እስራኤል የጋዛን እርዳታ የማታሳድግ ከሆነ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምትቀንስ አሜሪካ አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባውን የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት በአንድ ወር ውስጥ የማታሳድግ ከሆነ አሜሪካ ወታደራዊ ድጋፏን እንደምትቀንስ አሜሪካ አስጠነቀቀች።
እስራኤል በጋዛ በምታደርገው ጦርነት የጀርባ አጥንት የሆነችው አሜሪካ ይህንን ለማስተካከከል የ30 ቀናት ቀነ ገደብ ማስቀመጧን በደብዳቤ ገልጻለች።
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ እንደገና በጀመረችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት በርካታ ፍልስጤማውያን መሞታቸው እየተዘገበ ባለበት ወቅት ነው አሜሪካ ይህንን ጠንከር ያለ ነው የተባለውን ደብዳቤ ለአጋሯ እና ወዳጇ እሰራኤል የጻፈችው።
አሜሪካ በጋዛ እያሽቆለቆለ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ ክፉኛ እንደሚያሳስባት የገለጸው ደብዳቤው አክሎም እስራኤል በሰሜን እና በደቡባዊ ጋዛ 90 በመቶ የሚሆነውን ሰብዓዊ እንቅስቃሴ መከልከሏን እንዲሁም ማገዷን እሁድ ጥቅምት 3/ 2017 ዓ.ም የተጻፈው ደብዳቤ አስፍሯል።
እስራኤል የደረሳትን ደብዳቤ እየገመገመችው እንደሆነ አንድ ባለስልጣኗ አስታውቀው አገራቸው “ይህንን በቁም ነገር እንደምትመለከተው” እና ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር “የተነሱባቸውን ስጋቶች” ለመፍታት አቅደናል ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለፍልስጤማውያን ሰብዓዊ እርዳታን ሆን ብላ እያገደች ነው ተብሎ የሚቀርብባትን ክስ የማትቀበለው እስራኤል የምታደርገው የተቀናጀ ጥቃት የሐማስ መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ነው ስትል በተደጋጋሚ ትሰማለች።
ወደ ጋዛ የሚገቡ እርዳታዎችን እንዲገቡ የመፍቀድ እና የማስተዳደር ኃላፊነት ያለው የእስራኤል ወታደራዊ አካል ኮጋት ከአለም የምግብ ፕሮግራም የተላኩ እርዳታ የጫኑ 30 መኪኖች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ገብተዋል ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ምግብ ድርጅት ለባለፉት ሁለት ሳምንታት ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ምንም አይነት እርዳታ እንዳልገባ ማስታወቁን ተከትሎ ነው ኮጋት ይህንን ያለው። የመንግሥታቱ ድርጅት 400 ሺህ ፍልስጤማውያን ለመኖር የሚያስፈልጋቸው መሰረታዊ ፍጆታዎች እየተመናመነ ነው ብሎ ነበር።
አሜሪካ ለእስራኤል ዋነኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢ ስትሆን የእስራኤል ጦር በጋዛ በሚያደርገው የተቀናጀ ጥቃት ከአሜሪካ የሚደርሰውን የጦር አውሮፕላኖች፣ ሚሳኤሎች እና ሌሎች መሳሪያዎችን ይዞ ነው።
አሜሪካ ለእስራኤል መንግሥት የላከው እና በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተረጋገው ደብዳቤ በመጀመሪያ ሪፖርት የተደረገው አክሲዮስ በተሰኘ ድረ ገጽ ነው። ደብዳቤው ተፈርሞ የወጣው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን እና በመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲን ስም ሲሆን የሰብዓዊ ቀውሱን እንድትቀለብስ በዚህ ወር እንድትቀለብስ ቀነ ገደብ አስቀምጧል።
እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ በምታደርገው ጥቃት ከ42 ሺህ 340 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስትር አስታውቋል። ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ ስር ካለው የጤና ሚኒስትሩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።












