የኢራኑ ፕሬዝዳንት ስለሞቱበት የሄሊኮፕተር አደጋ እስካሁን የምናውቀው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሒም ራኢሲን ጨምሮ ለስምንት ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የሄሊኮፕተር አደጋ የተከሰተው ትናንት እሁድ ነበር።
ሄሊኮፕተሩ የተከሰከሰው በአዘርባጃን ድንበር አቅራቢያ ሲጓዝ እንደነበር የኢራን ባለሥልጣናት ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
እስካሁን ስለ ሄሊኮፕተሩ አደጋ የምናውቃቸው ነጥቦች ቀጣዮቹ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ ለምን በሄሊኮፕተር ተጓዙ?
ፕሬዝዳንቱ ወደ አገሪቱ ሰሜን ምዕራብ የኢራን አካባቢ (የአዘርባጃን ምዕራባዊ ክፍል አቅራቢያ) የተጓዙት ‘ቂዝ ቃላሲ’ የተባለውን ግድብ ለማስመረቅ ነበር።
ይህም ኢራን ከአዘርባጃን ጋር በምትጋራው አራስ ወንዝ ላይ የተገነባ ኃይል ማመንጫ ግድብ ነው።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከአዘርባጃኑ ፕሬዝዳንት ኢልሐም አሊይቭ ጋር ተገናኝተዋል።
ሄሊኮፕተሩ ከመነሳቱ በፊት ኢብራሒም ራኢሲን “በወዳጅነት መሰናበታቸውን” አሊይቭ ተናግረዋል።
ሄሊኮፕተሩ ከግድቡ በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደሚገኘው ታብሪዝ ከተማ እየተጓዘ ነበር።
በታብሪዝ ከተማ ፕሬዝዳንቱ ሁለት የነዳጅ ፕሮጀክቶችን እንዲመርቁ እየተጠበቁ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሄሊኮፕተሩ ውስጥ እነማን ነበሩ?
ፕሬዝዳንቱን አጅበው ስምንት ሰዎች በሄሊኮፕተሩ ውስጥ ነበሩ።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሲን አሚር-አብዶላሂን፣ የምሥራቅ አዘርባጃን ግዛት አገረ ገዢ ማሌክ ራሕማቲ፣ የታብሪዝ ከተማ የአርብ ፀሎት መሪ አያቶላ መሐመድ ዓሊ ሐሺም እንዲሁም በምሥራቅ አዘርባጃን ከፍተኛ የሺዓ እምነት መሪው ዓሊ ካሃሜኒ ተወካይ ይገኙበታል።
የተቀሩት አምስት ሰዎች በሄሊኮፕተሩ የመስተንግዶ እና የበረራ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ እንዲሁም የፕሬዝዳንቱ ጠባቂዎች መሆናቸውን የኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

ሄሊኮፕተሩ የተከሰከሰው የት ነው?
ሄሊኮፕተሩ የተከሰከሰው ተራራማ በሆነ ገጠራማ አካባቢ ነው።
ከተመረቀው ግድብ በ58 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ኡዚ ከተባለ መንደር ደግሞ 2 ኪሎሜትር እንደሚርቅ የኢራን ባለሥልጣናት መግለጫ እና በብሔራዊ ቴሌቭዢን የተላለፈው መረጃ ይጠቁማል።
የኢራን መገናኛ ብዙኃን መጀመሪያ ላይ ዘገባውን ያስተላለፉት ሄሊኮፕተሩ ወደ ታብሪዝ ሲጓዝ በከፍተኛ ጉም እና ዝናብ ምክንያት “ምቹ ባልሆነ ሁኔታ አርፏል” በሚል ነበር።
የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ አሕመድ ቫሂዲ በሰጡት መግለጫ፣ ከፕሬዝዳንቱ ጋር የነበረ የልዑካን ቡድን በሦስት ሄሊኮፕተሮች እየተጓዘ ሳለ ፕሬዝዳንቱ የነበሩበት ሄሊኮፕተር “በአካባቢው በነበረ ጉም እና መጥፎ የአየር ሁኔታ ሳቢያ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ለማረፍ ተገዷል” ብለዋል።
ብዙ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ ስፍራው ቢያመሩም በጉም፣ በበረዶ እና በዝናብ ምክንያት የፍለጋ ሥራው ተስተጓጉሏል።
ሁለቱ ሄሊኮፕተሮች ከ15 እስከ 20 ለሚሆን ደቂቃ ከሦስተኛው ሄሊኮፕተር ጋር ለመገናኘት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
በድንገተኛ ሁኔታ ለማረፍም ተገደዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የከፍተኛ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሞሕሰን መንሱሪ እንዳሉት፣ በፕሬዝዳንቱ አውሮፕላን ውስጥ ከነበሩ ሁለት የበረራ ሠራተኞች ጋር መነጋገር ተችሎ ነበር።
“ሄሊኮፕተሩ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ከእኛ ጋር መነጋገር ችለው ነበር። የአደጋው መጠን ከፍተኛ እንዳልነበር ያሳያል” ብለዋል።
የፍለጋ ሥራው እስከ ምሽት ድረስ ቢቀጥልም ሄሊኮፕተሩን ማግኘት የተቻለው ዛሬ ሰኞ ንጋት አካባቢ ነው።
በአደጋው ቦታ ምን ተገኘ?
የኢራን ቀይ ጨረቃ ኃላፊ ፒርሆሴይን ኮሎቫንድ እንዳሉት፣ ሄሊኮፕተሩ ያለበት ቦታ ከታወቀ በኋላ ወደቦታው ለመድረስ አንድ ሰዓት ወስዷል።
አደጋው የደረሰበት ቦታ ከፍታው ወደ 2,200 ሜትር እንደሚጠጋ ተገልጿል። ኃላፊው እንዳሉት በሕይወት ያለ ሰው ስለመኖሩ ጠቋሚ ምልክት አልነበረም።
በብሔራዊ ቴሌቭዢን ጣቢያው ኢርና የተላለፈው ተንቀሳቃሽ ምሥል አደጋው የደረሰበትን አካባቢ ያሳያል።
ሰማያዊ እና ነጭ ቀለም ያለው የሄሊኮፕተሩ ጫፍ ከተቃጠሉ ክፍሎች ጋር ይታያል።
በዚህ አካባቢ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሲረባረቡ እና በጨርቅ የተሸፈኑ አስክሬኖች ሲያወጡም ታይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአደጋው መንስዔ ምንድን ነው?
ስለ አደጋው መንስዔ ከኢራን ባለሥልጣናት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ሚኒስትሮች እንዳሉት ግን ሄሊኮፕተሩ በአስቸጋሪ ጉም እና ዝናብ ከተፈተነ በኋላ ነው አደጋው የተከሰተው።
አደጋው የደረሰበትን ሁኔታ በተመለከተ የአገሪቱ መንግሥት ምርመራ እንደሚያደርግ እና ውጤቱን እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።
ስለ ሄሊኮፕተሩ ምን እናውቃለን?
በብሔራዊ ቴሌቭዢን ጣቢያ የተላለፈው መረጃ ሄሊኮፕተሩ ቤል 212 መሆኑን ጠቁሟል።
ይህም ለካናዳ መከላከያ ሠራዊት በአሜሪካ ተቋም እአአ በ1960ዎቹ የተሠራ ሞዴል ነው።
የኢራን የባሕር ኃይል እና አየር ኃይል 10 ተመሳሳይ ሞዴል ያላቸው ሄሊኮፕተሮች እንዳሏቸው ‘ፍላይትግሎባል’ በ2024 የአየር ኃይሎች ዝርዝሩ ውስጥ ገልጿል።
ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉን የኢራን መንግሥት እንደሚያንቀሳቅስ ግልጽ አይደለም።
በኢራን ብሔራዊ ቴሌቭዢን ጣቢያ መረጃ መሠረት፣ ፕሬዝዳንቱን ይዞ የነበረው ሄሊኮፕተር ስድስት ተሳፋሪዎች እና ሁለት የበረራ ሠራተኞችን ማጓጓዝ ይችላል።
‘ፍላይት ሴፍቲ ፋውንዴሸን’ የተባለው ተቋም ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በኢራን ቤል 212 ሄሊኮፕተር ለመጨረሻ ጊዜ አደጋ የደረሰው በአውሮፓውያኑ 2018 ነበር።












