የጀርመን ርዕሰ-ብሔር ታንዛኒያን ይቅርታ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጀርመን ርዕሰ- ብሔር የሆኑት ፍራንክ ቫልተር ሽታንማየር አገራቸው በቅኝ ግዛት ዘመን በታንዛኒያዊያን ላይ ለፈጸመችው የትየለሌ በደል ይቅርታ ጠየቁ።
ርዕሰ-ብሔሩ በይፋ ይቅርታ የጠየቁት በታንዛኒያ እያደረጉ ባለው ጉብኝት ነው።
ጀርመን የዛሬዋን ታንዛኒያን ቅኝ በገዛችበት ዘመን በርካታ አሰቃቂ ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀል፣ ባርነት፣ መድፈርና ሌሎች ጸያፍ ተግባራትን በታንዛኒያ አርበኞችና ሲቪሎች ላይ አድርሳለች።
ርዕሰ ብሔር ፍራንክ ሽታንማየር በቅኝ ግዛት ዘመን የአገራቸው ሰዎች የፈጸሙትን ተግባር “አሳፋሪ” ሲሉ ገልጸውታል።
የጀርመን ወታደሮች “ማጂ ማጂ” በሚል በሚጠራው የነጻነት ትግል አመጽ እና ያንን ተከትሎ በትንሹ 300 ሺህ ሰዎችን እንደገደሉ ሰነዶች ያሳያሉ።
ይህም የሆነው እንደ አውሮፓዊኑ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ነበር።
የጀርመን ርዕሰ-ብሔር ሽታንማየር የማጂ ማጂ አመጽ የተካሄደበትን ሶንጊያ ሙዝየምን በጎበኙበት ወቅት ነው ይቅርታውን የጠየቁት።
“በዚህ ቦታ ተገኝቼ ጀርመናውያን በእናንት አያት፣ ቅድመ አያቶች ላይ ለፈጸሙት መጥፎ ተግባር ይቅርታ እጠይቃችኋለሁ” ብለዋል።
የማጂ ማጂ አመጽ የተቀጣጠለው ቅኝ ገዢዎች የአገሬውን ሕዝብ የጥጥ ምርት እንዲያመርት የጉልበት ብዝበዛ ባደረሱበት እና በተለይም ይህን የጥጥ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ በሚል የገዛ መሬቱን ቀምተው ባፈናቀሉበት ወቅት ነበር።
ታንዛኒያ ቀድሞ የጀርመን ምሥራቅ አፍሪካ ግዛት ከሚባለው ሰፊ የጀርመን ይዞታ ውስጥ አንዷ ነበረች። በዚህ ሰፊ የጀርመን ቅኝ ግዛት ክልል ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ እና ከፊል ሞዛምቢክ ይገኙበታል።
የጀርመን ርዕሰ- ብሔር ሽታንማየር ይህን የግፍ ታሪክ ወደ አገራቸው በመውሰድ ስለሆነው ነገር ሕዝብ እንዲያውቅ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።
በጀርመን አሁንም ድረስ ‘የቅኝ ግዛት ዝንጋታ ("colonial amnesia") እንዳለ በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ዚመር ይናገራሉ።
“የጀርመን ቅኝ ግዛት አጸያፊነት እና ዘረኝነት አሁን ባለው የጀርመን ማኅበረሰብ እምብዛምም አይታወቅም፤ ወይም ይዘነጋል” ይላሉ ፕሮፌሰር ዚመር።
ለሦስት ቀናት በይፋ ታንዛኒያን እየጎበኙ ያሉት ርዕሰ-ብሔር ሽታንማየር የማጂ ማጂ አመጽ መሪ የነበሩ የአርበኛ የልጅ ልጆችን አግኝተው አነጋግረዋል።
ቺፍ ሲንጊያ ኢምባኖ በማጂ ማጂ የፀረ ቅኝ ግዛት አመጽ አንጋፋ አርበኛ የነበሩ ሲሆን፣ በ1906 እንደ አውሮፓዊያኑ በስቅላት ተገድለዋል።
የእኚህን ሥመ ጥር አርበኛ የልጅ ልጆች ርዕሰ-ብሔሩ አግኝተው አነጋግረዋል።
ቺፍ ሲንጊያ ኢምባኖ አሁን በታንዛኒያ ብሔራዊ ጀግና ሆኖ ይዘከራሉ።
ርዕሰ ብሔሩ አገራቸው ጀርመን የዚህን ጀግና ቅሪት ለማግኘት ጥረት እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።
በቅኝ ግዛት ወቅት የተገደሉ ብዙዎቹ ታንዛኒያዊያን የራስ ቅላቸው እና ሌሎች የሰውነት ክፍላቸው ዘረኛ ለሆኑ ምርምሮች እና አንዳንዴም እንደ ጀብዱ ወደ ጀርመን ይላኩ ነበር።
የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሳን ጀርመን በቅኝ ግዛት ወቅት የዘረፈቻቸውን ቅርሶች ለመመለስ ጥረት እንድታደርግ ርዕሰ-ብሔሩን ጠይቀዋል።
በታንዛኒያ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት መሐመድ ሰኢድ የጀርመኑን ርዕሰ-ብሔር ይቅርታ በበጎ እንደሚመለከቱት ጠቅሰው ነገር ግን ይህ በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
“በዚያ ዘመን ሕዝቡ እንዳይታገላቸው እና እንዲራብ እርሻዎችን በእሳት ያነዱ ነበር። ይህ በዛሬ ሕግ ቢሆን ፍርድ ቤት የሚያስቆም ወንጀል ነው” ይላሉ መሐመድ ሰኢድ።
እንደ ታሪክ ተመራማሪው መሐመድ ሰኢድ ሐሳብ ጀርመን ታንዛኒያ መካስ አለባት።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ2021 ጀርመን በናሚቢያ የቅኝ ግዛት ዘመን ለፈጸመችው የዘር ማጥፋት ተግባር የ1.3 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ እርዳታ ሰጥታ ነበር።
በተመሳሳይ በኬንያ ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ በማኦ ማኦ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ወቅት አገራቸው እንግሊዝ ለፈጸመችው ተግባር በይፋ ተቀባይነት እንዳልነበረው ጠቅሰዋል።
ይሁንና ንጉሥ ቻርለስ አገራቸው ለፈጸመችው አሰቃቂ የቅኝ ግዛት ዘመን ግፎች ኬንያዊያንን በይፋ ይቅርታ አልጠየቁም።












