ቤተ-እስራኤላዊው አቨራ መንግሥቱ እና ለዓመታት በሐማስ እገታ ሥር ያሉ ሌሎች እስራኤላውያን

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከሰሞኑ በሐማስ ታግተው የተወሰዱ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል።
ሆኖም ግን በሐማስ ታግተው የተወሰዱ እነዚህ ብቻ አይደሉም።
ሐማስ ለዓመታት ቢያንስ ሁለት እስራኤላውያንን ይዟል።
ስለ ኢትዮጵያዊ-እስራኤላዊው አቨራ መንግሥቱ እና ስለ የቦዴያን አረብ-እስራኤላዊው ሒሻም አል-ሳይድ ብዙም አልተሰማም። የታገቱት ከስምንት ዓመታት በፊት እአአ በ2014 እና 2015 ነው።
ከ2014 ጀምሮ ሁለት እስራኤላዊ ወታደሮች የሆኑ እና አስክሬን ለቤተሰባቸው ያልሰጠ እስራኤላውያንም አሉ።
ሐዳር ጎልዲን እና ኦሮን ሻሁል እምና በእስራኤልና ሐማስ ውጊያ ነው የተገደሉት።
በኢራን የሚደረገፈውን ሐማስ ምዕራባውያን አሸባሪ ቡድን ይሉታል። እስራኤላዊ ታጋቾችን ለመልቀቅ ከፍተኛ ገንዘብ ጠይቋል። እንደ መደራደሪያም ነው የተያዙት።
የኦሮን ወንድም የሆነው አቪራም ሻሁል እንደሚለው ለ10 ዓመታት የኦሮን አስክሬን የት እንደሆነ ሐማስ ለቤተሰቡ አላሳወቀም።
በ2014 የኦሮን ጥይት ተከላካይ ጃኬት እና የራስ ቆብ በጋዛ የሐማስ መተላለፊያ ውስጥ ተገኝቷል።
ከዚያ በኋላ ግን የኦሮን ወንድም እንደሚለው “እስራኤለውያን ረስተውታል።”
“ወንድሜን ማምጣት የሚቻልበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው። 200 ታጋቾች ጋዛ ይገኛሉ። ወንድሜን ለመመለስ በቂ ጥረት መንግሥት አላደረገም። አሁን ግን ከፍተኛ ሙከራ ማድረግ አለበት” ይላል አቪራም።
እስራኤል ሰብአዊ ስምምነት አድርጋ ታጋቾችን ማስለቀቅ እንዳለባት ይናገራል።
“ሐማስ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ ከፈለገ ታጋቾቹን መልቀቅ አለበት። የወታደሮችን አስክሬን መመለስ አለበት” ይላል።
በ2011 በተደረገ ምሥጢራዊ ስምምነት እስራኤል ጊላድ ሻሊት የተባለ ወታደርን በ1,027 ፍልስጤማውያን እስረኞት ተለዋውጣለች።
እስራኤል አሁን ሐማስን ለማጥፋት እንደተነሳች እየገለጸች ሲሆን፤ በአየር ድብደባ ከፍተኛ ጉዳትም እያደረሰች ነው።
አዲስ የእስረኞች ልውውጥ ከባድ እና አወዛጋቢ ይሆናል።
በጋዛ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የፍልስጤማውያን በእስራኤል ላይ ያላቸው ቁጣም እየተባባሰ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሐጊ ሐዳስ የቀድሞ የእስራኤል ኮማንደር እና የሞሳድ የስለላ ኃላፊ ነው። ጊላድ ሻሊት የተባለውን ወታደር ከሐማስ በማስለቀቅ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
የእስረኛ ልውውጥ ፖለቲካዊ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።
እስራኤል በሐማስ ላይ ክፉኛ በተቆጣችበት በዚህ ጊዜ ይህን ማድረግ “የማይሆን ነው” ይላል።
ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አወዛጋቢው የወታደሩ ጊላድ ሻሊት ልውውጥ ቀድሞ ሊሆን ይችል የነበረ ነገር እንደሆነ እና በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ልውውጥ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ድርድር እንዳስፈለጋቸው ይናገራል።
“አሁን ግን ልውውጡ በፍልስጤማውያን እስረኞች አይሆንም። በሌላ መንገድ ነው ልውውጡ” ይላል።
ታጋቾቹ ያሉበት ቦታ ከታወቀ እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ የማካሄድ አማራጭ ልትወስድ እንደምትችል ይገልጻል።
ሌላው የእስራኤል አማራጭ ክፍያ መፈጸም ነው። ወይም የሐማስ አመራሮች ከጋዛ አምልጠው ኳታር እንዲገቡ መፍቀድ።
“አብዛኞቹ በሐማስ እጅ እንደሆኑ አምናለሁ። ያልሆኑም ብዙ አሉ። እስራኤል ታጋቾቹ ያሉበትን ለማወቅ የተቻላትን እያደረገች እንደሆነ አምናለሁ” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
እስራኤል ወታደራዊ አማራጭ ልትጠቀም እንደምትችል ይናገራል።
“በጋዛ ሙሉ ጦርነት ቢከፈት እንኳን እስራኤል ታጋቾችን ለማስለቀቅ መደራደሯ አይቀርም። እስከ መጨረሻው ሰከንድ መፍትሄ ለመፈለግ ይሞከራል” ይላል።
ከ2014 (እአአ) ጀምሮ በሐማስ ሥር ያሉት እስራኤላውያን “አልታገቱም። ወደ ጋዛ ነው የሄዱት። በሥነ ልቦና አልተዘጋጁም” ሲልም አክሏል።
ሐማስ እንደሚለው፣ አቨራ መንግሥቱ እና ሒሻም አል-ሳይድ ወታደሮች ናቸው። የእስራኤል አመራሮች ሰነዶችን ያየው ሂውማን ራይትስ ዋች እንደሚለው ግን ሁለቱም ከወታደራዊ አገልግሎት ውጪ የሆኑ ንጹሃን ዜጎች ናቸው።
ጥላ ፈንታ አቨራን ለማስመለስ የሚደረገው ንቅናቄ መሪ ናት። እስራኤል ጉዳዩን ችላ እንዳለች ይሰማታል።
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ትኩረታቸው ጋዛ ላይ መሆኑ ለጉዳያቸው መጠናከር እንደሚረዳ ታምናለች።
“አቨራ መንግሥቱ የተሻለ ዕድል የሚኖረው አሁን ነው ብዬ አምናለሁ። ይሄን ስል በሐዝነ ነው” ብላለች ለቢቢሲ።
“አሁንም ከድንጋጤው አልወጣንም። 1400 እስራኤላውያን በሐማስ ጥቃት ከተገዱ በኋላ ሁላችንም እስራኤላውያን እንደደነገጥን ነው።”
እስራኤል አቨራ እና ሒሻምን ለዓመታት ማስመለስ አለመቻሏ እንደሚያሳዝናቸው ጥላ ትናገራለች።
“ወታደሮች አይደሉም። ሁለቱም ታመዋል። የአእምሮ ሕመም አለባቸው። ሐማስ ሰብአዊነትን ጥሶ ነው የያዛቸው” ትላለች።
የአቨራ እና ሒሻም ጉዳይ ምንም መሻሻል አለማሳየቱ የእስራኤል ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያውያን-አይሁዶች እንዲሁም የቦዴያን አረቦች ያለውን መድልዎ ማሳያ ነው ትላለች።
“አቨራ ማኅበረሰቡ ብዙም የማይወደው ሰው ነው። ለዚህ ምክንያቱ የቆዳ ቀለሙ፣ የአእምሮ ታማሚ መሆኑ እና በአሽኬሎን የድሃ ሰፈር ማደጉ ነው” ስትል ታስረዳለች።
“ይሄ ሁሉ ተደማምሮ በማኅበረሰቡ የማይፈለግ አደረገው። ቆዳው ትንሽ ነጣ ቢል ወይም ጥሩ አካባቢ ቢወለድ ነገሮች የተለዩ ይሆኑ ነበር። ስለ አገሬ ክፉ የምናገርበት ጊዜ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ግን እውነታው መነገር አለበት።”
የቦዴያን አረብ ተወላጅ መሆኑም ሌላ የመድልዎ ሰለባ መሆን ምክንያት ነው። ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ብዙ ማድረግ እንደነበረባቸው ታምናለች።

የፎቶው ባለመብት, YOAV LEMMER/AFP VIA GETTY IMAGES
ጁማ አቡ ጋኒማ ወደ ጋዛ የተሻገረው እአአ በ2016 እንደሆነ ይታመናል። አሁንም ያለበት አይታወቅም። ቦዴያን አረብ ሲሆን ማረጋገጫ ባይኖርም በሐማስ እጅ እንዳለ ይገመታል።
ወደ ጋዛ በሕገ ወጥ መንገድ ከመግባታቸው በፊት አቨራ እና ሒሻም በተደጋጋሚ ጠፍተዋል። የአእምሮ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደነበረም የሂውማን ራይተስ ዋች ሪፖርት ይጠቁማል።
ከወራት በፊት ሐማስ መቼ እንደተቀረጸ ያልታወቀ ተንቀሳቃሽ ምሥል ለቋል።
አንድ ሰው በሂብሩ “የታገትኩት አቨራ መንግሥቱ ነኝ። ከጓደኞቼ ጋር በእገታ ለምን ያህል ጊዜ ነው የምቆየው” ሲል ይሰማል።
የአቨራ ቤተሰቦች በተንቀሳቃሽ ምሥሉ የሚታየው አቨራ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
ኔታንያሁ ለአቨራ እናት አጉርነሽ እንደነገሯቸው ልጃቸው አቨራ በሕይወት እንዳለ የእስራኤል መንግሥት አረጋግጧል።
“እስራኤል አቨራ መንግሥቱን እንዲሁም ሌሎችም የታገቱ እና የጠፉ ዜጎችን ሳታስመልስ ጥረት አታቆምም” ብለዋል።
ሰኔ 2022 ላይ ሐማስ በለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምሥል ሒሻም አል-ሳይድ ይታያል። አባቱ ሻባን አል-ሳይድ በተንቀሳቃሽ ምሥሉ የሚታየው ሒሻም እንደሆነ አረጋግጠዋል።
ጤናው እክል የገጠመው ሒሻም ብቻ እንደሆነ ሐማስ ቢገልጽም፣ ከዚያ የዘለለ መረጃ አልሰጠም።
ከእስራኤላዊ መታወቂያው ጋር በመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ [ቬንትሌተር] እየታገዘ ሲተነፍስ ይታያል።
የሞተው ወታደር ሐዳር ጎልዲን ወንድም ቱዙር ጎልዲን እንደሚለው የወንድሙ አስክሬን አሁንም ጋዛ ነው።
እስራኤል የሐማስን እገታ ለማቆም ግልጽ አሠራር እንድትዘረጋ ይጠይቃል።
“እገታ የሚያነጣጥረው ቤተሰቦች ላይ ነው። ማኅበረሰብን ይሰነጥቃል። ይሄን የደኅንነት ቀውስ እየለመድነው መጥተናል። የሚታገቱ እና የሚጠፉ ሰዎች መረሳትን እየለመድነው መጥተናል” ሲል ለእስራኤሉ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን አርትዝ ሼቫ ተናግሯል።
“ውጊያ ይካሄዳል ከዚያ ዝምታ ይሰፍናል። ይሄ አዙሪት ይቀጥላል” ሲልም አክሏል።
በሐማስ የታገቱ ሰዎችን ማስለቀቅ ቀላል አይመስልም። አወዛጋቢም ነው።
ሐጊ ሐዳስ ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ ጥሩም መጥፎም የሆኑ ተቃራኒ አማራጮች አሉ።












