተከታዮቹ ደጋግሞ ይሰብክ ነበር” ይላል ከመርማሪዎች አንዱ።

ፓስተር ማኬንዚ የጀብሎ ንግዱን ትቶ ይህን ቤተ ክርስቲያን እንደከፈተ ወደ ብልጽግና መንገድ ሰተት ብሎ አልገባም። ስኬትን ወዲያውኑ መቀዳጀት አልሆነለትም።

መልሶ ወደ ጎዳና መውጣት ነበረበት። ለንግድ ሳይሆን ለጎዳና ላይ ስብከት። በማሊንዲ ጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ ድምጽ እያሰማ መስበክ ጀመረ።

በፓስተር ማኬንዚ ትምህርት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በፓስተር ማኬንዚ ትምህርት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“የመጨረሻው ዘመን ተቃርቧል እና ንሰሐ ግቡ” እያለ ወጪ ወራጁን ያስፈራራ ነበር።

ከዚያ ወደ ሞምባሳ ሄደና በቪካትዋኒ አካባቢ በወረራ መሬት በመያዝ ቤተ ክርስቲያን ገነባ። ነገር ግን ይህ መሬት ያንተ አይደለም በሚል ፍርድ ቤት ቤተ ክርስቲያኑን አፈረሰበት። መሬቱንም ቀማው።

ከዚህ በኋላ ነው ወደ ውቧ የወደብ ከተማ ማሊንዲ ተመልሶ በመሄድ ስብከቱን እርግፍ አድርጎ በመተው ወደ ታክሲ ሾፌርነት ሥራ የገባው።

የታክሲ ሹፍርና ሥራ ከእጅ ወደ አፍ ሆነበት። ብዙ ታግሎ ውሎ ቢገባም ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ እንጂ ከባንክ ወደ አፍ ፈቀቅ አላለም።

በድጋሚ ዕድሌን ልሞክር ብሎ ተነሳ። በድጋሚ ስብከቱን ጀመረ። ቤተ ክርስቲያንም ከፈተ።

ስብከቱ የሰላ ሆነ። የሰዎችን የዕለት ተዕለት ችግር እና ስቃይ አስተጋባ። በሰዎች ፍርሃት ላይ አተኮረ። “ይቺ ዓለም ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ናት” ሲል አወጀ።

የምዕመኑ ቁጥር ከዕለት ዕለት በፍጥነት በረከተለት። ገቢውም በዚያው ፍጥነት አደገ።

የወጣት ቡድን አቋቋመ። ሴቶችን ብቻ የማማከር አገልግሎትም ጎን ለጎን ከፈተ።

ነገሮች መስመር እየያዙለት መጡ።

ፓስተር ማኬንዚ ስሙ ዜና መሆን የጀመረው በፈረንጆቹ 2019 ነበር።

ያን ጊዜ ኬንያ ሑዱማ የተባለ ዘመናዊ የዜጎች ምዝገባ ዘዴ (Huduma Namba) የሚባል 10 ቢሊየን ሽልንግ የተከሰከሰበት ሥርዓነት በማስተዋወቅ ላይ ነበረች።

ሑዱማ ማለት አንድ ዜጋ አሻራ በመስጠት ከተመዘገበ በኋላ ልዩ ቁጥር ይሰጠዋል። ያ መለያ ቁጥር ማንኛውንም የመንግሥት አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኝ ያስችለዋል።

ከተራ የመታወቂያ አገልግሎት እስከ መንጃ ፍቃድ እና የሆስፒታል ካርድ ድረስ ሁሉም በአንድ መለያ ቁጥር ይስተናገዳል።

ማኬንዚ በዚህ ጊዜ ተቆጣ። በኬንያ ሰይጣን ዘለቀ ሲል አወጀ። ተከታዮቹን በማስተባበር ከባድ ተቃውሞ አነሳ።

የሑዱማ መለያ ቁጥር ዘዴ ሌላ ሳይሆን በመጨረሻው ዘመን ይመጣል የተባለው 666 ነው አለ።

ከብዙ ተከታዮቹም በርካታ ድጋፍ አገኘ። ፖሊስ መንግሥትን በማወክ ከሰሰው። የክስ ሂደቱ ግን ሳይጀመር ከሰመ።

‘ልጆች ከራባቸው እንዲሞቱ ፍቀዱላቸው’

ፓስተር ማኬንዚ ሰዎች ከዚህ ዓለም ድሎት እና ምቾት ራሳቸው እንዲያርቁ ብቻ አልነበረም የሚሰብከው።

ይቺን ዓለም እንዲንቁ ብቻ አልነበረም ለተከታዮቹ የሚነግራቸው።

ራሳቸውን በጾም በፀሎት እንዲያተጉ ብቻ አልነበረም የሚወተውታቸው።

አሁኑኑ ሃብት ንብረታቸውን ለእርሱ ቤተ ክርስቲያን ጥለው እነርሱ ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን በረሃብ ቀጥተው ይህቺን ከንቱ ምድር እንዲሰናበቱ ነው የሚያበረታታቸው።

‘መናኛ’ የሚላትን ምድር ሲሰናበቱ ደግሞ የሚጠብቃቸው ኢየሱስ እንደሆነ እና እሱን ማግኘት የሚቻለው ግን ተከታዮቹ በረሃብ መሞት ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ይመክራቸው ነበር።

አንድ የእርሱ ቤተ ክርስቲያን የቀድሞ አባል ይህንኑ መስክራለች።

ቢቢሲ በተመለከታቸው የተቀረጹ ስብከቶቹ ግን አንዳቸውም ላይ ይህን ሲሰብክ አይሰማም።

ነገር ግን ለምዕመናኑ ማንኛውምን የሚወዱትን ነገር ሕይወትንም ጭምር መስዋዕት ማድረግ እንደሚያጸድቅ ሲናገር የሚሰማበት ቪዲዮ አለ።

ከእነዚህ ቪዲዮዎች በአንዱ ፓስተሩ ይህን ሲል ይታያል።

“ኢየሱስን መስበክ የማይሹ ሰዎች አሉ። ለምን ሲባሉ ልጆቻችን ተርበው እያለቀሱ ነው ይላሉ። ልጆቻቸው እንዲሞቱ ለምን አይፈቅዱላቸውም? ተርበው የሚያለቅሱ ልጆቸ ቢሞቱ ምንድነው ችግሩ? ችግሩ አይታየኝም።”

ፓስተሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በረሃብ እንዲሞቱ ሰብኳል የሚል ክስ ነው እየቀረበበት ያለው። ብዙዎቹ አስከሬኖች የተገኙትም ክፍት በሆነ የራሱ እርሻ ቅጥር ውስጥ ነው።

በረሃብ ተቆራምደው ደክመው ሞት የተራዘመባቸው ምዕመናን ከእርሱ የስንብት እርዳታ ያገኙ ነበር የሚሉ መረጃዎችም እየወጡ ነው።

ሆኖም ኔሽን የተባለው የኬንያ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ለፓስተር ማኬንዚ ይህንኑ የተመለከተ ጥያቄ አነሳለት። ምላሹም የሚከተለው ነበር።

“ሟቾቹ ተቆልፎባቸው አጥር ተዘግቶባቸው ተመልክተሃል? ያስገደዳቸውስ አለ?”

የፖሊስ መርማሪዎች አሰከሬኖችን ከተቀበሩበት ሲያወጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የፖሊስ መርማሪዎች አሰከሬኖችን ከተቀበሩበት ሲያወጡ

ልጆቹን እርስ በእርስ ያጋባቸው ነበር

ፓስተር ማኬንዚ በይፋ የሚታወቁ 17 ልጆች አሉት። እነዚህን ልጆች ያፈራው ከሦስት ሚስቶች ነው። አንዱ የተመሠረተበት ክስ ደግሞ ለልጆቹ መሠረታዊ ትምህርት መከልከል የሚል ነው።

በምርመራ የተደረሰበት ሌላው ጉዳይ ታዲያ ልጆቹን ትምህርት መንፈግ ብቻ አይደለም፤ ፓስተር ማኬንዚ ያደረገው። እርስ በእርሳቸው እንዲጋቡም ያስገድዳቸው ነበር ተብሏል።

“መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዘው ይህንን ነው፤ የቤተሰብ ቅርርብ ጥብቅ እንዲሆን እርስ በእርስ መጋባት አለባችሁ” ይላቸው ነበር ተብሏል።

ፓስተር ማኬንዚ በዚህ ሁኔታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንን በረሃብ አለንጋ ቀጥቶ ወደ ሞት ሲሸኝ እርሱ ግን በድሎት እና በፍሰሐ ይኖር ነበር ነው የተባለው።

በርካታ ሰፋፊ እርሻዎች፣ ባዶ መሬቶች፣ ተሽከርካሪዎች እና በርከት ባሉ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ አለው። ግማሹ የምዕመን አስከሬን ተቀብሮ የተገኘው በስሙ በተመዘገበ 300 ሔክታር መሬት ላይ ነው።

የሃብቱ መጠን ግን በውል አልተሰላም።

‘ዘመናዊ ትምህርት ሰይጣናዊ ተግባር ነው’

ፓስተር ማኬንዚ አብዝቶ ከሚሰብካቸው ጉዳዮች መካከል ዘመናዊ ትምህርት እንዴት ሰይጣናዊ ተግባር እንደሆነ ነው።

ምዕመናን በማንኛውም መልኩ ከዘመናዊ ትምህርት ራሳቸውን እንዲያርቁ፣ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት እንዳይልኩ፣ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያስወግዱ ይመክር ነበር።

“ትምህርት ሰይጣናዊ እንደሆነ እነርሱ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ለራሳቸው ትርፍ ሲሉ ይጠቀሙበታል” ይላል በአንድ የስብከት ቪዲዮ ላይ።

እንዴት ትምህርትን ለራሳቸው ትርፍ ማጋበሻነት እንደሚጠቀሙበት ሲያብራራም፤ “ዩኒፎርም ይሸጣሉ፣ እስክሪብቶ እና ደብተር ይሸጣሉ፣ ለዚህ ትርፍ ሲሉ ነው ሰይጣናዊ ትምህርቱን የሚያስቀጥሉት፤ እነሱ ይበለጽጋሉ፤ የእናንተ ልጆች በድህነት ይቆያሉ” ብሎ ያስረዳል።

ፓስተሩ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ በመስበኩ በ2017 እና በ2018 ክስ ተመስርቶበት ታስሮ ነበር። በኋላ ላይ በነጻ ተለቋል።

“ዘመናዊ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ እውቅና የለውም። ትምህርቱ የተመሳሳይ ጾታግንኙነትን ያበረታታል” ሲልም ይሰብካል።

ለኔሽን ጋዜጣ በሰጠው ቃለ ምልልስም ይህን አልካደም። “ዘመናዊ ትምህርት ቤት ልጆችን ወንድ እና ወንድ ሴት እና ሴት ጋብቻን ነው የሚያበረታቱት” ሲል ተናግሯል።

ፓስተር ማኬንዚ ለእስር አዲስ አይደለም።

ከዓመታት በፊት ማሊንዲ በሚገኘው ቤተክርስቲያኑ ያስቀመጣቸውን 90 ሕጻናት ፖሊስ በድንገት ወረራ በማድረግ ከሞት ታድጓቸዋል።

በወቅቱ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከነበሩት 35 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁሉም ‘ትምህርት የሰይጣን ነው’ በሚል ከኮሌጆቻቸው ትምህርትን ተጸይፈው እንዲወጡ ያሳመናቸው ነበሩ።

በማሊንዲ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክስ ተመሥርቶበት የነበረ ቢሆንም ተማሪዎቹ በእርሱ ላይ ለመመስከር በመፍራታቸው ወይም ባለመፍቀዳቸው በነጻ ተሰናብቷል።

ፓስተር ማኬንዚ በአንድ ወቅት የጥቃቅንና አነስተኛ የጎዳና ላይ ነጋዴ ነበር

የፎቶው ባለመብት, youtube

የምስሉ መግለጫ, ፓስተር ማኬንዚ በአንድ ወቅት የጎዳና ላይ ነጋዴ ነበር

‘ዶክተሮች ሁሉ ሰይጣን ናቸው’

የቤተሰብ ምጣኔንም አምርሮ ይቃወማል። ልጆች ካርቱን ፊልም እንዳይመለከቱ እና የሰይጣን ሥራ እንደሆነም አስተምሯል።

ፓስተር ማኬንዚ ሐኪሞች ሁሉ ሌላ ባዕድ አምላክን ያመልካሉ ሲል አስተምሯል። እናቶች በፍጹም ሐኪም ዘንድ ሄደው እንዳይወልዱ እና ልጆቻቸውን ክትባት እንዳያስከትቡም ይመክር ነበር።

በአንድ የስብከት ቪዲዮው አንዲት እናት እንዴት በጌታ ፍቃድ የጎረቤት ልጅ ያለ ሐኪም እርዳታ እንድትገላገል አንዳስቻለ እና መንፈስ ቅዱስ ጎረቤቶቿን ሁሉ ልጆቻቸውን የትኛውንም ክትባት እንዳይከተቡ እንድታስጠነቅቅ እንደተናገራት ምስክርነት ስትሰጥ ይታያል።

ከዚያ ቀጥሎ የሚናገረው ፓስተር ማኬንዚ “ከክትባት ተጠበቁ፤ ሐኪሞች የሚያመልኩት ሌላ የሰይጣን አምላክ አላቸው ከእነርሱም ተጠበቁ” ሲል ይሰማል።

ሴቶች ሰው ሠራሽ ፀጉር አንዳያጠልቁ፣ ፀጉራቸውንም ቁጥርጥር እንዳይሰሩ፣ ማንኛውንም ጌጣጌጥ እንዳያደርጉ ያሳስባል።

‘አዲስ ሰይጣናዊ ዓለም እየተገነባ ነው’

የፓስተር ማኬንዚ ዋና አስተምህሮው የዓለም ፍጻሜ መቃረብ ላይ ያጠነጠነ ነው።

ምዕመኑን ለማስፈራራትም በዓለም ላይ አዲስ ምሥጢራዊ እና ሰይጣናዊ መንግሥታት እንዳሉ ይጠቅሳል።

አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተጋግዘው አሁን ያሉትን የዓለም አገራት በመጨፍለቅ አንድ ዓለም አቀፍ ሰይጣናዊ አገዛዝ ሊያሰፍኑ እየተጉ ነው ይላል።

ከዚህ ሁሉ ሰይጣናዊ ዓለም ነጻ መሆን የሚቻለው ራስን በጾም አድክሞ ይህቺን ዓለም በመሰናበት ነው ብሎም ይሰብካል።

ይህን ያመኑ እና እንዳላቸው ያደረጉ ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 90 ኬንያውያን አስከሬን በፖሊስ ተገኝቷል። ቁጥሩ ወደ ሦስት መቶ ሊደርስ ይችላል ተብሏል።

ፓስተር ማኬንዚ ግን የምቾት ሕይወቱ ቀጥሏል። ምናልባት ከዚህ በኋላ መሰንበቻው እስር ቤት ይሆን ይሆናል።

ምዕመኑን ተራቡ እያለ የፈጀው ፓስተር ማኬንዚ መራብን ያውቃት ይሆን?

“ቅንጡ ሕይወት ነው ሲመራ የኖረው። ቤተ መንግሥት በመሰለው እና በተንጣለለው ሻካሆላ ነው የሚኖረው። ዘወትር ቤቱ ውስጥ ድግስ አለ። የምግብ ፍላጎቱም ከፍ ያለ ነው።

“ስለ ምግብ ወዳጅነቱ ሲጠየቅ ‘ምግብ ወንጌልን ጮክ ብዬ ለመስበክ ጉልበት ስለሚሰጠኝ ነው የምወደው’ ይላል” ከፖሊስ ሪፖርት የተወሰደ ቃል።