አይሁዳውያን መንገደኞችን ከበረራ ያገደው የሉፍታንዛ አየር መንገድ 4 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተጣለበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥቂት መንገደኞች የኮቪድ መመሪያን አላከበሩም በሚል ከ128 በላይ አይሁዳውያን መንገደኞችን ከሁለት ዓመት በፊት ከመብረር ያገደው የጀርመኑ አየር መንገድ ሉፍታንዛ የአሜሪካ ትራንስፖርት ሚኒስትር 4 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ጣለበት።
መንገደኞቹ ከኒውዮርክ ተነስተው በፍራንክፈርት አድርገው ወደ ቡዳፔስት ይጓዙ የነበረ ሲሆን አየርመንገዱ በፍራንክፈርት ላይ ካረፉ በኋላ አላሳፍርም ማለቱ ተገልጿል።
የአሜሪካው ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሉፍታንዛ በተሳፋሪዎቹ ላይ አድሏዊ ተግባር ፈጽሟል ብሏል። እንዳይበሩ የተደረጉት መንገደኞች በሙሉ አይሁዳውያን ሲሆኑ በጥቂት መንገደኞች ምክንያት አብዛኛዎቹ አብረው ያልነበረው፣ የማይተዋወቁ የሆኑትን ሁሉንም “እንደ አንድ ቡድን ቆጥሮ” ከልክሏቸዋል ብሏል።
ሚኒስቴሩ ከሲቪል መብቶች ጋር በተያያዘ በፍትሃ ብሄር ክርክር የተጣለ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት እንደሆነ ተገልጿል።
ሉፍታንዛ የፍርድ ሙግቱን ለማስቀረት የገንዘብ ቅጣቱን ለመክፈል መስማማቱን ቢያሳውቅም “አድልዎ አላደረግኩም” ብሏል። ክስተቱን “አሳዛኝ እና ትክክለኛ ባልሆነ የኮሙኒኬሽን ክፍተት የተፈጸመ ስህተት ነው” ብሏል።
“ሉፍታንዛ የበጎ ፈቃድ፣ የመቻቻል፣ የብዝኃነት እና መቻቻልን በዋናነት ያነገበ ምባሳደር ነው” ሲል በመግለጫው ያተተው ሉፍታንዛ በምርመራው ላይ ትብብር በማድረግ እንዲሁም ለሰራተኞቹ ስልጠና ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጿል።
ክስተቱ የተፈጠረው ከሁለት ዓመት በፊት ከኒውዮርክ ወደ ቡዳፔስት በረራ ለማድረግ ፍራንክፈርትን መሻገሪያ ባደረጉ መንገደኞች ላይ ነው።
በርካታ ተሳፋሪዎቹ ወንዶች ሲሆኑ በአይሁዳውያን ኦርቶዶክስ ወንዶች የሚደረገውን ልዩ ስካርፍ የለበሱ ቲኬታቸውን የገዙትም በጉዞ ወኪሎች አማካይነት እንደሆነ ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ከኒውዮርክ ወደ ፍራንክፈርት በነበረው የመጀመሪያ በረራ ላይ ካፒቴኑ አንዳንድ መንገደኞች ማስክ ለማድረግ እንዲሁም እና በአውሮፕላኑ መተላለፊያ ላይ ሰብሰብ እንዳይሉ የተቀመጡ መመሪያዎችን ተላልፈዋል ሲሉ ለሉፍታንዛ የደህንነት ሰዎች አስታውቀው ነበር።
ይህንን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ከ100 በላይ ቲኬቶችን የያዙ ሁሉም አይሁዳውያን ከፍራንክፈርንት በኋላ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዳይቀጥሉ ተደርገዋል።
ሉፍታንዛ ይህ ድርጊቱ መመሪያውን ያከበሩ ተሳፋሪዎችን እንደሚጎዳ ቢገነዘብም ነገር ግን መመሪያውን የጣሱ ተሳፋሪዎችን በተናጠል ለማነጋገር ተግባራዊ ሳያደርግ ቀርቷል ብሏል ሚኒስቴሩ።
አብዛኛዎቹ በዚያኑ ቀን በሌላ በረራ እንዲጓዙ ተደርገዋል ተብሏል።
“ማንም ሰው በጉዞው ላይ መድልዎ ሊደርስበት አይገባም። የዛረው እርምጃ የመንገደኞች ሲቪል መብቶች በሚጣሱበት ወቅት ለመርመር እና እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናችንን ለአየር መንገዱ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል” ሲሉ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ጸሐፊ ፒት ቡቲጌግ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ለምርመራ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው መንገደኞች ምንም አይነት ጥፋትም ሆነ ጥሰት እንዳላዩ የተናገሩ ሲሆን ሉፍታንዛ በኋላ መመሪያዎቹን ያልተከተለ አንድም መንገደኛ መለየት ሳይችል ቀርቷል ተብሏል።
ነገር ግን አየር መንገዱ ለስምምነቱ ታዛዥ እንደሆነ በገለጸበት ወቅት ሰራተኞቻቸው መመሪያዎቹን የተላለፉ መንገደኞችን መለየት ያልቻሉት “ጥሰቶቹ በርካታ ስለነበሩ እና በበረራው አብዛኛው ጊዜ መቀጠላቸውን እና መንገደኞቹም በረራው ሳይቋረጥ መቀመጫቸውን ቀይረዋል” ብሏል።
አየር መንገዱ ከተሳፋሪዎቹ ጋር ባደረገው ስምምነት የከፈለው 2 ሚሊዮን ዶላር ቀደም ታሳቢ ተደርጎለት ተጨማሪ 2 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 4 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ታዟል።












