“ሙስሊም ነኝ፤ ረመዳን ሲመጣ ግን መበሳጨት እጀምራለሁ” በቤይሩት ኢትዮጵያዊቷ ሠራተኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለስደተኛ የቤት ሠራተኞች የአረብ አገራት ኑሮ ወትሮም የድሎት አይደለም።
ድብድባ፣ ብዝበዛ እና ውርደትን የሚያስተናግዱ ጥቂቶች አይደሉም። በአሰሪዎቻቸው ከባድ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀምባቸዋል።
አብዛኞቹን በዚህ ሁሉ መሃል አበርትቶ የሚያቆያቸው ሕይወትን የመለወጥ ተስፋ እና የተሸከሙት የቤተሰብ ኃላፊነት ነው።
በተለይ በረመዳን ወር የቤት ሠራተኞቹ የሚደርስባቸው የጉልበት ብዝበዛ የበረታ ነው። በዚህ ምክንያት ለጤና ችግር የሚዳረጉ እንዳሉም ይሰማል።
የእኛ ለእኛ በስደት የተሰኘው በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኛ የቤት ውስጥ ሠራተኞች ማኅበር መሥራችና በአረብ አገራት በቤት ሠራተኝነት ስትሰራ የቆየችው ባንቺ ይመር፣ በረመዳን ወቅት ከባድ ትዝታ ነው ያላት።
“በተለይ አያት ቤት የምትሰሪ ከሆነ ለአፍታ መቀመጥ፣ ለአፍታ ማሸለብ ህልም ነው” ትላለች።
ከቤተሰብ ጋር በጋራ መኖር ባህል በሆነባቸው የአረብ አገራት፣ በተለይ በረመዳን ወር ልጅ፣ የልጅ ልጅ እንዲሁም ዘመድ ወዳጅ ለኢፍጣር አንድ ላይ መሰባሰባቸው የተለመደ ነው።
ለማፍጠሪያ የሚዘጋጀው ምግብ እና መጠጥም ዓይነቱ ብዙ ነው። ቢበላም ባይበላም መዘጋጀቱ አይቀሬ ነው።
ይህ ሁሉ የሥራ ድርሻ ደግሞ የቤት ሠራተኞቹ ነው።
“እነርሱ ተኝተው ነው የሚያሳልፉት። ለሶላት ብቻ ነው በየመሃሉ የሚነሱት” የምትለው ባንቺ፣ ሠራተኞቹ እንደእነሱ ጾመኛ ቢሆኑም ግድ የሚሰጣቸው ጥቂት መሆናቸውን ትናገራለች።
ከተቀጠሩበት ቤት አልፎም የዘመዶቻቸውን ቤት እንዲያጸዱ እና ምግብ እንዲያበስሉ የሚላኩም አሉ።
ሰላም መሐመድ በሊባኖስ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ መሥራት ከጀመረች አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል።
“ሙስሊም በመሆኔ ለረመዳን ወር ትልቅ ፍቅር ቢኖረኝም፣ ካለብኝ የሥራ ጫና የተነሳ ረመዳን ሲመጣ መነጫነጭ እና መበሳጨት እጀምራለሁ” ትላለች።
ሰላም እንደምትለው ጾመኛ ብትሆንም የተለየ የሚደረግላት እዝነት የለም። ከሥራው በሰበብ አስባቡ ወደ ኋላ ማፈግፈግም የማይታሰብ ነው። የእንጀራ ገመድን ያሳጥራል።
ሰላም አሁን በምትሰራበት ቤት ስድስት የቤተሰብ አባላት ናቸው የሚኖሩት።
“አሰሪዎቼ ባህርያቸው ብዙም የከፋ አይደለም” የምትለው ሰላም፣ ረመዳን ሲመጣ ግን ዘመድ አዝማድ ስለሚሰበሰብ እና ብዙ ዓይነት ምግብ ስለሚዘጋጅ የሥራ ጫናው ከአቅሟ በላይ እንደሚሆንባት ትናገራለች።
በመሆኑም “በየዓመቱ የረመዳን ወር ሲመጣ የሥራ ጫናው ፊት ለፊቴ ይደቀናል። ያነጫንጨኛል። ቤተሰቦቼ ሲያወሩኝም በደንብ አላናግራቸውም” ትላለች።
መኪያ ጀማልም እዚያው ቤይሩት የተለያዩ ቤቶች ውስጥ ተቀጥራ ሠርታለች።
አሁን ያለችበት ቤት መሥራት ከጀመረች አራት ዓመታት ተቆጥረዋል።
አሰሪዎቿ ሦስት ልጆች አሏቸው። አብሯቸው የሚኖር ሌላ ዘመድም አለ። ለዚህ ሁሉ ቤተሰብ ምግብ የምታዘጋጀው፣ ቤት የምታጸዳው፣ እቃ የምታጥበው እርሷ ናት።
በአዘቦት ቀንም ያለው ሥራ ለእርሷ ፈታኝ ቢሆንም፣ በረመዳን ወቅት የሚኖረው ሥራ ፋታ የሚሰጣት አይደለም።
መኪያ በረመዳን ትጾማለች። ጾመኛ በመሆኗ ግን የምታገኘው እንክብካቤም ሆነ እረፍት አሊያም ሥራ ስለበዛባት የምታገኘው ተጨማሪ ክፍያ የለም። ቢሆንም ረመዳን ሲመጣ ደስ ይላታል።
“የማሳልፈው ጊዜ ከባድ ቢሆንም፤ ጤነኛ ሆኜ በመስራቴ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ” ትላለች።
በአረብ አገራት በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው ይሠራሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ከሁለት ዓመታት በፊት ባወጣው መረጃ በሊባኖስ ወደ 250 ሺህ የሚጠጉ የቤት ሠራተኞች የሚኖሩ ሲሆን 99 በመቶ የሚሆኑት የሥራ ፈቃድ ያላቸው ስደተኞች ናቸው።
ከእነዚህም መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በወር ከ150 እስከ 400 ዶላር ደመወዝ የሚከፈላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ፊሊፒናውያን፣ ባንግላዲሻውያን እና ሲሪላንካውያን ሴቶች ናቸው።

“ሠራተኞች እንዳይለቁባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ”
ሰላም ከዚህ በፊት በሰራችበት ቤት እርሷን ጨምሮ ሁለት ኢትዮጵያውያን እና አንድ ባንግላዲሻዊት ሠራተኞች ይሰሩ እንደነበር ታስታውሳለች።
ቤቱ መሬት ላይ ያለ ቪላ በመሆኑ ከላይ፣ ታች መውጣት እና መውረዱን አስቀርቶላቸዋል።
በቤት ውስጥ የሚኖሩት ስድስት ቤተሰቦች ናቸው። የልጅ ልጅ እና ሌሎች ዘመድ አዝማዶች ሲጨመሩ ግን ከ15 በላይ የቤተሰብ አባል ይሆናሉ።
በተለይ ቅዳሜ እና እሁድ የልጅ ልጆች በአንድ ላይ መሰባሰብ የተለመደ ነው። ረመዳን ሲሆን ግን ይህ የሚሆነው በየቀኑ ነው። በየቀኑ እስከ 20 ሰው ለኢፍጣር ይሰበሰባል።
“ለኢፍጣር ለአንድ ሰው ብቻ የሚቀርበው መመገቢያ ሳህን እና ብርጭቆ ብዙ ነው” ትላለች።
የማፍጠሪያ ሥነ ሥርዓቱም ጊዜ ይወስዳል። ቶሎ በላ በላ አድርጎ መነሳት የማይታሰብ ነው።
ሰላም እንደምትለው ምግብ ከመሥራቱ እና ከማስተናገዱ በላይ ተመግበው እስከሚጨርሱ መጠበቅ ያደክማል።
በረመዳን ወቅት በተለይ በአረብ አገራት ለማፍጠሪያ ብዙ ዓይነት ምግብ ነው የሚዘጋጀው።
ዛሬ የተሰራውን ለነገ ማሳደር አይቻልም። ያደረ ምግብ ከመደፋት ውጪ ሌላ ዕጣ ፋንታ የለውም። በየቀኑ ምግብ እንደ አዲስ ነው የዘጋጀው።
“ብርጭቆውን አንድ ነገር ከጠጡበት በኋላ ደግመው አይጠቀሙበትም። ሌላ አዲስ ነው የሚቀርበው” ትላለች ሰላም።
መኪያም ረመዳን ሲመጣ የሚያስመርራት ሥራው ነው። በተለይ ምግብ መሥራት እጅግ የምትመረርበት ጉዳይ ነው።
ጾመኛ ናት ብለው የተለየ እንክብካቤ የሚያደርጉ ቢኖሩም፣ እዝነት የሌላቸውም አሉ የምትለው መኪያ፣ እሷ የምትሰራበት ቤት ክፉ ባይሆኑም “ቀን ቀን ግን አያስተኙኝም” ትላለች።
እስካሁን በሥራ ብዛት ምክንያት የገጠማት የከፋ የጤና ችግር ባይኖርም፣ አንዳንዴ በእንቅልፍ እጦት የማዞር ስሜት እንደሚሰማት ትናገራለች።
በአረብ አገራት በረመዳን ወቅት በሥራ ጫና ምክንያት ሥራ የሚለቁ አሉ።
ሰላም እንደምትለው አሰሪዎች በረመዳን ወር ሠራተኞች እንዳይለቁባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። በጣምም ይፈራሉ።
በዚህም ምክንያት አንዳንድ አሰሪዎች ብዙም ባይሆን ለሠራተኞቻቸው ጉርሻ (ቲፕ) ይሰጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በረመዳን የኢትዮጵያውያኑ የአንድ ቀን ውሎ
ሰላም እንደምትለው የማፍጠሪያ ሰዓት ከተጠናቀቀ በኋላ እስከ ሌሊቱ 6፡00 ድረስ እቃ ሲያጥቡ ነው የሚያመሹት። የቤት ሠራተኞቹ ሦስት ቢሆኑም ቶሎ አይጨርሱም።
ከዚያ ሌሊት 7፡00 ላይ ጋደም ይላሉ። ገና ዓይናቸው መከደን ሲጀምር ሌሊት 8፡00 ላይ ለስሁር [ለጾም ማሰሪያ] ምግብ እንዲያቀርቡ ይቀሰቀሳሉ።
ምግቡንም አሟሙቀው ያቀራርባሉ።
የተመገቡበትን እቃ አነሳስተው ሲያጥቡ ወገግ ብሎ ይነጋል።
“በአንድ ቀን ውስጥ ብንተኛ ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዓት ነው” ትላለች ሰላም። ከዚያም ቀኑን ሙሉ ያው ተመሳሳይ ሒደት ይቀጥላል።
“እግሬ ያብጣል። ሐኪም ቤት ስሄድ እረፍት አድርጊ ነው የሚሉኝ። እኔ ግን እረፍት የለኝም” ትላለች ሰላም።
መኪያም ብትሆን በረመዳን ወቅት ከዚህ የተለየ ቀን አይደለም የምታሳልፈው።
የቀን ውሎዋ የሚጀምረው የአሰሪዎቿን ልጆቹ ትምህርት ቤት በመላክ ነው። ከዚያ የቤት ጽዳት ይከተላል። እሱን ስትጨርስ ምግብ ማዘጋጀት ትጀምራለች።
“አንዳንዴ ጽዳት ሳልጨርስ ልጆቹ ከትምህርት ቤት ይመለሳሉ” ትላለች።
እንዲህ እንዲህ ሲባል ለአፍታ አረፍ ሳትል ይመሻል። ለማፍጠሪያ ያዘጋጀችውን ምግብ ታቀራርባለች። ምግብ ከተመገቡ በኋላ ቶሎ ብሎ እቃ ማነሳሳት አይታሰብም። ተረጋግተው ትኩስ መጠጦችን እስኪጎነጩ መጠበቅ የግድ ነው።
ከሌሊቱ 6፡30 የተመገቡበትን እቃ አነሳስታ እና አጽድታ ትጨርሳለች።
ሰባት ሰዓት ላይ ትተኛለች። ከዚያ እንደገና ለስሁር 9፡00 ተነስታ ምግብ ታሰናዳለች።
“አብልቼ ተመልሼ እተኛለሁ። እንደገና ጠዋት 1፡00 ላይ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት እሸኛለሁ። እረፍት የለኝም። በቀን ውስጥ የምተኛው ለሦስት አሊያም ለአራት ሰዓታት ብቻ ነው። ግን ስደት ላይ አይደለሁ። አልሃምዱሊላህ ነው የምለው” ትላለች።
ለዚህ ድካማቸው በወር የሚከፈላቸው ቢበዛ 200 ዶላር ነው።
ወደ ስደት ጉዞ
ሰላም ትውልዷ በደቡብ ክልል፣ ዲላ ከተማ ነው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ በግብርና ሙያ በዲፕሎማ ተመርቃለች።
ትዳር መሥርታም ስትኖር ነበር። ወደ አረብ አገር ያቀናችው ቤት ኪራይ አስመርሯት ጥራ ግራ የራሷን ቤት ለመሥራት በማለም ነበር። ነገር ግን የጠበቀችው እና ያሰበችው አልገጠማትም።
ዓመታት ቢቆጠሩም ቤት አልሰራችም። ተስፋ ግን አልቆረጠችም። አሁንም ሕይወቷን ለመለወጥ እዚያው በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ እየሰራች ነው።
በቆየችባቸው ዓመታት ውስጥ ብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈች የምትናገረው ሰላም፣ ገና እንደገባች ሊባኖስ የተቀበለቻት በህመም እንደነበር ታስታውሳለች። ለሦስት ወራትም በህመም ምክንያት ሥራ አልገባችም።
ሥራ አስቀጣሪው ቢሮ [መክተብ] ተኝታ ነበር ወራቱን ያሳለፈችው። ወደተቀጠረችበት ቤት ቢወስዷትም አልተመቻትም።
ገና በሄደች በወራት ውስጥ ወደ አገሬ መልሱኝ የሚል ጥያቄ አቀረበች።
ምላሻቸው “‘የመጣሽበትን የትኬት ዋጋ እና ሁሉንም ወጪሽን ሳትከፍይ በነጻ የሚሸኝሽ የለም’ የሚል ነበር” ትላለች።
በወቅቱ ይህንን ማድረግ ባለመቻሏ ሌላ ቤት ወሰዷት።
“እዚያም በተገቢው መልኩ ደመወዜን አይከፍሉኝም ነበር” ትላለች። የሚያስፈለጋትን የምታሟላው በዚያው በምታገኘው አነስተኛ ደመወዟ ነው።
ለተሰደደችበት ዓላማዋ የሚተርፋትን ገንዘብ መቆጠብ አልቻለችም። ከዚህም ወጥታ ሌላ ቤት ውስጥ ገባች።
እዚያም የጠበቃት ድብደባ እና አካላዊ ጥቃት እንደነበር ትናገራለች። ብዙም ሳትቆይ ከዚያም ለመልቀቅ ተገዳለች።
ቤቶችን ቀያይራለች። ተስፋ እንጂ ሕይወቷ ላይ የታየ ለውጥ እንደሌለ ግን ትናገራለች።
መኪያ ጀማልም በስደት መኖር ከጀመረች ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል።
ኑሮዋ በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ነበር። መኪያ ከ11ኛ ክፍል አቋርጣ ስደትን የመረጠችው ቤተሰቦቿን ለመርዳት በሚል ነበር።
ስትሄድ ለሁለት ዓመት ኮንትራት ቢሆንም ያሰበችው ስላልሞላ አራዝማ እዚህ ደርሳለች።
“በምን ሁኔታ ውስጥ እንደምንሠራ የማይረዳ ቤተሰብ አለ”
የትም ይሁን የት ከአገር ውጭ ከሚገኝ ሰው እጅ የሚጠብቁ ብዙ ናቸው። ውጭ አገር ገንዘብ በቀላሉ የሚገኝ፣ የሚታፈስ የሚመስላቸውም አሉ።
በዚህም ምክንያት በርካቶች ገንዘባቸውን በትነው የተሰደዱበትን ዓላማ ሳያሳኩ ባዶ እጃቸውን ይቀራሉ።
“በምን ሁኔታ ውስጥ፣ ምን ዓይነት ሥራ እንደምንሰራ የሚረዳ የለም” ሲሉ መስማትም የተለመደ ነው።
ሰላም ወደ ቤሩት ከመሄዷ በፊት ትዳር መስርታ ነበር። አገሯ ላይ ቤት ለመሥራት በየወሩ ከምታገኘውም ሆነ እቁብ ገብታ የምትቆጥበውን ገንዘብ ትልካለች። ሆኖም ለሁለት ዓመት ገንዘብ ብልክም ቤቱ አልተሰራም።
ለቆርቆሮ፣ ለምስማር እና ለእንጨት መግዣ የምትለከው ገንዘብ እንደባከነባት እና አገልግሎት ላይ እንዳልዋለ ትናገራለች።
“ፎቶ እያነሳ የሚልክልኝ የሌላ ሰው የቤት ክዳን ቆርቆሮ ነበር” ትላለች።
መኪያም ከምታገኘው ገንዘብ ለቤተሰብ ትልካለች። ወደ ስደት ስትሄድ በከፈተችው የግሏ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ገንዘብ ትቆጥባለች። ለቤተሰብ መርዳት ያለባትንም በፕሮግራም እንደምታደርግ ትናገራለች።
ብዙዎች ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ ባክኖ ለብስጭት እንደሚዳረጉ የምትናገረው መኪያ፣ እነዚህ ስደተኞች ገንዘብ ሲልኩ በፕሮግራም እና በዕቅድ መሆን እንዳለበት እና ለራሳቸውም ገንዘብ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ትመክራለች።
መኪያ መቼ ወደ አገሯ እንደምትመለስ አታውቅም። አንድ ቀን ግን ስትመለስ በአገሯ ላይ ሰርታ የመለወጥ ህልም አላት።












