የፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ሞት በኢራን ውስጥ ምን ሊያስከትል ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢራን ፕሬዝዳንቷ ኢብራሂም ራኢሲ በሄሊኮፕተር አደጋ መሞታቸውን አረጋግጣ ለአምስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን አውጃለች።
ራኢሲ እሑድ ዕለት በሄሊኮፕተር እየተጓዙ ሳለ ባጋጠማቸው ጥቅጥቅ ደመና እና ዝናብ ምክንያት የአዘርባይጃን ድንበር አካባቢ ነው ለህልፈት የበቁበት አደጋ ያጋጠማቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሆሴን አሚር-አብዶላሂያንን ጨምሮ ሄሊኮፕተሯ ውስጥ የነበሩ ሁሉም ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱን የሚተካ ሰው በሚቀጥሉት 50 ቀናት ውስጥ እንደሚመረጥ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ እስከዚያው ድረስ ግን ምክትላቸው ሞሐመድ ሞኽቤር ራኢሲን ተክተው ይሠራሉ።
ሟቹ የ63 ዓመቱ ራኢሲ የሚቀጥለውን የኢራን የበላይ መሪ ለመወሰን የሚያስችል ተፅዕኖ ፈጣሪ ድምፅ እንዳላቸው ይታመን ነበር።
የሄሊኮፕተር አደጋው እንዴት ተከሰተ?
የሄሊኮፕተር አደጋው በምን ምክንያት እንደተከሰተ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ነገር ግን የኢራን የአየር ትራንስፖርት ደኅንነት አስተማማኝ አይደለም ይላል የቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያ ሲያቫሽ አርዳላን።
ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ በተደጋጋሚ የጣለችው ማዕቀብ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ከኢራን ጋር የሚደረግን ንግድ መከልከሏ የአየር ትራንስፖርቱን ጎድቶታል።
ፕሬዝዳንት ራኢሲ፤ ቤል 212 በተሰኘችውን ሄሊኮፕተር ተሳፍረው ሲጓዙ እንደነበሩ የኢራን መንግሥት የዜና ወኪሎች ዘግበዋል። ይህ ሞዴል አሜሪካ ውስጥ የተመረተ ሲሆን፣ ከ1979 የኢራን አብዮት በኋላ ወደ ቴህራን ሊገባ አይችልም።
መከላከያ እና ትራንስፖርት ሚኒስትሮች እንዲሁም የኢራን የምድር እና አየር ኃይል አዛዦች በአውሮፕላን እና በሄሊኮፕተር አደጋ ሲሞቱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
አንዳንድ ለዘብተኛ አሊያም ለውጥ የሚሹ የኢራን ፖለቲከኞች ኢራንን በሚመሩበት ወቅት ከምዕራባውያን ጋር ስምምነት በመድረስ የአገሪቱን የአየር ጉዞ ለማሻሻል ሞክረዋል። ይህን ማድረግ ያሰቡት ኢራን የኑክሌር ግንባታዋን በመግታት የተጣለባትን ማዕቀብ እንዲነሳ በማድረግ ነው።

አሁን ምን ሊሆን ይችላል?
የኢራን አስላማዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት፤ አንድ ፕሬዝዳንት በሕመም፣ በሞት አሊያም በሹም-ሽር ምክንያት ሥራውን መከወን ባቃተው ጊዜ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በግልፅ አስቀምጧል ይላል የቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያው ባሕማን ካልባሲ።
ይህ ሲሆን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተክተው ይሠራሉ። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሞሐመድ ሞኽቤር የአገር ውስጥ እና የውጭ ጉዳይ ሥራዎችን ከፓርላማው አፈ-ጉባዔዎች እንዲሁም ከሕግ አስፈፃሚው ጋር በመሆን ይሠራሉ። ነገር ግን በ50 ቀናት ውስጥ አዲስ ፕሬዝዳንት መመረጥ አለበት።
እርግጥ ነው ይህ የሚሆነው የበላይ መሪው ፈቃድ ሲሰጡ ነው። የበላይ መሪው በኢራን ጉዳይ የመጨረሻው ወሳኝ ሰው ናቸው።
የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ መሞታቸውን ማረጋገጡን ተከትሎ የኢራን መንግሥት ምርጫ ያካሂዳል። ይህ ምርጫ ባለፈው ጊዜ ከነበረው ምርጫ ያነሰ ትኩረት እንደሚኖረው ይታመናል።
ኢራን ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የራኢሲ ተቀናቃኝ የነበሩ ዕጩዎች ከመወዳደር እንዲታገዱ ተደርገዋል። ይህን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ድምፅ አንሰጥም ቢሉም፣ ራኢሲ ያለማንም ተቀናቃኝ መንበሩን ጨብጠዋል።
ሞሐመድ ሞኽቤር ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞኽቤር አድራጊ ፈጣሪ በሆኑት የኢራን የበላይ መሪ የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
ሞሐመድ ሞኽቤር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት በ2021 ራኢሲ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ነው።
የ68 ዓመቱ ጉምቱ ዲፕሎማት የበላይ መሪው አሊ ኻሜኒ ቀኝ እጅ ናቸው። በሚቀጥሉት 50 ቀናት አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ የተዋቀረው ሦስት ሰዎችን የያዘ ኮሚቴ አባል ሆነው ያገለግላሉ።
ሞኽቤር ባለፈው ጥቅምት ወደ ሩሲያ አቅንተው ሞስኮን ከጎበኙ በኋላ ኢራን ከመሬት ወደ አየር የሚወነጨፉ ሚሳዔሎች እና ድሮኖችን ለሩሲያ ለማቅረብ ተስማምተው መጥተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2012 የአውሮፓ ኅብረት “የኑክሌር ወይም የባለስቲክ ሚሳዔል እንቅስቃሴው አሉበት” ያላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር አውጥቶ ማዕቀብ ሲጥል የእሳቸው ስም ተካቶ ነበር። ሞኽቤር ከሁለት ዓመት በኋላ ከዚህ ዝርዝር ተሰርዘዋል።
ከዚህ ቀደም ሴታድ የተባለው የበላይ መሪውን ኻሜኒ ትዕዛዝን የሚያስፈጽም ድርጅት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። ድርጅቱ ከበላይ መሪው ጋር ግንኙነት ያለው የኢንቨስትመንት ፈንድ ነው።
በ2013 የአሜሪካ ግምጃ ቤት ይህን ፈንድ ጨምሮ ሌሎች 37 ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል። ምክትል ፕሬዝዳንት በአሜሪካ መንግሥት የግል ማዕቀብም ተጥሎባቸዋል።
ኢራንን የሚመራት ማነው?

የኢራኑ ኃያሉ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ናቸው። ኻሜኒ ከአውሮፓውያኑ 1989 ጀምሮ የኢራን የበላይ መሪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
ኻሜኒ፤ የአገር መሪ እና የጦር ሠራዊቱ ጠቅላይ አዛዥ ናቸው። አልፎም የብሔራዊው ፖሊስ እና የሥነ-ምግባር ፖሊሱንም ይቆጣጠራሉ።
አያቶላህ ኻሜኒ የአገር ውስጥ ደኅንነት ፖሊስ የሆነው የእስላማዊው አብዮታዊ ዘብ የበላይ ጠባቂም ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ባሲጅ የተሰኘው ወዶ ዘማች ሚሊሻም አዛዥ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ የሚገኝ በድምፅ የሚመረጥ ከፍተኛው ባለሥልጣን ሲሆን፣ ከበላይ መሪው ቀጥሎ ሁለተኛው ተደርጎ ይቆጠራል።
በኢራን ፕሬዝዳንቱ የዕለት ከዕለት የመንግሥትን ተግባርን የሚፈፅም እና በአገር ውስጥ ፖሊሲ እና በውጭ ጉዳይ ላይ ተፅዕኖ ያለው ነው። ነገር ግን በተለይ በፀጥታ እና በደኅንነት ጉዳዮች ላይ የፕሬዝዳንቱ ሚና የተገደበ የሚባል ነው።
የፕሬዝዳንቱ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ብሔራዊውን ፖሊስ ቢያስተዳድርም የፖሊስ አዛዥ የሚመረጠው በበላይ መሪው ሲሆን፣ ተጠሪነቱም ለኻሜኒ ነው።
የአብዮታዊው ዘብ እና የባሲጅ አዛዦችም ተጠሪነታቸው ለበላይ መሪው ነው።
ፕሬዝዳንቱ ያላቸው ጉልበት በፓርላማው ሊመረመር ይችላል። ፓርላማው አዳዲስ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን አለው።
የበላይ መሪው የቅርብ ሰዎችን የያዘው የበላይ ምክር ቤት አዳዲስ ሕጎችን የማፅደቅ እና የመሻር ሥልጣን ያለው ነው።
በሚቀጥለው ምርጫ ምን እንጠብቅ?
ሟቹ ኢብራሂም ራኢሲ ተቺዎች “የተቀነባበረ” ያሉትን ምርጫ አሸንፈው ነው ወደ ሥልጣን የመጡት ይላል የቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያው ፓርሀም ጎባዲ።
ዕጩዎችን የሚመረምረው የበላይ ምክር ቤት ተቀናቃኝ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ዕጩዎች ከምርጫው ውጭ አድርጓል። ይህን ተከትሎ በኢራን ታሪክ እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ሕዝብ ነው ወጥቶ ለፓርላማ እና ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዕጩዎች ድምፁን የሰጠው።
በሚቀጥሉት 50 ቀናት አዲስ ፕሬዝዳንት የሚያስፈልጋት ኢራን እንዳለፈው ዓይነት ምርጫ ልትደግም ትችላለች የሚል ግምት አለ። ለበላይ መሪው አያቶላህ ኻሜኒ ቅርብ እና ታማኝ የሆነ ሰው ምርጫውን ሊረታ እንደሚችል ብዙዎች ቀድመው ይተነብያሉ።
በርካቶች እንደሚያምኑት የ85 ዓመቱ ጠቅላይ አዛዥ ከሕልፈተ-ሕይወታቸው በኋላ ግርግር የሌለበት የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ከአሁን የኢራንን የፖለቲካ ምኅዋር እየዘወሩት ነው።
ኢብራሂም ራኢሲ ማን ነበሩ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ወዳጆቻቸው እንደሚሉት ራኢሲ “ተሰዉ” እንጂ አልሞቱም። አገራቸውን እያገለገሉ እያሉ፤ የደሆች እና ተመልካች የሌላቸው ሰዎች ፕሬዝዳንት ሆነው ነው ያለፉት ይላሉ።
በ2021 የኢራን ሕግ አስፈፃሚ ኃላፊ እና ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆነው ሲቀርቡ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ ሙስናን እንደሚታገሉ፣ የኑሮ ውድነትን እንደሚገቱ እንዲሁም ለደሀ ኢራናዊያን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤቶችን እንደሚሠሩ ቃል ገብተው እንደነበር የቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያው ጂያር ጎል ያስታውሳል።
በርካቶች የአስፈፃሚው ክንፍ አስተዳዳሪ ሆነው ይህን ባለማድረጋቸው ትችት ይሰነዝሩባቸው ነበር። እዋጋዋለሁ ያሉትን ሙስናም ባለመታገላቸው ነቀፌታ ገጥሟቸዋል።
ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሾሙ ወደ ተለያዩ የኢራን ክፍላተ አገራት ተጉዘው ችግሮችን እንደሚፈቱ ቃል ሲገቡም ነበር።
መንበሩን ከተረከቡ 1000 ቀናት ያሳለፉት ሟቹ ፕሬዝዳንት ዕጩ ሳሉ የገቡትን ቃል አለመፈፀማቸው በተግባር ታይቷል።
ኢራናውያን ከዛሬ 3 ዓመታት በፊት ከነበሩበት ድህነት የዘቀጠ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት። የኢራን መገበያያ ገንዘብ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነፃፀር የነበረው ዋጋ ወርዷል። የዋጋ ንረት በኢራን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ አሻቅቧል።
ቃል እንደገቡት ለደሀ ኢራናውያን መኖሪያ ቤት ሳይገነቡ ነው የሞቱት።
የፖለቲካ ተንታኞች “ልወደድ ባይ ፕሬዝዳንት ናቸው” ሲሉ ይተቿቸዋል። ራኢሲ ወደ ፕሬዝዳንቱ መንበር የመጡት ለበላይ መሪው እጅግ ታዛዥ እና ታማኝ ስለሆኑ ነው ይባልላቸዋል።
በ1980ዎቹ ዐቃቤ ሕግ ሆነው እያገለገሉ ሳለ 5 ሺህ ገደማ የፖለቲካ እስረኞች እንዲገደሉ አስተዋፅዖ አድርገዋል ተብለውም ይወቀሳሉ።
አብዛኞቹ የሟቾች ቤተሰቦች የተደበላለቀ ስሜት ላይ ናቸው። ፕሬዝዳንቱን ባይወዷቸውም በሕይወት ቆይተው ለፈፀሙት ወንጀል ፍርድ ሲቀበሉ ቢያዩ ደግሞ ደስ ይሰኙ ነበር።












