ወታደራዊ ስምምነትን ተከትሎ የሩሲያ ወታደሮች ኒጀር ገቡ

ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኒጀር ከሩሲያ ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት ካጠናከሩ የሳህል ቀጠና አገራት መካከል አንዷ ናት።

ከምዕራቡ ዓለም ጋር ግንኙነቱን ካቋረጠው የኒጀር ወታደራዊ መንግሥት ጋር የተገባውን አዲስ ስምምነት ተከትሎ በርካታ የሩሲያ የጦር አሰልጣኞች ኒጀር ገቡ።

ወታደሮቹ ዘመናዊ የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓት ይዘው ኒጀር መግባታቸውንም የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ወታደሮቹ የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓቱን በመግጠም አጠቃቀሙን ለኒጀር ጦር ትምህርት ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በሳህል ቀጠና በወታደራዊ መንግሥት ከሚመሩ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ነው።

የኒጀር ወታደራዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ሩሲያውያኑ ወደ አገሪቷ የገቡት ወታደሮችን ለማሰልጠን መሆኑን አርብ ዕለት ተናግረዋል።

አፍሪካ ኮርፕስ ተብሎ የሚጠራው የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን በቴሌግራም ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፣ወታደሮችን እና በጎ ፈቃደኞችን ያካተተ የመጀመሪያው ቡድን ኒጀር መግባቱን ገልጿል።

ከጽሑፉ ጋር በተያያዘው ቪዲዮ ላይም አንድ ወታደር በፈረንሳይኛ ቋንቋ ሲናገር “ እዚህ የመጣነው በአገራቱ መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ለማጎልበት ነው። ለሥልጠና የሚረዱ የተለያዩ ወታደራዊ መሣሪያዎችን ይዘን መጥተናል” ብሏል።

የሩሲያ ወታደራዊ አሰልጣኞች ከጭነት አውሮፕላን ላይ መሣሪያዎችን ሲያወርዱ በኒጀር የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያም ታይተዋል።

ስለ ዲሞክራሲ በሚያቀነቅነው ኮንራድ አድኔር ፋውንዴሽን የሳህል ቀጠና ባለሙያ የሆኑት ኡልፍ ሌሲንግ፣ “የጦር መሣሪያ አቅርቦቱ አገዛዙ ዕድሜውን የሚያራዝምበት አንዱ መንገድ ይመስላል” ሲሉ ለቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ኒውስደይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት የኒጀሩ ፕሬዚደንት መሐመድ ባዙም በወታደሮች በተፈፀመ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት ባለፈው ዓመት ነበር።

ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ አገዛዝም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አገሪቷ ከቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያቋረጠ ሲሆን ከአሜሪካ ጋር የነበረውን ስምምነትም አንስቷል።

የአውሮፓ ሕብረትም መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ ከአገሪቷ ጋር ያለውን የጸጥታ ትብብር አቋርጧል።

ሌሲንግ እንደሚሉት ወታደራዊ መንግሥቱ፣ ኢኮዋስ ተብሎ የሚጠራው የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) በኒጀር ጣልቃ ይገባል ብሎ አሁንም ይሰጋል።

ሩሲያ የአየር መከላከያ ያቀረበችላት ምክንያቱም እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖችን ለመዋጋት ከመርዳት ይልቅ ለዚህ ይመስላል ብለዋል ባለሙያው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቤከን የጸጥታ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ካቢር አዳሙ ኒጀር ከምዕራባውያኑ አገራት ውጭ ሩሲያ፣ ቻይና እና ኢራንን ጨምሮ ከሌሎች አገራት ጋር ግንኙነት እየፈጠረች ነው ብለዋል።

ከሩሲያ ጋር ያላት ጥምረትም በማሊ እንደሆነው ሁሉ ወታደራዊ መንግሥቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንዳይሸጋገር ሊያበረታታ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በኢኮዋስ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር የሆኑት አብደል ፋታህ ሙሳ በበኩላቸው ኒጀር የማሊንና የቡርኪና ፋሶን ፈለግ እየተከተለች እንደሆነ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ሦስቱ አገራት የጦር ትብብር ስምምነትም መስርተዋል።

ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶን እና ማሊም ጭምር ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመለሱ ሲያሳስብ ከቆየው ኢኮዋስ አባልነት ታግዳለች።

በወታደራዊ መንግሥት የሚመሩት አገራቱ ጥር ወር ላይ ከቡድኑ አባልነት እንደሚወጡም አሳውቀዋል።

ኮሚሽነሩ በሳህል ቀጠና ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ግጭት እንዳይፈጠር ስጋታቸውን ገልጸዋል።

“ አቋማችን ግልጽ ነው።ለሚፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አገራቱን ተጠያቂ እናደርጋለን” ብለዋል። ኮሚሽነሩ።

“ምንም እንኳን ሉዓላዊ አገራቱ አጋራቸውን የመምረጥ መብት ቢኖራቸውም በቀጠናው ያሉ አገራት በአፍሪካ ሌላ የውክልና ጦርነት እንዳያመቻቹ እናሳስባለን።” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኒጀር በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች የሚፈፀመው ጥቃት እየጨመረ ሲሆን ከናይጀሪያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎችም ስጋት አለባት።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከማሊ ጋር አዋሳኝ በሆነችው ቲላቤሪ ክልል በተፈፀመ የቦምብ ፍንዳታ ቢያንስ ስድስት ወታደሮች ተገድለዋል።

የኒጀር መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱ መፈፀሙን አረጋግጦ፣ የጦሩ የቅኝት ተሽከርካሪ በደቡብ ምዕራብ በምትገኘው ቲንጋራ መንደር አቅራቢያ የተቀበረ ፈንጅን በመምታቱ የተወሰኑ ወታደሮች ተገድለዋል፤ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ብሏል።

ሚኒስቴሩ ጨምሮም ፈንጅ ከሚቀብሩት አካላት አካባቢውን ነጻ ለማውጣት የአየር ድብደባ ማካሄዱን ገልጿል።

ወታደራዊ መንግሥቱ በኒጀር ላለው የጸጥታ ሁኔታ መባባስ ከመፈንቅለ መንግሥትጋር የተያያዘ እንደሆነ ቢጠቅስም፤ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ቲላቤሪ ክልል በሰርጎ ገቦች የሚፈፀሙ ጥቃቶች መቀጠላቸውን ሪፖርቶች አመልክተዋል።