"ወንጀል ሳይፈጽሙ የመታሰር ያህል ነው" በአሠሪዎቻቸው የሚበዘበዙ ስደተኞች ሰቆቃ

የታሰረ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፊታችን እሑድ ዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀን በሚሊዮኖች ዘንድ ይከበራል።

ባለፉት ሁለት ዐሠርታት ለሠራተኞች የተሻለ ደሞዝ እንዲከፈልና ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግም ትግሉ ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የሚገመገምበት ቀን ነው።

ለውጦች መኖራቸው ባይካድም አሁንም ድረስ መብታቸው የሚጣስ ሠራተኞች በርካታ ናቸው።

በተለይም ስደተኛ ሠራተኞን በማንገላታት በእጅጉ የሚተቸው መካከለኛው ምሥራቅ ነው።

ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ተቋም እአአ በ2017 በመዘገበው መሠረት፣ በዋነኛነት ከእስያ እና አፍሪካ የሚሄዱትን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ወደ 23 ሚሊዮን የሚጠጉ ሠራተኞች ይገኛሉ።

የሚያገኙት ገቢ ለየትውልድ አገራቸው የምጣኔ ሀብት እድገት አስፈላጊ ነው።

የዓለም ባንክ እንደሚለው፣ እአአ በ2020 540 ቢሊዮን ዶላር ወደየአገራቸው ልከዋል።

ይህም አነስተኛና መካከከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት በድጎማ እንዲሁም በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከሚያገኙት ገንዘብ በላይ ነው።

ነገር ግን እነዚህ ሠራተኞች አማካይ ገቢያቸው እጅግ ውስን ነው። የሕክምና አገልግሎት አያገኙም። የሠራተኞች ማኅበራት መቀላቀል አይችሉም። ብዝበዛም ይደርስባቸዋል።

ጥቃት ለሚደርስባቸው ሠራተኞች የሚታገሉ ሦስት ሰዎችን ቢቢሲ አነጋግሯል።

"ወንጀል ሳይፈጽሙ የመታሰር ያህል ነው" ባንቺ ይመር

ባንቺ ይመር ለሰባት ዓመታት ሊባኖስ ውስጥ ነበር የምትሠራው።

"በከፋላ ሥርዓት ውስጥ የቤት ሠራተኛ መሆን ወንጀል ሳይፈጽሙ የመታሰር ያህል ነው" ትላለች።s.

ለሰባት ዓመታት ያህል በሊባኖስ የሠራችው ባንቺ ይመር

የፎቶው ባለመብት, Banchi Yimer

የምስሉ መግለጫ, ለሰባት ዓመታት ያህል በሊባኖስ የሠራችው ባንቺ ይመር

"አንዱ ቤት እንድሠራ ተቀጥሬ የዘመዶቻቸውን ቤት እንዳጸዳና ምግብ እንዳበስል እላክ ነበር" ስትል ታስታውሳለች።

በቀን 18 ሰዓታት ትሠራ ነበር። ራሷን ከወሲባዊ ጥቃት መከላከል ነበረባት። ሕይወቷን የምትገፋው ያለ መሠረታዊ አቅርቦትም ነበር።

"በክረምት አየር አማሞቂያ፣ በበጋ አየር ማቀዝቀዣ መጠቀም አልችልም ነበር። ሰውነቴን ለመታጠብ እንኳን በቂ ውሃ አላገኝም። ስቃይ ነው። ከምሠራበት ቤት ስጠፋ ሰነዶቼን ትቼ ነበር።"

ባንቺ ከብዝበዛ ኑሮ መውጣት የምትችለው ራሷን በሞያ ስታዳብር እንደሆነ በማመን እንግሊዘኛ መማር ጀመረች።

ለሰባት ዓመታት ያህል በሊባኖስ የሠራችው ባንቺ ይመር

የፎቶው ባለመብት, Banchi Yimer

የምስሉ መግለጫ, ለሰባት ዓመታት ያህል በሊባኖስ የሠራችው ባንቺ ይመር

ስትማር ብዙ እንሷው ያሉ ሠራተኞችን አገኘች። ልታሰባስባቸውም ወሰነች።

2017 ላይ 'እኛ ለእኛ በስደት' ተቋም ተመሠረተ።

"ሴቶች በነጻነት የሚወያዩበት ቦታ መፍጠው ነው ፍላጎታችን" ትላለች ባንቺ።

እኛ ለእኛ ሲጀመር 70 ሴቶች ተቀላቀሉ። በወር 5 እና 10 ዶላር ያዋጡ ነበር።

አንዳንዶቹ ለተቋሙ የሚከፍሉት የደሞዛቸውን አብላጫውን እንደነበር ባንቺ ትናገራለች።

የእኛ ለእኛ አባላት ቡና፣ ቅመም፣ ምግብ ይሸጣሉ። ገንዘብ ለማሰባሰብ ባህላዊ መሰናዶዎችም ያዘጋጃሉ።

"የምናገኘውን ገንዘብ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ እናውለዋለን። ትኬት ከ300 እስከ 400 ዶላር ነው የሚሸጠው።"

ለሰባት ዓመታት ያህል በሊባኖስ የሠራችው ባንቺ ይመር

የፎቶው ባለመብት, Egna Legna Besidet

የምስሉ መግለጫ, ለሰባት ዓመታት ያህል በሊባኖስ የሠራችው ባንቺ ይመር

የባንቺ ተቋም በ2018 ቃጠሎ የደረሰባቸውን ጨምሮ 25 ሴቶችን ወደ ኢትዮጵያ ልኳል።

2019 ላይ ባንቺ ወደ ካናዳ ስታቀና ሥራቸው ተጠናከረ።

"በካናዳ 350,000 ዶላር መሰብሰብ ቻልኩ። ይህም ከ700 ባይ ኢትዮያውያን እና የሌሎች አገራት ዜጎችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ረድቷል" ትላለች።

በዝባዥ አሠሪዎችን የሚቀጣ የሕግ አሠራር አለመኖሩ ባንቺን ያሳዝናታል።

"አብዛኞቹ የአፍሪካ ኤምባሲዎች ስለ ሠራተኞቻቸው ግድ የላቸውም። ቅሬታ ስናቀርብም አይተባበሩንም። ፖሊስ ጋር ስንሄድ ሴቶቹን ወደ አሠሪዎቻቸው የሚመልሱም አሉ።"

ፖሊሶች አንዳንድ አሠሪዎችን ማስጠንቀቂያ ከሰጧቸው በኋላ አሠሪዎቹ ሠራተኞቹን የበለጠ ማሰቃየት ይጀምራሉ።

"ቀጣሪ ፈታስሮ አይቼ አላውቅም። ሠራተኛቸውን የደፈሩ እንኳን አይታሰሩም" ትላለች።

"ወሲባዊ ጥቃትን በመከላከሌ ታሰርኩ" አን አቡንዳ

አን አቡንዳ፣ ኩዌት ውስጥ የምትሠራ የፊሊፒንስ ተወላጅ ሠራተኛ ናት።

እንደ አብዛኞቹ ያገሯ ልጆች እአአ በ2000 ከተመረቀች በኋላ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አቀናች።

በሦስት ሳምንታት ኩዌት ገባች። ማብሰል፣ ማጽዳት፣ ማጠብ፣ መጠገን፣ ሁሉም ሥራ እሷ ጫንቃ ላይ ወደቀ።

አን አቡንዳ

የፎቶው ባለመብት, Sandigan Kuwait

በወር 450 ዶላር ይሰጥሻል ተብላ ነበር። ያገኘችው ግን 200 ዶላር ብቻ ነው።

"ትራፊ ምግብ ነበር የሚሰጡኝ። እሱም አይበቃም። እና ምግብ መስረቅ ጀመርኩ። ለምን ሰረቅሽ ሲሉኝ እኔን ምግብ ባለማብላታቸው ማፈር እንደሚገባቸው ነገርኳቸው።"

ከዛ በኋላ የአን ቀጣሪዎች ያንገላቷት ጀመር። ስልክ ወርውረውም መተዋታል።

ከዚያ ደላላ ሌላ ሥራ እንዲፈልግላት ጠየቀች።

አዲሱ ሥራ ግን የተሻለ አልሆነም።

"አዲሱ ቀጣሪ ወሲባዊ ጥቃት ሊያደርስብኝ ሞከረ። በለስላሳ ጠርሙስ ስመታው ደም በደም ሆነ" ስትል ታስታውሳለች።

በዚህ ምክንያት 2 ወራት ታሰረች። ስትለቀቅ ሰው ቤት አልቀጠርም ብላ የሽያጭ ሥራ ጀመረች።

በ2008 ከፊሊፒንስ የሄዱ የቤት ሠራተኞችን በአንድ ማኅበራዊ ዝግጅት አገኘች።

የሚደርስባቸውን መደፈር፣ አካላዊ ጥቃትና ሌሎችም ብዝበዛዎች ነገሯት።

አን ከሰራተኞቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Sandigan Kuwait

"ታሪካቸውን አጠናቅሬ ለኤምባሲያችን ሰጠኋቸው ነገር ግን ምንም አልተፈጠረም" ትላለች።

በአውሮፓውያኑ 2010 የተከሰተው የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ ስደተኛ ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።

ባለሥልጣናቱ ሕጋዊ ሰነድ የላቸውም ያሏቸውን ሠራተኞች በመሰብሰበም ሲጠርዟቸው ነበር።

በበርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ውስጥ በተለምዶ ሥራ ከተወሰኑ ቀጣሪዎች ጋር የተቆራኘ ነው።

ካፋላ ወይም ስፖንሰርሺፕ በተሰኘው አሠራር ቀጣሪዎች የሠራተኞቹን ፓስፖርት መያዝ ይችላሉ።

ሠራተኞቹ ያለ ቀጣሪዎቻቸው ይሁንታ ሥራቸውን ከለቀቁ በሕጋዊ መንገድ የመሥራት ሁኔታቸውም ያከትማል። ይህ አሠራር በጣም አወዛጋቢ ሲሆን አንዳንድ አገራት ይህን ሁኔታ አሻሽለውታል።

"አንዳንድ ሴቶች በዚያን ወቅት ተደፍረዋል። ሕጋዊ አይደላችሁም ስለተባሉና ምንም አይነት ሕጋዊ ከለላ ስሌላቸው እርዳታን መሻት አልቻሉም" ስትል አን ታስታውሳለች።

የፊሊፒንስ ኤምባሲ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል ዐቅም እንዳልነበረው ለአን ነግሯታል።

ገር ግን ኤምባሲው እንዲህ ዓይነት ምላሽ ቢሰጣትም ተስፋ ባለመቁረጥ ሳንዲጋን ኩዌት (የምንማረው ነገር አለ) የተባለ ድርጅት መሠረተች።

በመጀመሪያም ያደረገችው ነገር በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ያሉ የቤት ሠራተኞችን በስልክ ጥሪዎች መርዳት ነው።

የድርጅቱ በጎ ፈቃደኞች ከአሠሪዎቻቸው ማምለጥ የሚፈልጉ ሴቶችን መንገዱን በማሳየት ከኤምባሲው የጉዞ ሰነድ እንዲያገኙ ማመቻቸት ጀመረ።

"በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ በየቀኑ ወደ ሦስት የሚጠጉ ሴቶችን ታድገናል" ትላለች።

ለአን በዋናነት እንደ መሠረታዊ ችግር ታየው የነበረው የቤት ሠራተኞችን የሥራ ሁኔታ የሚቆጣጠር ሕግ አለመኖሩ ነው።

ይህንንም ክፍተት ለመሙላት ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር መሥራት ጀመረች።

በመጨረሻም ኩዌት በአውሮፓውያኑ 2015 የቤት ሠራተኛ ሕግን አጸደቀች።

አን በተጨማሪም ከኩዌት ልዕልት ቢቢ ናስር አል ሳባህ ጋር በመተባበር መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ትመራ ነበር። ይህም አጋጣሚ አስፈላጊ ባለሥልጣናትን እንድታገኝ ረድቷታል።

በኩዌት ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ለጋሾች እና የሃይማኖት ተቋማት ገንዘብ በማሰባሰብ የታሰሩ ሠራተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንዲሁም የሕግ ባለሙያዎችን ውክልና እንዲያገኙ በማድረግ ትገኛለች።

አን አንዳንድ መሻሻሎችን በማየቷ ደስተኛ ናት። ነገር ግን ፍትህን ማግኘት ፈታኝ እንደሆነ ታምናለች።

"አንዳንድ ጥቃት አድራሾችን ፍርድ ቤት ከሰናል ነገር ግን ፍትህ የምናገኘው ምናልባት ከዐሥሩ በአንዱ ላይ ብቻ ነው" ትላለች።

"ከጠፉት መካከል ጥቂቶቹ እስር ቤት ናቸው፣ ቀሪዎቹም ሞተዋል" ማሄንድራ ፓንዲ

ማሄንድራ ፓንዲ ከአገሩ ኔፓል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲያቀና በተስፋ ተሞልቶ ነበር።

ሳዑዲ ስትደርስ ዳጎስ ባለ ደሞዝ በሽያጭ ሠራተኝነት አስቀጥርሃለሁ ብሎ ቃል ለገባለት ወኪልም ከ500 ዶላር በላይ ተበድሮ ከፍሏል።

ነገር ግን ማሄንድራ ሳዑዲ እንደጠበቀው የተስፋይቱ ምድር ሆና አልጠበቀችውም።

ለአሰልቺ ረዣዥም ሰዓቶች መሥራት፣ እዚህ ግባ የማይባል 200 ዶላር ደሞዝ በየወሩ ማግኘት እንዲሁም ብድሩን መክፈል አለመቻሉ ተደምሮ ያስጨንቀው ጀመር

በምሽት የግንባታ ሠራተኛ ሆኖ ሁለተኛ ሥራ ጀመረ።

ድርጅቷ ሳንዲጋን በአሁኑ ወቅት ከፊሊፒንስ በመጡ የቤት ሠራተኞች ቢሆንም የሚተዳደረው ነገር ግን የሌሎች አገራት ሠራተኞችንም ይረዳል።

ማሄንድራ ፓንዲ

የፎቶው ባለመብት, Mahendra Pandey

ከሦስት ዓመታት እንቅልፍ ማጣት በኋላ በአውሮፓውያኑ 200 ማሄንድራ ወደ ኔፓል ተመለሰ። ሲመለስ ሁሉ ነገር ሰልችቶት፣ ከፍተኛ ድካም ተጫጭኖትና በንዴት ነበር።

"ሰዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለሥራ የሚያደርጉትን ስደት እንዲያቆሙ እፈልጋለሁ" ይላል ማሄንድራ።

ነገር ግን ከውጭ አገራት ወደ ኔፓል የሚላከው ገንዘብ ለአገሪቷ በጣም አስፈላጊ ነው። በአውሮፓውያኑ 2020 ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት 24 በመቶ የሚሆነው ይህ ገንዘብ እንደሆነ የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል።

ከመካከለኛው ምሥራቅ የተመለሱ በርካታ ሠራተኞች ከማሄንድራ ጋር በመሆን ፕራቫሲ በተሰኘ የኔፓል አስተባባሪ ድርጅት ልምዳቸውን አካፍለዋል።

"በዚያን ጊዜ ወደ ባሕረ ሰላጤ ያቀኑ በፍጥነት ሀብታም ይሆናሉ፣ ትልቅ ቴሌቪዥን ይገዛሉ የሚል አመለካከት ነበረ። ያንን ትርክት መቀየር ፈልጌ ነበር" ይላል ማሄንድራ።

ማሄንድራ በሳዑዲ ምን ያህል የሃይማኖት ነፃነት እጦት እና የመናገር ነፃነት ላይ ስላለው ገደብም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይናገራል።

በተጨማሪም የቅጥር መልማዮች ለሠራተኞች በደሞዝ ላይ ትክክለኛውን ቁጥር እንደማይነግሯቸውና ያለውንም እውነታ ማጋለጥ ጀመረ።

ከዚያም በመካከለኛው ምሥራቅ ሲሠሩ የጠፉ ሰዎችን ፍለጋ ጀመረ።

ማሄንድራ ፓንዲ ከአያቱ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Mahendra Pandey

"አንዳንድ የቤተሰብ አባላት ዘመድ ወዳጆቻቸው የማይደውሉላቸውና የማይጽፉላቸው ከሆነ እርዳታ እንዴት እንደሚፈልጉ እንኳን አያውቁም። በርካታዎቹ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ናቸው" ሲል ያስረዳል።

ማሄንድራ ከጠፉት መካከል የተወሰኑት በእስር ቤት ውስጥ እንዳሉ ደርሶበታል፣ ነገር ግን በርካቶች መሞታቸውንና አስከሬናቸውንም የወሰደው አካል እንደሌለ ይናገራል።

"የሞቱት ሠራተኞች አስክሬን ለቤተሰቦቻቸው እንዲመለስ ማገዝ ጀመርን። ይህ ሥራ ከኤምባሲዎች እና ኩባንያዎች ጋር በርካታ መመላለሶችን ያካትታል።"

በተጨማሪም "የደም ገንዘብ" በመክፈል ሦስት ሠራተኞችን ከሞት ቅጣት አድኗል።

"ለተገደለው ሰው ቤተሰቦች ይቅርታ እንዲያደርጉ ገንዘብ ከፍለናል። ይህ ብቸኛው ሕጋዊ አማራጭ ነው" ይላል።

የመጀመሪያውም የምሕረት ጉዳይ በአውሮፓውያኑ 2012 ሲሆን 20 ሺህ ዶላር ማሰባሰብ ተችሏል።

በአውሮፓውያኑ 2014 ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ ሂውማኒቲ ዩናይትድ ለተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራት ጀመረ።

ይህ ድርጅት ዝቅተኛ ደሞዝ ለሚከፈላቸው ስደተኛ ሠራተኞች ጥቅምን ለማስከበር የሚንቀሳቀስ ነው።

"በወረቀት ላይ የሰፈሩ መብቶች አሉ። ነገር ግን መሬት ላይ ያለው እውነታ ስደተኛ ሠራተኞች ምንም ዓይነት ድጋፍ የላቸውም" ይላል።

በተለይም በያዝነው ዓመት መጨረሻ የእግር ኳስ ዋንጫን የሚያስተናግደውን የኳታር የሚያብረቀርቁ ስታዲየሞችን ምስሎች ባየ ቁጥር ልቡ በሐዘን ይሞላል።

"6,500 ሠራተኞች ስታዲየሞቹን ሲገነቡ እንደሞቱ የዜና ዘገባ ያሳያል። ከኒውዮርክ፣ ለንደን ወይም ሲድኒ ቢሆኑ አገሮቻቸው ምን ምላሽ ይሰጡ ነበር? መሪዎቻችን ስለዚህ ጉዳይ ለምን መናገር አይችሉም?" በማለትም ይጠይቃል።

ማሄንድራ እንደሚናገረው ብዙ ሠራተኞች በድህነት ምክንያት አደገኛ ሥራዎችን ለመሥራት ይገደዳሉ።

እሱም በዚህ ስላለፈበት በተለያዩ ሴሚናሮች እና ወርክሾፓችም ለሚሰደዱ ሠራተኞች ግንዛቤያቸውን ለመጨመር በርካታ ሥራዎችን ይሠራል።

"ስደተኛ ሠራተኞች እውነተኛ ጀግኖች ናቸው። ነገር ግን ተረስተው ወደ ኋላ ቀርተዋል" የሚለው ማሄንድራ "ይህም ኃይል ስለሌላቸው ነው። ስለዚህ የእኔ ሥራ ድምጻቸውን ማጉላት ነው" በማለትም ያስረዳል።