በሄሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው የኢራኑ ፕሬዝዳንት የመሪነት ጉዞ

ኢብራሂም ራኢሲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሄሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ከኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ኾሜኒ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራቸው ጠንካራ ሃይማኖተኛ ነበሩ።

ፕሬዚዳንቱ በአውሮፓውያኑ 2021 ወደ ሥልጣን መምጣታቸው በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ግዛቶች ላይ የወግ አጥባቂዎቹ የበላይነት መስፈንን ያረጋገጠ ነው ተብሏል።

ምርጫውን ተከትሎ የ63 ዓመቱ ኢብራሂም የቀድሞ የፍትህ ቢሮ አለቃ ሐሰን ሩሃኒን ተክተው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለመሆን በቁ።

ምርጫው በርካታ ለዘብተኛ እና ለውጥ አራማጅ ዕጩዎች የታገዱበት ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኞቹ ኢራናውያን መራጮች ያልተሳተፉበት ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ኢራን በበርካታ ፈተናዎች እየተፈነች ባለበት ወቅት ነበር ሥልጣን የተረከቡት።

የምጣኔ ሐብት ተግዳሮቶች፣ የቀጠናው ውጥረቶች እየተባባሱ እንዲሁም ከዓለም ኃያላን አገራት ጋር በኑክሌር ስምምነት ዙሪያ ውዝግብ በቀጠለበት ሁኔታም ነበር ቃለ መሐላ የፈጸሙት።

ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ከአንድ ዓመት በኋላ በመላው ኢራን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ተቀጣጠለ። እንዲሁም በኢራን እገዛ ይደረግለታል የሚባለው የፍልስጤሙ ሐማስ በጋዛ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቱ እና ኢራን ከእስራኤል ጋር የጀመረችው የእጅ አዙር ግጭት ወደ ይፋዎ ፍጥጫ መሸጋገሩ በሥልጣን ዘመናቸው ጎልተው ወጥተዋል።

በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በነበረው የፖለቲካ እስረኞች ላይ በተፈጸመው የጅምላ ግድያ ውስጥ ነበራቸው ስለሚባለው ሚና ምርመራ እንዲደረግ ከበርካታ ኢራናውያን እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥያቄ እየቀረበባቸው ነበር።

ኢብራሂም ራኢሲ በአውሮፓውያኑ 1960 በኢራን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ እና የአገሪቱ የሺዓ ሙስሊሞች ቅዱስ ተብላ በምትታወቀው ማሽሃድ ነው የተወለዱት።

የሃይማኖት አባት የነበሩት አባታቸው የአምስት ዓመት ልጅ እያሉ ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

በሺዓ ባህል መሠረት የነብዩ መሐመድ ዘር መሆናቸውን የሚገልጽ ጥቁር ጥምጣም የሚለብሱት ራኢሲ፣ የአባታቸውን ፈለግ በመከተል በቅድስቲቷ ቆም ከተማ በ15 ዓመታቸው ሃይማኖታዊ ትምህርት መከታተል ጀመሩ።

ተማሪ እያሉ በምዕራቡ ዓለም የሚደገፈውን የሻህ መንግሥትን በመቃወም በተደጋጋሚ አደባባይ ወጥተዋል። ሻህ አስተዳደር በአውሮፓውያኑ 1979 በአያቶላ ሩሆላህ ኾሜኒ በሚመራው እስላማዊ አብዮት ከሥልጣን ተወገደ።

ራኢሲ ከአብዮቱ በኋላ የፍትህ አካላትን ተቀላቅለው በተለያዩ ከተሞች ዐቃቤ ሕግ ሆነው አገልግለዋል። በ1981 የኢራን ፕሬዝዳንት በሆኑት በአያቶላ አሊ ኾሜኒም ሥልጠና ወስደዋል።

ኢብራሂም ራይሲ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ከኢራን ‘የሞት ኮሚቴ’ ጋር የነበራቸው ግንኙነት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ራይሲ በ25 ዓመታቸው ነው ቴህራን ውስጥ ምክትል ዐቃቤ ሕግ ለመሆን የበቁት።

በዚህ ወቅት ነበር በ1988 በተቋቋመው የምሥጢራዊ እና በኋላም “የሞት ኮሚቴ” ለመባል በበቃው ፍርድ ቤት የፍርድ ብያኔ ካስተላለፉት መካከል አራት ዳኞች አንዱ ናቸው።

ፍርድ ቤቱ በፖለቲካዊ ተሳትፏቸው በእስር ላይ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን “እንደገና ብያኔ ያስተላለፈባቸው” አብዛኞቹ የኢራን ሕዝቦች ሙጃሂዲን ድርጅት (ፒኤምኦአይ) በመባል የሚታወቀው የግራ ዘመም ተቃዋሚ ቡድኑ የሙጃህዲን-ኢ ካልክ (ሜክ) አባላት ነበሩ።

በፍርድ ቤቱ የሞት የተፈረደባቸው ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር በውል አይታወቅም።

ሆኖም ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ወንዶች እና ሴቶች ተገድለዋል ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይገልጻሉ። ግለሰቦቹም ምልክት በሌለው የጅምላ መቃብር የተቀበሩ ሲሆን፣ ይህም በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደሆነ ይቆጠራል ተብሏል።

የእስላማዊ ሪፐብሊኳ መሪዎችም ግድያው መፈጸሙን ባይክዱም ነገር ግን ዝርዝር ጉዳዮችን አይጠቅሱም።

ራኢሲ በዚህ ሞት ፍርድ ውስጥ ሚና እንዳልነበራቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል። በአያቶላህ ኾሜኒ በፋትዋ ወይም ሃይማኖታዊ ውሳኔ ምክንያት መጽደቁን ግን አይክዱም።

ራኢሲን ጨምሮ ሌሎች የፍትህ አካላት እና በወቅቱ ምክትል መሪ የነበሩት አያቶላ ሆሴን አሊ ሞንታዘሪ መካከል በ1988 በተደረገ ስብሰባ ወቅት የተቀረጸ ድምጽ በአውሮፓውያኑ 2016 ሾልኮ ወጥቷል።

ሞንታዘሪ ግድያውን “በኢስላማዊ ሪፐብሊኳ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ወንጀል” በማለት ሲገልጹት ተደምጧል።

ከአንድ ዓመት በኋላ ሞንታዘሪ የአያቶላህ ኾሜኒ ተተኪ ከሚያደርጋቸው ቦታቸው ተነሱ። አያቶላህ ደግሞ የኻሜኒ ህልፈተ ሕይወትን ተከትሎ ጠቅላይ መሪ ሆኑ።

ስለጅምላ ግድያው ጉዳይ እአአ በ2021 ከሪፖርተሮች ለቀረበላቸው ጥያቄ “ዳኛ እና ዐቃቤ ሕግ የሕዝቡን ደኅንነት ከጠበቁ ሊመሰገኑ ይገባል... አሁን እስከያዝኩት ሥልጣን ድረስ ለሁሉም የሰብአዊ መብት ጥበቃ በማድረጌ ኩራት ይሰማኛል” ሲሉ መልሰዋል።

የተገደሉ ሰዎች የታሰበቡት ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የማይመስሉት ፕሬዝዳንታዊ ምኞቶች

ራኢሲ እአአ በ2017 ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ በመግለጽ ብዙዎችን አስገርመዋል።

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 57 በመቶ ድምጽ በማግኘት የሃይማኖት መሪ የሆኑት ሩሃኒ ለሁለተኛ ጊዜ በከፍተኛ ድምጽ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።

ራሳቸውን የፀረ ሙስና ታጋይ አድርገው ያቀረቡት በ38 በመቶ ድምጽ ሁለተኛ ሆኑ። በወቅቱ ምክትል ዐቃቤ ሕግ ሆነው ሙስናን ለመዋጋት ብዙም አልሠሩም በሚል በሩሃኒ ተተችተውም ነበር።

ይህ ግን ስማቸውን አላጎደፈውም። በ2019 በአያቶላህ ኻሜኒ የአገሪቱ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ ከመሆንም አላገዳቸውም።

በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ ቀጣዩን የአገሪቱን ሃይማኖታዊ መሪ የመምረጥ ኃላፊነት ያለው እና 88 አባላት ያሉት የሊቃውንት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ለመመረጥ በቁ።

ራኢሲ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ እያሉ የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ በሞት የሚቀጡ ሰዎችን እና በአደንዛዥ ዕጽ ምክንያት ሞት የሚፈረድባቸው ሰዎችን ቁጥር እንዲቀንስ አድርገዋል። ከዚያም በኋላ ቢሆን ኢራን ከቻይና በቀር ከየትኛውም በሞት ቅጣት የሚበልጣት አልነበረም።

የፍትህ አካላትም ከደኅንነት መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር ተቃውሞዎችን ለመግታት እና ሁለት ዜግነት ያላቸው ወይም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው በርካታ ኢራናውያንን ሰላይ ናቸው በሚልም ክስ መመሥረታቸውን ቀጠሉ።

የያኔው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ምክንያት ራኢሲ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።

እአአ በ2009 ከተካሄደው አጨቃጫቂ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በኋላ የተቃዋሚውን ግሪን ሙቭመንት ለማስቆም በተደረገው ግድያ እጃቸው አለበት በሚል ተከሰዋል።

ራይሲ ራሳቸውን እንደጸረ ሙስና ታጋይ አድርገው አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ራኢሲ ለ2021 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩ መሆናቸውን ሲያሳውቁ “በአገሪቱ በሥራ አስፈፃሚው ላይ ለውጦችን ለማድረግ እና ድህነትን፣ ሙስናን እና መድልዎን እዋጋለሁ” ብለው ነበር።

ታዋቂ ለዘብተኛ እና የለዉጥ አራማጅ ዕጩዎች ከሂደቱ መሰናበታቸው ምርጫ ላይ የራሱን ተጽዕኖ ፈጠረ። ተቃዋሚዎች እና አንዳንድ የለውጥ አራማጆች መራጮች በምርጫው እንዳይሳተፉ ጠየቁ። ራኢሲ ምንም ዓይነት ከባድ ፉክክር እንዳይገጥመው ለማድረግ የተቀነባበረ ነው ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በአንደኛው ዙር 62 በመቶ ድምጽ በማግኘቱት ትልቅ ድል አስመዝግበዋል። ይሁን እንጂ የመራጮች ቁጥር ከ49 በመቶ በታች ነበር። ይህም ከ1979ኙ አብዮት ወዲህ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በጣም ዝቅተኛው ቁጥር ነው።

ራኢሲ በነሐሴ ወር የአራት ዓመት የሥራ ዘመናቸውን ሲጀምሩ “የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት፤ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል እና ማንኛውንም ዲፕሎማሲያዊ ዕቅድ በመደገፍ” አገሪቱ የተጣለባትን ማዕቀብ እንዲነሳ ለማድረግ እንደሚሠሩ ቃል ገብተው ነበር።

እአአ በ2015 የኢራንን የኑክሌር ግንባታን የሚገድብ ስምምነትን እንደገና ለማደስ እና በ2018 በአሜሪካ የተጣለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለማስነሳት ያለመ ነበር።

ራኢሲ ከኢራን ጎረቤት አገሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻልም ቃል ገብተው ነበር። በተመሳሳይም በአካባቢው ያላቸውን እንቅስቃሴ “የማረጋጋት ኃይል” በማለት ተከላክለዋል።

ራኢሲ በድርድሩ ላይ ጠንካራ አቋም ቢይዙም የኑክሌር ስምምነትን ለማደስ ከአሜሪካ ጋር የተደረገው ስምምነት እአአ ነሐሴ 2022 ተዘግቷል። ይሁን እንጂ ጥረቶቹ በኢራን ውስጥ በተፈጠሩ ክስተቶች ምክንያት ተስተጓጉለዋል።

ራይሲ ፕሬዝዳንት ሆነው ሳይቆዩ ኢራን በተቃውሞ ተናጠች

የፎቶው ባለመብት, EPA

በፀረ መንግሥት ተቃውሞ መናጥ

መስከረም አገሪቱ ሃይማኖታዊ አስተዳደር እንዲያበቃ በሚጠይቁ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተናጠች።

በቴህራን ሂጃብዋን “ያለአግባብ” ለብሳለች በሚል ክስ የተመሠረተባት ወጣቷ ማህሳ አሚኒ በእስር ላይ እያለች ሕይወቷ ማለፉ “ሴት፣ ሕይወት፣ ነፃነት” የሚለው ንቅናቄ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነ።

ባለሥልጣናት ምንም የተፈጸመባት በደል የለም ብለው ቢክዱም፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪ ቡድን ግን “ለሞት ላበቃት አካላዊ ጥቃት ተዳርጋለች” ብሏል።

ራኢሲ በአገሪቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት “በቆራጥነት ለመፍታት” ቃል ገቡ። ባለሥልጣናትም ተቃውሞውን በኃይል አፈኑት።

ባለሥልጣናት የሟቾችን ቁጥር ይፋ ባያደርጉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ታማኝ መረጃዎችን ጠቅሶ እስከ 551 የሚደርሱ ተቃዋሚዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን አስታውቋል። አብዛኞቹ በጥይት የተገደሉ ናቸውም ተብሏል። መንግሥት 75 የፀጥታ አባላት ተገድለዋል ብሏል።

ሌሎች ከ20 ሺህ በላይ ተቃዋሚዎች መታሰራቸው እና ዘጠኝ ወንዶች መገደላቸው ተነግሯል።

ሕዝባዊ ተቃውሞው ጋብ ቢልም በሃይማኖት አባቶች እና በሂጃብ ሕጎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ መኖሩ አሁንም ድረስ ቀጥሏል።

በርካታ ሴቶች እና ልጃገረዶች በድፍረት ፀጉራቸውን በአደባባይ መሸፈናቸውን አቆሙ። ይህንን ድርጊት ለማስቆም የኢራን ፓርላማ እና ራኢሲ አዲስ ሕግ ለማውጣት ተገደዋል።

ኢራን እና አካባቢያዊ ውጥረት

እአአ በ2023 ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ካቋረጡ ከሰባት ዓመታት በኋላ መንግሥታቸው ከአካባቢው ሌላኛዋ ኃያል አገር ሳዑዲ አረቢያ ጋር መቀራረብ ለመጀመር የራኢሲ መንግሥት ተስማማ።

በመስከረም ወር ሐማስ በደቡብ እስራኤል ያልተገመተ ድንበር ዘለል ጥቃት መፈጸሙን ተለትሎ እስራኤል በጋዛ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቷ የቀጣናውን ውጥረት ጨመረው።

ይህንን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚንቀሳቀሱ የኢራን አጋር ታጠቂ ቡድኖች እና ተላላኪዎች (በሊባኖስ ሄዝቦላህ፤ በየመን ሁቲዎች እና በኢራቅ እና ሶሪያ ያሉ ታጣቂዎች) ለፍልስጤማውያን ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በእስራኤል ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ አጠናከሩ።

ሚያዝያ ላይ አካባቢያዊው ውጥረት ኢራን በእስራኤል ላይ የመጀመሪያውን ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ወደ ጦርነት ያድጋል ተብሎ ስጋት ፈጥሮ ነበር።

በሶሪያ የሚገኘው የኢራን ቆንስላ ላይ ለደረሰው አሰቃቂ ጥቃት አጸፋዊ ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች ወደ እስራኤል እንዲተኮስ መወሰኑን ራኢሲ ደግፈዋል።

ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ግን በእስራኤል፣ በምዕራባውያን እና በአረብ አገራት ተመትተው እንዲከሽፉ ተደርገዋል። በደቡባዊ እስራኤል የሚገኝ የአየር ኃይል ብቻ የተወሰነ ጉዳት ደርሶበታል።

ራኢሲ የኢራን ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት "የአገራችንን ቆራጥነት" አሳይቷል አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እስራኤል አጸፋዊ ምላሽ እንዳትሰጥ ከምዕራባዊያን የቀረበላትን ጥሪ ወደ ጎን ብላ የኢራን የአየር ኃይል ሰፈር ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽማለች።

ራኢሲ ጥቃቱን መጠን ዝቅ አድርገው አቀረቡ። የኢራን ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት “የአገራችንን ቆራጥነት” አሳይቷል ሲሉ ተናግረው ነበር።

የሄሊኮፕተር አደጋ ከማጋጠሙ በፊት እሑድ ዕለት በሰሜን ምዕራብ ኢራን የተሠሩ ግድቦችን በመረቁበት ወቅት አገራቸው ለፍልስጤማውያን የምታደርገውን ድጋፍ አፅንዖት ሰጥተው “ፍልስጤም የሙስሊሙ ዓለም የመጀመሪያዋ አጀንዳ ናት” ሲሉ ራይሲ ተናግረው ነበር።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚር-አብዶላሂን ጨምሮ ከበርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ከጉብኝቱ ሲመለሱ ሄሊኮፕተራቸው በተራራማ አካባቢዎች ላይ አደጋ እንዳጋጠመው የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ጥቅጥቅ ያለው ጭጋግ እና የነበረው ከባድ ዝናብ የነፍስ አድን ጥረቶችን አደናቅፏል። ሰኞ ጠዋት ግን ባለሥልጣናት አደጋው የደረሰበትን ቦታ ማግኘታቸውን እና ራኢሲን ጨምሮ በሄሊኮፕተሯ ውስጥ የነበሩ ሰዎች በሙሉ መሞታቸውን ገልጸዋል።

ባለቤታቸው ጀሚላ ቴህራን በሚገኘው ሻሂድ ብሄሽቲ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከማስተማራቸው እና ሁለት ሴት ልጆች እንደነበሯቸው ከመታወቁ ውጪ ስለ ራኢሲ የግል ሕይወት ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም።