የዓለም ዋንጫ አዘጋጇ ኳታር ክፍያ የጠየቁ ሠራተኞችን አባረረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ዋንጫ ዝግጅት ላይ የምትገኘው ኳታር ክፍያቸው እንዲፈጸምላቸው የጠየቁ ሠራተኞችን ከአገር አባረረች።
ከ60 ያላነሱ ሠራተኞች አደባባይ ወጥተው ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የጠየቁ ሲሆን ከእነዚህ መካከል እስከ የ7 ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው ይገኙበታል ተብሏል።
ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ የታሰሩ ሲሆን በውል ቁጥራቻው ያልታወቁ ደግሞ ከአገር ተባረዋል።
የኳታር መንግሥት ከአገር የተባረሩት “የደኅንነት ሕጎችን ስለጣሱ ነው” ብሏል።
ኳታር እአአ በ2010 ላይ የ2022 የዓለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ ከተመረጠች በኋላ በርካቶች በአገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ያላቸውን ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል።
በስታዲየሞች እና በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች አያያዝም በባሕረ ሰላጤዋ አገር ላይ ጥያቄ ሲያስነሳባት ቆይቷል።
ሠራተኞቹ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ድምጻቸውን ያሰሙት የግንባታ እና ምህንድስና ኩባንያ በሆነው ዘ አል ባንዳረይ ኢንተርናሽል ግሩፕ በተባለ ኩባንያ ዋና ቢሮ ፊት ለፊት ነበር።
ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት መካከል ምን ያህሉ በዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች እና መሠረተ ልማቶች ላይ የተሰማሩ ስለመሆናቸው የተባለ ነገር የለም።

የፎቶው ባለመብት, Twitter
የኳታር መንግሥት ግን ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች የአገር ደኅንነት ሕጎችን በመተላለፋቸው በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብሏል።
“ሰላማዊ ያልነበሩ” ሠራተኞች ግን ከአገር እንዲባረሩ መደረጋቸው የተመላከተ ሲሆን ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅማቸው ላልተሰጣቸው ሠራተኞች የኳታር መንግሥት ክፍያ እንደሚፈጽም አስታውቋል።
ኢኩይደም የተባለ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ክፍያ የጠየቁት ሠራተኞች የባንግላዴሽ፣ ሕንድ፣ ኔፓል፣ ግብጽ እና ፊሊፒንስ ዜግነት ያላቸው ናቸው።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሙስጠፋ ቃድሪ ሠራተኞቹ በሞቃታማ የአየር ጸባይ ተቃውሞ ለማሰማት አደባባይ የሚወጡ ከሆነ ምሽት ላይ ያለ አየር ማቀዝቀዣ እንዲተኙ ሊደረጉ እንደሚችሉ ፖሊስ ነግሯቸዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በ42 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ሲያሰሙ ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ያሳያል” ሲሉ ሙስጠፋ ቃድሪ ተናግረዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት ቢቢሲ ኳታር በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ሕይወታቸው የሚያልፉ ሠራተኞች ቁጥርን አሳንሳ ሪፖርት እያደረገች ነው የሚል ሪፖርት ይዞ ወጥቶ ነበር።












