የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በጋዛ ‘ደኅንነቱ የተጠበቀ’ ቦታ የለም አሉ

የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በጋዛ ‘ደኅንነቱ የተጠበቀ’ ቦታ የለም አሉ። ይህ የተባለው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ከሐማስ ጋር አየተደረገ ባለው ግጭት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየቀረቡ ያሉትን ጥሪዎች ውድቀ ማድረጋቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ ማን ናቸው?

  2. ቱርክ የእስራኤል አምባሳደሯን ጠራች

    ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ቱርክ በእስራኤል የሚገኙ አምባሳደሯን መጥራቷን የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።

    ሚኒስቴሩ አምባሳደሩ የተጠሩት እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ስላለችው ድብደባ እና በጋዛ ስለተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ምክክር ለማድረግ ነው ተብሏል።

    ከእስራኤል-ጋዛ ጦርነት በኋላ ቴል አቪቭ እና አንካራ ከፍተኛ ወደሚባል የዲፕሎማሲ ፍጥጫ እየገቡ ነው።

    ከጥቂት ቀናት በፊት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን እስራኤልን “የጦር ወንጀለኛ” ብለው መናገራቸውን ተከትሎ እስራኤል በቱርክ ያላትን አምባሳደሯን ጨምሮ ሁሉም ዲፕሎማቶቿን ጠርታለች።

  3. የአሜሪካ ባለስልጣን በሰሜን ጋዛ 400ሺህ ያክል ሰዎች መኖራቸውን ገለጹ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ በሰሜናዊ ጋዛ 400ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መኖራቸውን ተናገሩ።

    ባለፉት ሳምንታት የእስራኤል ጦር ነዋሪዎች ከሰሜን ጋዛ ወጥተው ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው ወደምትለው ደቡባዊ ጋዛ እንዲያመሩ ስታሳስብ ቆይታለች።

    የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ አንስቶ እስራኤል በተለይ በሰሜን ጋዛ የማያባራ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ስትፈጽም ቆይታለች።

    ሳተርፊልድ ዛሬ በጆርዳን መዲና አማን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ 800ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ደቡባ ጋዛ መሸሻቸውን ገልጸው ከ350-400ሺህ የሚሆኑት ግን አሁንም በሰሜን ጋዛ ይገኛሉ ብለዋል።

  4. የእስራኤል ጦር በጋዛ ትልቁ አውራ ጎዳና ላይ ለሦስት ሰዓታት ለትራፊክ ክፍት ነው አለ

    የእስራኤል ጦር በጋዛ ከሚገኙ ሁለት ግዙፍ ዋና መንገዶች መካከል አንዱ የሆነው ሳላህ አል-ዲን ለሦስት ሰዓታት ያክል ለትራፊክ ክፍት ሆኖ ይቆያል አለ።

    ጦሩ በኤክስ ገጹ ላይ ነዋሪዎች ከሰሜናዊ ጋዛ ወደ ደቡብ ጋዛ እንዲሄዱ የሚያስችለው መንገድ ዛሬ ከሰዓት ለትራፊክ ክፍት ነው ብሏል።

    እስራኤል ሰሜናዊ ጋዛ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ስለምወስድ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ደቡባዊ የጋዛ ሰርጥ እንዲያመሩ ስታሳስብ ቆይታለች።

    ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሰብዓዊ ድርጅቶች የትኛውም የጋዛ ክፍል ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም ይላሉ።

  5. ብሊንከን ከሌባኖስ እና ኳታር መሪዎች ጋር ተገናኙ

    ብሊንከን ከኳታሩ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ብሊንከን ከኳታሩ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሌባኖስ እና ኳታር ጠቅላይ ሚንስትሮች ጋር ተገናኙ።

    ብሊንከን መሪዎቹን እያነጋገሩ ያሉት በጆርዳን ነው።

    ብሊንከን ቀደም ሲል ከሌባኖስ ግዚያዊ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ ጋር ተገናኝተዋል።

    ብሊንከን ከሌባኖሱ ግዚያዊ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ብሊንከን ከሌባኖሱ ግዚያዊ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር

    የግዚያ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጸ/ቤት ከብሊንከን በነበራቸው ውይይት ሌባኖስ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ስለመጠየቋ አስታውቋል።

    አንቶኒ ብሊንከን ከጆርዳን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ጋርም እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

  6. ብሊንከን ዛሬ በጋዛ ጉዳይ ከበርካታ የአረብ አገራት መሪዎች ጋር ሊነጋገሩ ነው

    ብሊንከን

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በእስራኤል ሐማስ ጦርነት ዙሪያ ከበርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መሪዎች ጋር ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

    የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ከሌባኖስ፣ ኳታር እና ጆርዳን መሪዎች ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

    ብሊንከን በአሁኑ ወቅት ጆርዳን የሚገኙ ሲሆን ከጆርዳን ንጉሥ አብዱላህ ሁለተኛ ጋር እና ከኳታር ጠቅላይ ሚንስትር ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

    ብሊንከን ቀደም ሲል ከሌባኖስ ግዚያዊ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ ጋር ተገናኝተዋል።

    አንቶኒ ብሊንከን ከጆርዳን፣ ሌባኖስ፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ጋርም እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

  7. “አንዳንድ ጊዜ ከካሜራ ጀርባ ቆሜ አለቅሳለሁ” የጋዛው ጋዜጠኛ

  8. እስራኤል የሐማስ መሪ መኖሪያ ቤትን በሚሳኤል መታች

    የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬ

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ለሐማስ ቅርበት ያላቸውን መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ እስራኤል የሐማስ የፖለቲካ መሪ መኖሪያ ቤትን በሚሳኤል መትታለች።

    ኢስማኢል ሃኒዬ እአአ 2009 ላይ ከጋዛ ሰርጥ ወጥቶ ቋሚ መኖሪያውን በቱርክ እና ኳታር አድርጓል። ጥቃቱ ሲፈጸምም ኢስማኢል ሃኒዬ ከጋዛ ውጭ ስለመሆኑ ሪፖርቶች ጠቁመዋል።

    በጋዛ በሚገኘው ኢስማኢል ሃኒዬ መኖሪያ ቤት ላይ በደረሰው ጥቃት በቤተሰብ አባላቱ ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

  9. የእስራኤል ጦር የውሃ ታንከሮችን፣ ጄነሬተሮችን፣ የሶላር ሳህኖችን ዒላማ ማድረጉ ተገለጸ

    የእስራኤል ጦር ሌሊቱን በጋዛ ባደረገው ድብደባ የውሃ ማከማቻ ታንከሮችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይሉ የሚያመነጩ ጄነሬተሮችን እና ሶላር ሳህኖችን ዒላማ ማድረጉ ተገለጸ።

    አናዱሉ፣ ቲአርቲ ዎርልድ እና አል ጀዚራ እንደዘገቡት በምዕራብ ጋዛ ለሚገኘው ናሰር የሕጻናት ሆስፒታል ከጸሐይ ብርሃን የኤሌክሪክ ኃይል አቅርቦት ይሰጡ የነበሩ የሶላር ሳህኖች በአየር ድብደባ እንዲወድሙ ተደርገዋል።

    የምስራቅ ራፋህ ነዋሪዎች የውሃ ማከማቻ ታንከርም እንዲሁ በእስራኤል ድብደባ ተመትቷል።

    በጋዛ ከተማ የአል-ዋፋ ሆስፒታል ዋነኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ የሆነ ጄኔሬተርም ተመትቶ ከጥቅም ውጭ መሆኑ ተዘግቧል።

  10. የፔንታገን ቃል አቀባይ፡ “ግጭቱ ወደ ቀጠናው እንዳይሻገር ተደርጓል”

    ብርጋዴር ጀነራል ፓትሪክ ኤስ ራይደር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፔንታገን ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል ፓትሪክ ኤስ ራይደር አሁን ባለው ሁኔታ የእስራኤል እና ሐማስ ግጭት ወደ ቀጠናው እንዳይስፋፋ ማድረግ መቻሉን ገለጹ።

    ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ “አሁን ግጭቱ የእስራኤልና ሐማስ ብቻ ነው” ብለዋል።

    የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስረላህ ከግጭቱ መነሳት በኋላ የመጀመሪያ ንግግራቸውን ትላንት ማድረጋቸውን ተከትሎ ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ፣ ግጭቱ ቀጠናዊ እንዳይሆን ማድረግ “የመንግሥታችንና መከላከያችን ዋነኛ ትኩረት ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

    ሁለት ተዋጊ አውሮፕላ ተሸካሚ መርከቦችን አሜሪካ ያስጠጋችው በዚህ ምክንያት እንደሆነም አክለዋል።

    “ቀጠናዊ ግጭት ተቀልብሷል ብለን እናምናለን። ከኢራን ጋር መጋጨት አንሻም። በቀጠናው ግጭት እንዲስፋፋ አንፈልግም። ግጭቱን አስቁሞ መረጋጋት ማስፈን ነው ግባችን” ብለዋል።

  11. የተመድ ባለሥልጣን በጋዛ ‘ደኅንነቱ የተጠበቀ’ ቦታ የለም አሉ

    ከፍርስራሽ ስር ሰዎች ሲፈለጉ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በጋዛ አሁን ላይ “ደኅንነቱ የተጠበቀ አንዳችም ቦታ የለም” አሉ።

    የተመድ ሕንጻዎች ለበርካታ የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ ሆነዋል።

    የተመድ ባለሥልጣኑ ቶማስ ዋይት ተቋሙ ለተፈናቃዮች ከለላ መስጠት ከአቅሙ በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል።

    በተመድ ከለላ የሚሹ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንደማይሆን ገልጸዋል።

    የተመድ የፍልስጥኤማውያን ተፈናቃዮች ተቋም ያስጠለላቸውን 600,000ተፈናቃዮች ደኅንነት ከዚህ በኋላ ለማረጋገጥ እንደሚቸገር ገልጿል።

    የተመድ የጋዛ ቅርንጫፎች “ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል” ብለዋል ባለሥልጣኑ።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የቀረበውን ሰብአዊ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንደማይቀበሉ ገልጸዋል።

    ብሊንከን አሁን በዮርዳኖስ የሚገኙ ሲሆን፣ ከአረብ አገራት መሪዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

  12. ኤል ጋዚ ለፍልስጥኤማውያን ድጋፉን በመግለጹ ክለቡ ውሉን አቋረጠ

    አንዋር ኤል ጋዚ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, አንዋር ኤል ጋዚ

    የክንፍ ተጫዋቹ አንዋር ኤል ጋዚ በማሕበራዊ ሚዲያ ገጹ ለፍልስጥኤማውያን ድጋፉን በመግለጹ ክለቡ ውሉን ሰረዘ።

    የጀርመኑ ሜንዝ የ28 ዓመቱ ተጫዋች ውል የሰረዘው ተጫዋቹ ለፍልስጥኤማውያን ድጋፍ የሚገለጽ መግለጫው እና ማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራቸው ይዘቶች ነው ብሏል።

    ኤል ጋዚ ከክለቡ ጋር የነበረው ውል መሰረዙን ተከትሎ “ለብቻችንንም ቢሆን ትክክል ለሆነው ነገር ጸንተን መቆም አለብን” ብሏል።

    ተጫዋቹ በጋዛ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እንዲቆም ሲጠይቅ ነበር።

    የኔዘርላንድስ ዜግነት ያለው ኤል-ጋዚ ከዚህ ቀደም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለአስቶን ቪላ እና ኤቨርተን ተጫውቷል።

  13. የእስራኤል ባለሥልጣን ሐማስ ከሆስፒታል ስር ማዘዣ ጣቢያ አለው አሉ

    የጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አማካሪ ማርክ ሬጌቭ ሐማስ ከሆስፒታል ስር የማዘዣ ጣቢያ እንዳለው እስራኤል መረጃው አላት አሉ።

    ይህ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሐማስ ማዘዣ ጣቢያ በጋዛ ትልቁ በሆነው አል-ሺፋ ሆስፒታል ስር የሚገኝ መሆኑን ቻናል 4 ለተባለ የዩኬ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

    ሬጌቭ የጠላት ኃይል በሰላማዊ ሰዎች መሠረተ ልማት ስር መሰል ግንባታ ካላው መሠረተ ልማቱ “ዒላማ ሊደረግ ይችላል” ብለዋል።

    እስራኤል በጋዛ በትልቁ ሆስፒታል ፊት ለፊት ጥቃት አድርሳ አምቡላንስ አውድማ 13 ሰዎች ስለመግደሏ ሪፖርት ተደርጓል።

  14. ዶ/ር ቴድሮስ ሆስፒታል አቅራቢያ ፍንዳታ ማጋጠሙ 'እጅግ አስደንግጦኛል' አሉ

    እናት እና ልጅ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከጋዛ ትልቁ ሆስፒታል ፊት ለፊት ፍንዳታ ማጋጠሙ 'እጅግ አስደንግጦኛል' አሉ።

    ዋና ዳይሬክተሩ በሪፖርቱ እጅግ መደናገጣቸውን ገለጸው በፍንዳታው ምክንያት ሰዎች መሞታቸውን፣ መጎዳታቸውን እና በሆስፒታል ንብረት ላይ ውድመት ማጋጠሙን ገልጸዋል።

    “ታማሚዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የሕክምና ጠቋማት እና አምቡላንሶች በየትኛውን ጊዜ ሊጠበቁ ይገባል። ሁልግዜም። አሁኑኑ የተኩስ አቁም ይደረግ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

    ቀደም ሲል በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚንስቴር አል-ሺፋ ሆስፒታል ፊት ለፊት ባጋጠመው ፍንዳታ 13 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።

  15. የእስራኤል ጦር አምቡላንስ መምታቱን ገለጸ

    አምቡላንሱን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል አየር ኃይል በጋዛ አምቡላንስ መምታቱን ገለጸ።

    ጦሩ አምቡላንሱን የመታው ተሸከርካሪው “በሐማስ ሽብርተኛ ቡድን ሴል” ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን በማረጋገጤ ነው ብሏል።

    የእስራኤል ጦር አምቡላንስን በመጠቀም ሐማስ አባላቱን እና ጦር መሳሪያዎችን እያዘዋወረ ስለመሆኑ መረጃው አለኝ ብሏል።

    በጋዛ ከተማ ትልቁ ከሆነው አል-ሺፋ ሆስፒታል ፊት ለፊት ከፍተኛ ፍንዳታ ስለማጋጠሙ ተዘግቧል።

    ቢቢሲ ያረጋገጣቸው ምስሎች በፍንዳታው የወደመ አምቡላንስ እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከሆስፒታሉ ፊት ለፊት ወድቀው ያሳያሉ።

    እስራኤል አሁንም ሰዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ወደ ደቡብ ጋዛ እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ መስጠቷን ቀጥላለች።

    “ይህ ቀጠና የውጊያ አካባቢ በመሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ለራሳቸው ደኅንነት ሲሉ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንዲሄዱ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል” ብሏል ጦሩ በመግለጫው።

  16. ኔታኒያሁ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረቡ ጥያቄዎችን ወደቅ አደረጉ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ከሐማስ ጋር አየተደረገ ባለው ግጭት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እየቀረቡ ያሉትን ጥሪዎች ውድቀ አደረጉ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው፣ ሐማሰ በእስራኤል ላይ ጥቃት በሰነዘረበት ወቅት የታገቱ ሰዎች በሙሉ አስከሚለቀቁ ድረስ በሚቀርቡት የተኩሰ አቁም ጥሪያዎች እንደማይስማሙ ገልጽ አድርገዋል።

    ኔታኒያሁ ይህንን የተናገሩት ዛሬ አርብ እስራኤልን የጎበኙት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ግጭቱ ጋብ እንዲል በድጋሚ ጥሪ ካቀረቡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። ብሊንከን ተኩስ ማቆም ከተደረገ “ታጋቾች እንዲለቀቁ አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል” ብለው ነበር።

    ብሊንከን ግጭቱ በጊዜያዊነት እንዴት ጋብ እንደሚል “ውይይት የሚደረግበት ይሆናል” በማለት፣ ይህ ግን እንዴት መሆን አለበት በሚለው ዙሪያ እስራኤል “ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎች አሏት” ሲሉ ተናግረዋል።

    ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ “እስራኤል የታገቱብንን ሰዎች ማስመለስን የማይጨምር ጊዜያዊ ተኩስ አቁምን እንደማትቀበል አሳውቀናል” ብለዋል።

    መደበኛ የተኩስ አቁም በአብዛኛው ተፋላሚ ወገኖች ንግግር እንዲያደርጉ የሚያስችል ረጅም ጊዜን የሚጠይቅ ሲሆን፣ ለሰብአዊ እርዳታ ግጭትን ማቆም ግን ለሰዓታት የሚቆይ ሊሆን ይችላል።

  17. የሒዝቦላህ መሪ ሐማሰ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት አደነቁ

    የመሪውን ንግግር ለመሰማት አደባባይ የወጡት የሒዝቦላህ ደጋፊዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የመሪውን ንግግር ለመሰማት አደባባይ የወጡት የሒዝቦላህ ደጋፊዎች

    በሊባኖስ ውስጥ በወታደራዊ እና በፖለቲካዊ አቅሙ ኃያል የሆነው የእስላማዊው ቡድን ሒዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ በእስራኤል እና በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተያየታቸውን ሰጡ።

    ናስራላህ ከምስጢራዊ ስፍራ በሰጡት እና በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤየሩት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው በተከታተሉት ንግግራቸው፣ ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጸሞ 1,400 ሰዎችነ የገደለበተን አርምጃ አድንቀዋል።

    አንደ ሒዝቦላህ ሁሉ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በምዕራባውያን አገራት ሽብርተኛ ድርጅት የተባለው ሐማስ፣ የወሰደው እርምጃ “ትክክለኛ፣ ብልህ እና ፍትሃዊ” ነው በማለት፣ በእስራኤል ላይ ላይ የተፈጸመው ጥቃት “100% የፍልስጤማውያን ነው” በማለት ገልጸውታል።

    ናስራላህ በንግግራቸው አሜሪካ በጋዛ ውስጥ ለሚካሄደው ጦርነት ተጠያቂ ናት በማለት በቁጣ ተችተዋል።

    በተጨማሪም በየመን እና በኢራቅ ያሉ በኢራን የሚደገፉ ኃይሎችን አመስግነዋል። በየመን የሚገኙት ሁቲ አማጺያን በእስራኤል ላይ ድሮኖችን ያስወነጨፉ ሲሆን፣ የኢራቅ ሺዓ ሚሊሻዎች ደግሞ በኢራቅ እና በሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃት ማድረሳቸው ይታወቃል።

    ኢራን ዋነኛውን ኃያል ቡድን ሒዝቦልህን ጨምሮ በኢራቅ ያሉ ሚሊሻዎችን፣ የሶሪያውን መሪ ባሻር አል-አሳድን፣ የሁቱ አማጺያንን እና ሐማስን የካተተውን እንቅስቃሴ ትደግፋለች።

  18. የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ "ተሰማርቷል እንዲሁም ዝግጁ ነው" ተባለ

    የእስራኤል ጦር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ የሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ።

    የእስራኤል ጦር ቃለ አቀባይ ኮሎኔል ሪቻርድ ሄክት የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በድንበር አቅራቢያ "ተሰማርቷል እንዲሁም ዝግጁ ነው" ብለዋል።

    አክለውም ጦሯቸው "ለመከላከል ዝግጁ" መሆኑንም ተናግረዋል። "ለሊባኖሳውያን የወደፊት ዕጣ ፈንታችሁን ለሐማስ አትሰው እያልን ነው" ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ የእስራኤልና ሐማስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ንግግር ያደርጋሉ በተባለበትም ወቅት ነው ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት።

    የሊባኖሱ የሺዓ ሙስሊም ቡድን መሪ እስከዛሬ ድረስ ለተከታዮቻቸው በአደባባይ ያሉት ነገር የለም። ሄዝቦላህ በቀጣይ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ሐሰን ናስራላህ ዛሬ በሚያደርጉት ንግግራቸው እንደሚጠቁሙ ይጠበቃል።

  19. ከአየር ጥቃቶቹ በፊት ስድስት ሚሊዮን አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች ማስጠንቀቂያ ተልኳል- እስራኤል

    የጋዛ የአየር ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የአየር ጥቃት ከመጀመሯ በፊት የማስጠንቀቂያ በራሪ ወረቀቶች መበተኗን ፕሬዚዳንቷ አይዛክ ሄርዞግ ለጋዜጠኞች አሳይተዋል።

    ስድስት ሚሊዮን አጭር የጽሁፍ መልዕክት እንደተላከ፣ አራት ሚሊዮን ስልክ እንደተደወለ እና 1.2 ሚሊዮን በራሪ ወረቀቶች ተበትነዋል ብለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ተበትኗል ብለው እያሳዩ የነበረውን በራሪ ጽሑፍ ላይ የተጻፈውን ማስጠንቀቂያ ቢቢሲ ማንበብ አልቻለም።

    እስራኤል በጃባሊያ መጠለያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን በዚህም ጥቃት ለሰላማዊ ዜጎች ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል በማለት አገራቸው አለም አቀፉን ህግ በማክበር ነው የምትሰራው ብለዋል።

    እስራኤል በተከታታይ ቀናት በጃባሊያ መጠለያ የፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶችን የተበባሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ "ግልጽ የሆነ የዓለም አቀፍ ህግ ጥሰት ነው" ሲሉ አውግዘውታል።

    አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባደረጉት ንግግር ሁለቱንም አካላት በስም ባይጠቅሱም ሐማስ ሰላማዊ ዜጎችን ሸፋን በማድረግ እንዲሁም እስራኤል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን በአስገዳጅ ሁኔታ ማፈናቀሏን ጠቅሰዋል።

  20. በጋዛ- እስራኤል የተከሰቱ የቅርብ ጉዳዮች

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በጋዛ- እስራኤል የተከሰተው ቀውስ አንድ ወር ሊሞላው የቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው።

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የአየር እና የምድር ጥቃቶችን እንዲሁም ከባህር በሚወነጨፉ ሚሳኤሎች የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏን ጦሯ አስታውቋል።

    • የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እስራኤል ገብተዋል። ሐማስ የፈጸመውን መብረቃዊ ጥቃት ተከትሎም ኃላፊው ለሶስተኛ ጊዜ ነው እስራኤልን ሲጎበኙ። የአሜሪካው ባለስልጣን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር የተገናኙ ሲሆን በጋዛ ሰርጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ "ተጨባጭ እርምጃዎች" ላይ እንደሚያተኩሩም ተገልጿል።
    • የእስራኤል ጦር የጋዛ ከተማን ሙሉ በሙሉ መክበቡን አስታውቋል።
    • በግብጽ በኩል ያለው የራፋህ የድንበር ማቋረጫ ከረቡዕ ጀምሮ ለሶስተኛ ጊዜ ተከፍቷል። ማቋረጫው የተከፈተው ጥምር ዜግነት ያላቸውን ዜጎች ለማስወጣት ነው።
    • እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እየፈጸመችው ባለው የአየር ጥቃቶች ከ9 ሺህ ሰዎች በላይ መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
    • ከጋዛ ወደ እስራኤል ለስራ ሄደው የነበረ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የስራ ፈቃዳቸው ተሰርዞ ወደ ጋዛ እንዲመለሱ መደረጋቸውን የእስራኤል መንግሥት አስታውቋል።
    • በዌስት ባንክ በተፈጸመው ጥቃት ስምንት ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም የህክምና ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።
    • በጋዛ ሴቶችና ህጻናት ጨምሮ 242 ግለሰቦች በሐማስ ታግተዋል።