የኢራኑ ፕሬዚዳንት በሄሊኮፕተር አደጋው ህይወታቸው እንዳለፈ ተዘገበ

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ ተሳፍረውባት በነበረው ሄሊኮፕተር በደረሰው አደጋ ህይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ የመንግሥት ሚዲያ አረጋገጠ።

ከሳቸው በተጨማሪ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴይን አሚር አብዶላሂያን እና ሌሎች በርካታ ሰዎች እሁድ፣ ግንቦት 12/ 2016 ዓ.ም በደረሰው የሄሊኮፕተር አደጋ መሞታቸው ተገልጿል።

ከኢራን ፕሬዚዳንት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተጨማሪ በታብሪዝ ከተማ የጁምአ ሰላት ኢማም የሆኑት አያቶላህ መሀመድ አሊ ኢ ሀሺም እና የኢራን ምስራቃቂዊ አዘርባጃን ግዛት አስተዳዳሪ ጄነራል ማሌክ ራህማቲ ህይወታቸው ማለፉን የኢራን የመንግሥት የዜና ወኪል ዘግቧል።

የዜና ወኪሉ የፕሬዚዳንት የጥበቃ ክፍል አዛዥ ሳርዳር ሰይድ መህዲ ሙሳቪ እንዲሁም በርካታ ጥበቃዎች እና ስማቸው ያልተገለጸ የሄሊኮፕተሯ ሰራተኞች ህይወት ማለፉን በዘገባው አካቷል።

መሞታቸው ከመዘገቡ በፊት ሄሊኮፕተሯ በተከሰከሰችበት ስፍራ የህይወት ምልክት እንደሌለ ተገልጾ ነበር።

ሮይተርስም በአደጋው ፕሬዚዳንቱ ሲጓዙባት የነበረችው ሄሊኮፕተር” ሙሉ በሙሉ መቃጠሏን” አንድ የኢራን ባለስልጣንን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

“የፕሬዚዳንት ራይሲ ሄሊኮፕተር በአደጋው ሙሉ በሙሉ ተቃጥላለች። በሚያሳዝን ሁኔታ ሁሉም ተሳፋሪዎች ሳይሞቱ አልቀሩም” ብለዋል ስማቸው ያልተጠቀሰው ባለስልጣን።

ፕሬዚዳንቱን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ሆሴይን አሚር አብዶላሂያንን አሳፍራ የነበረችው ሄሊኮፕተር በትናንትናው ዕለት አደጋ ከገጠማት በኋላ በአደገኛ ሁኔታ ማረፏ ተዘግቦ ነበር።

አደጋው ወደደረሰበት ስፍራ የነፍስ አድን ሰራተኞች እንደተሰማሩ እና ሁኔታው ጥሩ እንዳልሆነ የኢራን የቀይ ጨረቃ ማህበረሰብ ፕሬዚዳንት መናገራቸውን የአገሪቱ ሚዲያ ዘግቦ ነበር።

ፕሬዚዳንቱን አሳፍራ የነበረችው ሄሊኮፕተር በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በከባድ ጭጋግ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥ ከገባች በኋላ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ማረፏ ተዘግቦ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ኢራን ከአዘርባጀን ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ የተገነቡ ሁለት ግድቦችን መርቀው ከከፈቱ በኋላ ወደ ሰሜን ምዕራቧ የአገሪቱ ከተማ ታብሪዝ እያመሩ እንደነበረ የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የፋርስ የዜና ወኪል ዘጋቢ እንዳለው ሄሊኮፕተሩ አርፋበታለች በተባለው ስፍራ ላይ በነበረው የከፋ ጭጋግ ምክንያት የነፍስ ማዳን ፍለጋ ሥራው አስቸጋሪ ሆኖ ነበር።

ፕሬዝዳንቱን አጅበው የነበሩት ሌሎቹ ሁለት ሄሊኮፕተሮች በሰላም ማረፋቸውንም የምክር ቤት አባሉ ገልጸዋል።

በመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ ከኢራኗ ቅዱስ ከተማ ማሻድ በቀረበ ቪዲዮ ላይ ምዕመናኑ ለፕሬዝዳንቱ ጤንነት ጸሎት ሲያደርጉ ነበር።

የ63 ዓመቱ ፕሬዚዳንት አጥባቂ የሚባሉ የሃይማኖት አባት ሲሆኑ የኢራን ታላቂ መሪ አያቶላህ አሊ ሆሚኒ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው። እንዲያውም የ85 አመቱን አያቶላህ ሆሚኒን ሊተኩ ይችላሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸው ነበር።

ፕሬዚዳንቱ በ2021 ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ግዛቶች ላይ የወግ አጥባቂዎቹ የበላይነት መስፈን ያረጋገጠ ነው ተብሏል። ህልፈታቸውን ተከትሎ የኢራን መንግሥት በሰጠው መግለጫ “ያለምንም መስተጓጎል” የመንግሥት ተግባራት እንደሚቀጥል አስታውቋል።