ሴኔጋላዊው አጥቂ ሳዲዮ ማኔ በክለቡ ሙኒክ ታገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቡድን አጋሩ የሆነውን ሊዮር ሳኔን በቡጢ ተማትቷል የተባለው ሴኔጋላዊው አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ክለቡ ባዬር ሙኒክ አገደው።
ከጀርመን እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ባዬር ሙኒክ በማንቸስተር ሲቲ 3 ለ 0 ከተሸነፈ በኋላ በመልበሻ ክፍል ውስጥ ማኔ የቡድን አጋሩ የሆነውን ሊዮር ሳኔን በቡጢ ተማትቷል ይላሉ።
በሁለቱ የቡድን አጋሮች መካከል ጸብ ከተፈጠረ በኋላ እንዲለያዩት የተደረጉት በሌሎች የቡድን አጋሮቻቸው ነው ተብሏል።
የፊታችን ቅዳሜ በሊጉ ከሆፌናያም ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ ማኔ መታገዱን ክለቡ ሙኒክ አስታውቋል። ክለቡ ሴኔጋላዊው የፊት መስመር ተጫዋች “በሥነ-ምግባር ጥሰት” መቀነሱን እና ቅጣት እንደሚጠብቀው ጨምሮ ገልጿል።
የ31 ዓመቱ ማኔ የፈጸምው “የሥነ-ምግባር” ጥሰት ምን እንደሆነ ክለቡ በግልጽ ያለው ነገር ባይኖርም፤ ለእግዱ ምክንያት የሆነው ማክሰኞ ዕለት ተካሂዶ ከነበረው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በኋላ በተፈጠረ ክስተት መሆኑን ግን በመግለጫው ጠቁሟል።
ቢልድ የተሰኘው ጋዜጣ ማኔ ከጨዋታው በኋላ ጀርመናዊው የክንፍ ተጫዋች “በተናገረኝ ነገር ደስተኛ አይደለሁም” በማለት ቅሬታ ስለማቅረቡ ዘግቧል።
ቡድኑ ወደ ጀርመን ከተመለሰ በኋላ ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ ተጫዋች ተብሎ የተሸለመው ሴኔጋላዊ ከአየር ማረፊያ በግል መኪና የተወሰደ ሲሆን፣ ሊዮር ሳኔ ግን ከቡድን አባላቱ ጋር በአውቶብስ ሄዷል።
ክስተቱን በተመለከተ ሁለቱም ተጫዋቾች ያሉት ነገር የለም። ከክስተቱም በኋላ ሁለቱም ተጫዋቾች ሐሙስ ዕለት ልምምድ አድርገዋል።
ማኔ ከወራት በፊት በ35 ሚሊዮን ፓዎንድ ከሊቨርፑል ወደ ጀርመኑ ክለብ ሙኒክ መዘዋወሩ ይታወሳል።
ማኔ ክለቡን እንደተቀላቀለ 7 ጨዋታዎችን አድርጎ 6 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የጎል ድርቅ አጋጥሞታል። ማኔ ለሙኒክ ጎል ካስቆጠረ 6 ወራት አልፈውታል።
የጀርመን እግር ኳስ ጋዜጠኛ የሆነው ራፋኤል ሆኒገሰተን በቢቢሲ ሬዲዮ 5 ላይ በቀረበበት ወቅት፣ የሁለቱ ተጫዋቾች አለመግባባት ሜዳ ላይ የጀመረ ነበር ብሏል።
ማኔ እና ሳኔ ሜዳ ላይ ሳሉ ቃላት ሲለዋወጡ መታየታቸውን አሳታውሶ፣ ወደ መልበሻ ክፍል ከገቡ በኋላ ማኔ ሳኔን በጥፊ መማታቱን እና የሊዮር ሳኔ ከንፈር አብጦ እንደነበረ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሁለት ሰዎች ነግረውኛል ብሏል።
ጋዜጠኛ ራፋኤል ባሎንዶር ሊያሸንፍ ይችላል ተብሎ ሲወራለት የነበረው ማኔ በጉዳት ምክንያት ከዓለም ዋንጫም ሲቀር፤ እንዲሁም በቶማስ ቱኅል ከተቀያሪ ወንበር እየተነሳ እንዲጫወት መደረጉ ላያስደስተው ይችላል በማለት ሴኔጋላዊው አሁን ባለበት ሁኔታ ደስተኛ ላይሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
ማኔ ያለበት አቋም በጣም ደካማ ነው ማለት ባይቻልም፤ ሙኒክ ሲያስፍርመው የጠበቀው አይነት ተጫዋች ግን አይደለም ይላል ራፋኤል።












