120 ሺህ እስራኤላውያን የጦር መሣሪያ ፍቃድ እንዲሰጣቸው የጠየቁት ለምንድነው?

ጠመንጃ አንግታ ልጇን አቅፋ በመንገድ ላይ የምትጓ እስራኤላዊት እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከሐማስ ድንገተኛ ጥቃት በኋላ በእስራኤላውያን ዘንድ ከፍተኛ የመታጠቅ ፍላጎት ተፈጥሯል

ከሳምንታት በፊት ሐማስ ባደረሰው መብረቃዊ ጥቃት ከ1,400 በላይ እስራኤላውያን መገደላቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ እስራኤል የአጸፋ እርምጃ መውሰዷን ቀጥላለች።

ይህ በአንዲህ እያለ 120 ሺህ የሚሆኑ እስራኤላውያን የጦር መሣሪያ ፍቃድ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል። በዚህም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ለመታጠቅ በስፋት ማመልከቻ እያስገቡ ነው።

የተኩስ ዒላማ ልምምድ የሚደረግባቸው ማዕከሎች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዜጎች ተሞልተዋል። ብዙ እስራኤላውያን ራሳቸውን ካልተጠበቀ ጥቃት ለመጠበቅ የተኩስ ዒላማ ልምምድ በማድረግ ተጠምደዋል።

የጦር መሣሪያ መሸጫ መደብሮችም በበርካታ መሳሪያ ፈላጊዎች እየተጎበኙ ነው። ከዚህ ቀደም መሣሪያ ገዝተው የማያውቁ ዜጎች ሳይቀር መሣሪያ ለመሸመት ረዣዥም ሰልፎች ላይ በትዕግስት ቆመው ይታያሉ።

ወቅታዊውን ሁኔታ ተከትሎ እስራኤል ጦር መሣሪያ የመታጠቅ ቅድመ ሁኔታዎችን ለዜጎቿ አላልታለች። ከዚህ ቀደም የጤና እክል እና የወንጀል ታሪክ የሌላቸው ዜጎች ከሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ፈቃድ ይሰጣቸዋል።

ለምሳሌ አንድ ግለሰብ 100 ጥይት ጎራሽ ይሰጠዋል። ቀደም ሲል 50 ጎራሽ ብቻ ነበር የሚፈቀድለት።

“አሁን ቅድመ ሁኔታዎቹ በመላላታቸው መሣሪያ መታጠቅ ለዜጎች ቀላል ሆኗል” ይላል ኦምሪ ሽናይደር። ኦምሪ የ41 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን፣ በሙያው ጠበቃ ነው። በኪቡትዝ ነዋሪ ነው። ኪቡትዝ ከኢየሩሳሌም ወጣ ብላ የምትገኝ ከተማ ናት።

የዒላማ ተኩስ የሚለማመድ እስራኤላዊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዒላማ ተኩስ የሚለማመድ እስራኤላዊ

ሽናይደር ይህ በጅምላ እና በዘመቻ ዜጎችን ጦር መሣሪያ የማስታጠቁ ውሳኔ ብዙም አላስደሰተውም። ለሲቪሎች በዚህ ደረጃ ይህን ያህል መሣሪያ መስጠት በኋላ ብዙ ጣጣ ይዞ ይመጣል የሚል ስጋት አለው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“እርግጥ ጥቅም አለው፤ ጉዳትም አለው። ጉዳቱን ለማየት አሜሪካንን ማየት ነው። እዚያ በየጊዜው ምን እንደሚሆን እናያለን። ቀላል ውሳኔ አይደለም። ነገር ግን እስራኤላውያን ደኅንነት እንዲሰማቸው ማድረግ ያለብን ነገር ነው እያደረግን ያለነው” ይላሉ ሚኒስትር ኢታማን ቤን ቪር።

ሚኒስትሩ የቀኝ አክራሪ ፓርቲ አባል፣ የብሔራዊ የደኅንነት ሚኒስትር እና ሰዎች የመታጠቅ መብት ሊሰጣቸው ይገባል በሚል ለረዥም ጊዜ ሲታገሉ የኖሩ ሰው ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት አሁን በዋናነት መሣሪያው እየታደለ ያለው ጋዛ ድንበር አካባቢ ለሚኖሩ ዜጎች ነው። በተለይም አይሁድ እና አረቦች ተቀላቅለው የሚኖሩባቸው ከተሞች።

አሁን ሁሉም አይሁዶች በየሰፈራቸው የደኅንነት ቡድን እንዲመሠርቱ እየተበረታቱ ነው። አረብ የአገሪቱ ዜጎች ግን ይህ ዕድል የላቸውም።

ሽናይደር በኪቡትዝ ነዋሪ ነው። ወደ 200 ቤተሰቦች በዚያ ይኖራሉ። ይህ በነዋሪዎች ተነሳሽነት የደኅንነት ጥበቃ አገልግሎት በየቦታው መጀመሩን ይደግፋል።

“ለምሳሌ ኪቡትዝ ያለው ሁኔታን ከግምት ውስጥ ስናስገባ መታጠቅ እንዳለብን ተረድተናል። አይበለውና ባለፈው እንደሆነው ዓይነት ጥቃት ከመጣ ራሳችንን ለመከላከል ይረዳናል” ይላል።

ምንም እንኳ በርካታ አይሁድ እስራኤላውያን ደኅንነት እንዲሰማቸው እየታጠቁ ቢሆንም፣ የሕዝቡን 20 ከመቶ የሚሆኑት የእስራኤል-አረቦች ግን በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ናቸው።

መገለል፣ መነጠል፣ መንጓጠጥ እና ሌሎች ጥቃቶችን በየቀኑ እንደሚያስተናግዱ ቢቢሲ በተደጋጋሚ በሠራቸው ዘገባዎች ለመረዳት ችሏል።

በማዕከላዊ እስራኤል የምትገኘው ሎድ የተባለችው ከተማ ከዚህ ቀደም በአረብ-እስራኤሎች እና በአይሁድ-እስራኤሎች መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት አጋጥሟታል።

ሱሃይር ሐምዱኒ
የምስሉ መግለጫ, ሱሃይር ሐምዱኒ

ሱሃይር ሐምዱኒ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ተንከባካቢ መምህርት ናት። ሕይወቷን ሙሉ በዚህ ሎድ በምትባለው ከተማ ነው የኖረችው።

በዚያ ማዶ አይሁዶች በዚህኛው ማዶ ደግሞ አረብ እስራኤሎች ይኖራሉ።

እሷ እንደምትለው የሐማስን ጥቃት ተከትሎ ገበያ ለመውጣት እንኳን አስፈሪ ሆኖባታል። በተለይ አይሁዶች የሚበዙበት ሰፈር ሱፐርማርኬት መሄድ ራሱ የሚታሰብ አይደለም።

ስለዚህ ራቅ ወደሚሉት የአረብ-እስራኤል ሱቆች ለመሄድ ትገደዳለች።

“ከዚህ ቀደም ቤታችን ቁጭ ብለንም ጥቃት ደርሶብናል። ያ የቀድሞው ፍርሃት ዛሬም አልሻረም” ትላለች።

በእስራኤል ውስጥ አረብ-እስራኤሎች ለብሔራዊው ወታደራዊ አገልግሎት አይገደዱም። ፍልስጤማውያን ተደርገው ነው የሚታሰቡት። ወታደራዊ ሥልጠናም ስለማይሰጣቸው የጦር መሣሪያ ፍቃድ ለማውጣት ዕድሉ አይኖራቸውም።

“አይሁዶች ራሳቸውን እንዲከላከሉ ልምምድ እንዲያደርጉ ሲበረታቱ [እኛ] እኔ እና ልጆቼ ግን ልንሞት እንደምንችል ነው የምናስበው። ሞቴን የማስበው ጥፋት አጥፍቼ አይደለም። የአረብ ዝርያ ስላለኝ ብቻ እንጂ። አይሁድ ጎረቤቶቼ ራሳቸውን እንዲከላከሉ መሣሪያ መታጠቅ ከተፈቀደላቸው፣ ስለምን ለእኛ አይፈቀድልንም?” ትላለች።

የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ በጎብኚዎች ይጨናነቁ የነበሩ የእስራኤል ከተሞች አሁን ጭር ብለዋል። ሬስቶራንቶች እና ሱቆች በብዛት ዝግ ናቸው።

“60 ከመቶ የሬስቶራንቱ ደንበኞቼ አይሁዶች ናቸው” ይላል አቡ አሚር። አሚር የሎድ ሬስቶራንት ባለቤት ነው።

“አሁን ግን ማንም እኔ ዘንድ አይመጣም። አሁን ያለው ነገር አስፈሪ ነው። አረቦች ወደ አይሁዶች ሰፈር መሄድ ይፈራሉ። አይሁዶች ደግሞ ወደ አረብ ሰፈሮች ለመሄድ ይፈራሉ።”