ለኳታር ንጉሣውያን ቤተሰቦች እና ለቱጃሮች ያለዕረፍት የሚሰሩት የቤት ሠራተኞች ሕይወት

የቤት ውስጥ

በባሕረ ሰላጤዋ አገር ኳታር በውጭ አገር ሠራተኞች ላይ ስለሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተለያየ ጊዜ ሪፖርቶች ይወጣሉ።

የዘንድሮውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ዝግጅትን ተከትሎም በስታዲየሙ እና በሆቴሎች ግንባታ ስለተሳተፉ የውጭ አገር ሠራተኞች አያያዝ ብዙ ተጽፏል።

ይሁን እንጂ ለኳታር ገዢ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ስለሚሰሩ የውጭ አገር የቤት ውስጥ ሠራተኞች እምብዛም አልተነገረም።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እነዚህ የቤት ውስጥ ሠራተኞች መብታቸው በወረቀት ላይ ቢሰፍርላቸውም ተግባር ላይ ግን የለም።

በኳታር ባለሥልጣን ቤት ውስጥ ተቀጥራ የምትሰራው ግላዲስ [ስሟ የተለወጠ] በቀን ውስጥ ከጠዋቱ 2፡00 ጀምሮ እስከ ምሽቱ 5፡00 እንደምትሰራ ትናገራለች።

ቤት ታጸዳለች፤ ምግብ ታዘጋጃለች፤ ልጆችን ትጠብቃለች።

የምትመገበው የእነርሱን ትራፊ ነው። ግላዲስ እንደምትለው በእነርሱ ቤት ውስጥ መሥራት ከጀመረችበት ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ በፊት አንስቶ የእረፍት ቀን ኖሯት አያውቅም።

በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኘው ፊሊፒናዊቷ ግላዲስ ‘ማዳም’ ስትል የምትጠራትን አሰሪዋን “እብድ ናት” ስትል ነው የምትገልጻት።

“በየቀኑ ትጮህብኛለች” ትላለች።

ኳታር የ2022 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ለማዘጋጀት የተካሄደውን ውድድር ከማሸነፏ በፊት የውጭ አገር ሠራተኞች ያለ አሰሪያቸው ፈቃድ ሥራቸውን መቀየር አሊያም አገሪቷን ለቀው መውጣት አይችሉም ነበር። በእርግጥ በበርካታ የባሕረ ሰላጤው አገራት አሁንም ያው ነው።

ከዚያ በኋላ ግን ኳታር በሕጎቿ ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ ጀምራለች።

ነገር ግን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሕጎቹ ተግባራዊ ባለመሆናቸው አሁንም የቤት ውስጥ ሠራተኞች የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት ማስቆም አልቻሉም ብሏል።

የግላዲስ ቀጣሪ ከእርሱ ፈቃድ ውጪ ሥራ እንዳትቀይር፣ ከአገርም እንዳትወጣ ለማድረግ ፓስፖርቷን ይዞባታል። ቢሆንም ግን ግላዲስ አሁንም ዕድለኛ እንደሆነች ነው የምታስበው።

ምክንያቱም ቢያንስ ስልኳን እንድትይዝ ተፈቅዶላታል። ይህም ብቻ ሳይሆን እንደ በርካታ ስደተኛ የቤት ውስጥ ሠራተኞች ድብደባ እና አካላዊ ጥቃት አልደረሰባትም።

ይህ በኳታር ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ክስተት ነው።

ግላዲስ አሁን ባለችበት ሥራ ላይ መቆየት የምትፈልግበትም ሌላም ምክንያት አላት። እርሷ ባለችበት ዕድሜ ከዚህ የተሻለ ሥራ አላገኝም ብላ ታስባለች።

አሁን በወር 1 ሺህ 500 ሪያል [412 ዶላር] ታገኛለች። በመሆኑም የምታገኘውን ሁሉ ቤተሰቧን ለመደገፍ ወደ አገሯ መላክ ትችላለች።

የቤት ውስጥ ሠራተኞች መብት

  • የኳታር ፕላን እና ስታስቲክስ ባለሥልጣን ከሁለት ዓመት በፊት ያወጣው መረጃ በአገሪቷ 160 ሺህ የሚሆኑ የውጭ አገር የቤት ውስጥ ሠራተኞች እንደሚኖሩ ያመለክታል።
  • በ2017 ኳታር የቤት ውስጥ ሠራተኞች በቀን ውስጥ 10 ሰዓታት ብቻ እንዲሰሩ እና በሳምንት አንድ ቀን የእረፍት ቀን እንዲኖራቸው እንዲሁም በክፍያ እረፍት እንዲኖራቸው ሕግ አውጥታለች።
  • በ2020 እንዲሁ ዝቅተኛ ክፍያ ምን ያህል መሆን እንዳለበት የወሰነች ሲሆን ሠራተኞችም ፈቃድ ሳይጠይቁ ሥራ ለመቀየር ወይም ከአገሪቷ መውጣት እንዲችሉ የሚያስችል መብት ሰጥታለች።
  • ሆኖም አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው እነዚህ ሕጎች በትክክል እየተተገበሩ ስላልሆነ ከፍተኛ የሥራ ጫና፣ የእረፍት እጦት፣ ስድብ እና አዋራጅ የሠራተኛ አያያዞች እንደቀጠሉ ናቸው።
የቤት ውስጥ ሠራተኞች ሥራ ሲሰሩ የሚያሳይ ግራፊክስ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአገራቸው ወጥተው የሚሰሩ ፊሊፒናውያንን የሚረዳው ማይግራንት ኢንተርናሽናል የተሰኘው ድርጅት ባልደረባ ጆዋና ኮንሴፕሽን፣ በርካታ የውጭ አገር ሠራተኞች ያሉበትን የሥራ ሁኔታ አይናገሩም ትላለች።

ምክንያቱ ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ ማግኘት የማይደራደሩበትና ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ በመሆኑ ነው።

በባሕረ ሰላጤው አገራት የሚኖሩት ግን በነጻነት ለማውራት በራስ መተማመን አላቸው ትላለች። ብዙ ጊዜም የሚደርስባቸውን የከፋ ጥቃት ይናገራሉ።

አንዲት ሴት አሰሪዋ ጭንቅላቷን ይዞ ሽንት ቤት ውስጥ እንደሚዘቀዝቃት እና ሲናደድ ምግብ እና ውሃ እንደሚከለክላት ተናግራለች።

በአንጻሩ በንጉሣውያኑ የአል ታኒ ቤተሰብ የተቀጠረች ሠራተኛ ግን በተሻለ ሁኔታ እንደሚይዟት ተናግራለች። ነገር ግን በአዲሱ ሕግ መሠረት ሁሉም ሠራተኞች የእረፍት ቀን ሊኖራቸው ቢገባም እርሷ ግን እረፍት የላትም።

አልቲያ [ስሟ የተለወጠ] ከቢቢሲ ጋር በቪዲዮ ቃለ ምልልስ ያደረገችው በንጉሣውያኑ ቤተሰብ መኖሪያ ምድር ቤት ውስጥ ሆና ነበር። 

አልቲያ አገሯ ፊሊፒንስ ውስጥ ይኑረኝ ብትል እንኳን መግዛት የማትችለውን አይፎን ስልክ፣ ልብሶች፣ ጌጣ ጌጦች እና በየዓይነት ጫማዎች አሰሪዎቿ እንደሰጧት ታስረዳለች።

ግላዲስ ግን ስደት ያስመረጣትን እና ለመኖር የሚያስፈልጋትን ክፍያ እንኳን በቅጡ አታገኝም።

አልቲያ በምትሰራበት ቤት ሌሎች ፊሊፒናውያን የቤት ሠራተኞችም አሉ። 

የራሳቸው መኝታ ክፍል እና የጋራ ማብሰያ ክፍል አላቸው። ይህ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ምክንያቱም አልቲያ በቲክቶክ እና በፌስቡክ የምታያቸው ሠራተኞች ምግብ ለማግኘት ሲለምኑ አሊያም የሆነ አካል ነፍሳቸውን እንዲታደግላቸው ሲማጸኑ ነው። የእርሷን ያህል ዕድለኛ አይደሉም።

“ሁልጊዜ እነዚህን ቪዲዮዎች አያለሁ። ለዚህም ነው እኔ ዕድለኛ እንደሆንኩ የሚሰማኝ። ለእኔ እያንዳንዱ ቀን ተረት ነው የሚመስለኝ” ትላለች።

ቢሆንም ግን ከፍ ያለ ጣሪያ ባላቸው፣ በወርቅ በተለበጡ ጥንታዊ እቃዎች፣ በእንቁ ያሸበረቁ ትላልቅ ጠረጴዛዎች እና በትኩስ አበቦች የተዋቡ በተረት እንደምታውቀው እና “የሲንደሬላ ቤተ መንግሥት” ስትል በገለጸችው ቤት ውስጥ መሥራት ከባድ ነው ትላለች።

ቀኗን የምትጀምረው ከማለዳው 12፡30 ነው። ቁርስ ማዘጋጀት የሚጀምሩት በዚያ ሰዓት ነው። አልቲያ ምግብ የምትበላው ቤተሰቡ በሙሉ ተመግበው ከጨረሱ በኋላ ነው።

ተመግበው ከጨረሱ በኋላ እቃውን አነሳስተው ክፍሉን ያጸዳሉ። ከዚያም እንደገና ቦታውን ለምሳ ያዘጋጃሉ።

“ሠራተኞቹ ብዙ ስለሆንን ሥራው ቀላል ነው” ትላለች።

ከዚያም ሠራተኞቹ ከቀኑ 9፡00 እስከ አመሻሽ 12፡00 ድረስ እረፍት ይወስዳሉ።

ከዚያም እራት ያዘጋጃሉ። እራት ተበልቶ ሲጠናቀቅ የአልቲያም ሥራም በዚሁ ያበቃል። ነጻ ትሆናለች። ንጉሣውያን ቤተሰቡ ፓስፖርቷን ስላልያዙባት ካሰኛት ከግቢው መውጣትም ትችላለች።

ይሁን እንጂ አልቲያ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናትን ጨምሮ ሁሉንም ቀናት የምታሳልፈው በሥራ ነው። የኳታር ሕግ የሚፈቅደውን የእረፍት ቀን አታገኝም። ይህ ቤተሰቦቿን ለገንዘብ ለመደገፍ የምትከፍለው ዋጋ ነው።

የሴት ምስል

ፊሊፒናውያን የቤት ሠራተኞችን ከባሕረ ሰላጤው አገራት ንጉሣውያን ቤተሰቦች እና ቱጃሮች ጋር የሚያገናኘው እና ፊሊፒንስ ዋና ከተማ ማኒላ የሚገኘው ቀጣሪ ድርጅት ውስጥ የምትሰራው ሜሪ ግሬስ ሞራሌስ “ቤተ መንግሥት ውስጥ መስራት የሚያስቀና ሥራ ነው” ትላለች።

ሜሪ የቤት ሠራተኞች በቤት ውስጥ ስለሚገጥማቸው ፈተና በጽሁፍ ሃሳቧን ስታጋራ “ቤተሰቡ ለጋስ ነው፤ ሴቶቹ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ሲቆዩ ይወፍራሉ። ጥሩ ነው የሚመግቧቸው” ትላለች። ነገር ግን ንጉሣውያኑ ጥቂት ውስን የሆኑ መስፈርቶች እንዳላቸው ትናገራለች።

ለኳታር ንጉሣውያን ቤተሰብ የሚላኩ ሠራተኞች “ዕድሜያቸው ከ24 እስከ 35 ዓመት መሆን እንዲሁም ቆንጆ መሆን አለባቸው” ትላለች።

በበርካታ አገራት በመልክ ሰዎችን መቅጠር ግን ሕግ ወጥ ነው።

ማይግራንት ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት ባልደረባዋ ጆዋና ኮንሴፕሽን በበኩሏ አልቲያ የተናገረችው እውነት እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ ትላለች።

“ነገር ግን ኳታር ውስጥ ሆና ለእንዲህ ዓይነት ንጉሣውያን ቤተሰብ ስትሰራ የምትኖረውን ሕይወት በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም” ብላለች።

ምክንያቱም አንዳንድ ንጉሳውያን ቤተሰብ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች አገሩን ለቀው ከወጡ በኋላ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።

እንደ አውሮፓውያኑ 2019 የግል ጠባቂ፣ አሠልጣኝ እና የግል አስተማሪ ሆነው የሚሠሩ ሦስት እንግሊዛውያን እና አሜሪካውያን ሠራተኞች የኢምሩን እህት ሼይክሃ አል ማያሳ ቢንት ሃማድ ቢን ካሊፋ አልታኒን እና ባለቤቷን ያለክፍያ ከሥራ ሰዓት ውጪ አሰርተውናል በሚል ኒው ዮርክ ውስጥ ክስ መስርተውባቸዋል።

ጥንዶቹ ግን ክሱን አጣጥለውታል።

የዓለም አቀፍ ሠራተኞች ድርጅት (አይኤልኦ) የአረብ አገራት ቀጠና ዳይሬክተር ሩባ ጃራዳት “ጥቃት እና ትንኮሳን የተመለከቱ ጉዳዮችን፣ የሥራ ደኅንነት እና የጤና እጦትን ማሳወቅ እንዲሁም መፍትሔ መስጠት ፈታኝ ነው” ይላሉ።

ድርጅቱ እንደሚለው ይህ አሁንም ፈታኝ ሆኖ የሚቀጥል ቢሆንም፣ ዝቅተኛ የክፍያ መጠንን፣ በሳምንት አንድ የእረፍት ቀን፣ የህመም እረፍት እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲኖር የሚያረጋግጡትን አዲስ ሕጎች ተግባራዊ ለማድረግ ከኳታር ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል።

በንጉሣውያኑ ቤተ መንግሥት የምትሰራው አልቲያ ረዥም ሰዓት በሥራ ብታሳልፍም በሥራዋ ግን ደስተኛ ናት ወደ መኝታዋ ከሄደች በኋላ ቤተሰቦቿን ታወራለች።

አገሯ ይናፍቃታል፤ ምክንያቱም ተረት የሚመስለው ቤተ መንግሥት የእርሷ አይደለም። ቢሆንም ወሳኝ የገቢ ምንጯ ነው። “ከዚህ ሥራ ውጪ ቤተሰቦቼን የምረዳበት ሌላ ሥራ የለኝም” ትላለች።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የኳታር ንጉሣውያን ቤተሰብ እና በለንደን የሚገኘው ኳታር ኤምባሲ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።