ምስጢራዊ ሰነዶችን አሾልኮ ያወጣው የ21 ዓመት ወጣት በቁጥጥር ሥር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, FACEBOOK
የአሜሪካን እና አጋሮቿን ምስጢራዊ ሰነዶች ይፋ ያደረገው የአገሪቱ አየር ኃይል ብሔራዊ ዘብ አባል የሆነ የ21 ዓመት ወጣት በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ምስጢራዊ ሰነዶቹን በበይነ መረብ ጨዋታ (ጌም) ጽሑፍ መላላኪያ ገጽ ላይ ያሰራጨው ጃክ ቴሼራ በአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ በሰላላ ክስ ይመሰረትበታል ተብሏል።
ወጣቱ ማሳቹሴትስ ግዛት ውስጥ ከሚገኘው ከወላጆቹ መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ሥር ሲውል የሚያሳይ ምስል ይፋ ተደርጓል።
ቴሼራ ይፋ ያደረጋቸው ሰነዶች በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ምስጢራዊ ጉዳዮችን ይፋ ከማድረጉም በላይ አሜሪካ በአጋሮቿ ላይ ስለላ ስለማድረጓ አጋልጧል።
ወጣቱ ዛሬ አርብ ሚያዚያ 6/2015 ዓ.ም. ቦስተን በሚገኝ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ሲቢኤስ ወጣቱ እአአ 2019 ላይ በሠራዊቱ መቀጠሩን እና የነበረው የሥራ እርከን የጀማሪ መሆኑን ከይፋዊ ሰነዶች ላይ መመልከቱን ዘግቧል።
የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ ወጣቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን ይፋ ቢያደርጉም፣ ምስጢራዊ ሰነዶችን አሾልኮ ለማውጣት ምን እንዳነሳሳው ያሉት ነገር የለም።
በሌላ መግለጫ ደግሞ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ብርጋዲዬር ጄኔራል ፓር ራይደር ድርጊቱ “ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ወንጀል ነው” ብለዋል።
ይህን መሰል ምስጢራዊ ሰነድ እንዴት ገና በወጣትነት ዕድሜ እና በታችኛው እርከን ባለ ሠራተኛ እጅ ላይ ሊገባ ቻለ ተብለው የተጠየቁት ብርጋዲዬር ጄኔራሉ፤ በአሜሪካ ጦር ውስጥ ሠራተኞች “ገና በወጣትነት እድሜ ከፍተኛ ኃላፊነት ይጣልባቸዋል” ሲሉ መልሰዋል።
ጃክ ቴሼር ማን ነው?
ጃክ ቴሼር እአአ 2019 ሥራ ይጀምር እንጂ በማሳቹሴትስ ከሚገኘው የትውልድ ከተማው ኖርዝ ዳይተን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በ2020 ነው።
የማሳቹሴትስ የአየር ኃይል ብሔራዊ ዘብ የደኅንነት ክንፍ ባልደረባ የሆነው ወጣቱ፣ የሥራ ድርሻው የአሜሪካ አየር ኃይል ዓለም አቀፍ ኮሚዩኒኬሽን ነበር።
ጃክ ቴሼር እሰካሁን ድረስ ለሥራ ተብሎ ከአገሩ አሜሪካ ወጥቶ አያውቅም።
ምስጢራዊ ሰነዱ በተጋራበት የጽሑፍ መልዕክት መላላኪያ ቡድን ውስጥ አባል የሆነ አንድ ወጣት ጃክ ቴሼርን “ስለ ጦር መሳሪያ ጽኑ ፍላጎት ያለው ወጣት” ሲል ገልጾታል።
ከቴሼር ጋር በአንድ ክፍል አብሬው ተምሪያለሁ ያለ የ22 ዓመቱ ኤዲ ሶውዝ ደግሞ ቴሼር በዚህ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ማመን አልቻልኩም ሲል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግሯል።
“በጣም ጥሩ ልጅ ነው። ችግር ፈጣሪ አይደለም። ዝምተኛ ነው። ሁኔታው በአጋጣሚ የተሰራ ቀሽም ስህተት አይነት ይመስለኛል” ሲል ተናግሯል።
ቴሼር ያወጣቸው ሰንዶች ምን ይዘዋል?
በኢንተርኔት አማካይነት ጌም በሚጫወቱ ሰዎች ዘንድ ዝነኛ በሆነው እና ዲስኮርድ በተባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከወራት በፊት ከ100 በላይ ምስጢራዊ ሰነዶች ተለቀው ነበር።
ሰነዶቹ በዩክሬን እየተደረገ ስላለው ጦርነት ምስጢራዊ ጉዳዮችን ይፋ አድርጓል። በመላው ዓለም ስላሉ አገራት ስለላም መረጃ ይዟል።
ሰነዶቹ የምዕራባውያን አገራት ልዩ ኃይሎች በዩክሬን ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ስለመሆናቸው አሳይቷል። ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ላቲቪያ እና ኔዘርላንድስ ልዩ ኃይሎችን ወደ ዩክሬን መላካቸውን አጋልጧል።
ግብፅ በምስጢር ለሩሲያ ሮኬቶችን ለማቅረብ ስለመዘጋጀቷም አጋልጧል። ዋሽንግተን ፖስት ምስጢራዊ ሰነዱን ከተመለከተ በኋላ ግብፅ በድብቅ 40 ሺህ ሮኬቶችን አምርታ ለሩሲያ ልታቀርብ ነው ብሏል።
እንዲሁም የተባባሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጌቴሬዝ የሩሲያን ፍላጎት ለሟሟላት ፍላጎት አላቸው ብላ አሜሪካ እንደምታምን ሰነዶቹ አጋልጠዋል።












