ሩሲያ በኒጀር ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት በተካሄደባት ምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር የሚደረግ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት “ለማያባራ ፍጥጫ ይዳርጋል” ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች።
የምዕራብ አፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) የኒጀርን ፕሬዚዳንት በኃይል እመልሳለሁ ማለቱንም ተከትሎ ነው ሩሲያ ይህንን ያለችው።
እንዲህ ያለው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ኒጀርን ጨምሮ የሳህልን ቀጠና በአጠቃላይ አለመረጋጋት ውስጥ እንደሚያስገባውም ነው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የገለጸው።
ሩሲያ መፈንቅለ መንግሥቱን በይፋ አልደገፈችም።
ከሥልጣን የተገረሰሱት የኒጀር ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙምን ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት እየደገፈች ያለችው አሜሪካ፣ የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር የኒጀርን አለመረጋጋት እየተጠቀመበት ነው ብላለች።
አርብ ዕለት በርካታ የመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎች በመዲናዋ ኒያሚ አቅራቢያ በሚገኝ የፈረንሳይ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
አንዳንዶች በአደባባዮች ላይ የሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ የነበረ ሲሆን ፈረንሳይንና ኢኮዋስንም ሲሳደቡ ተሰምተዋል።
ፈረንሳይ እና አሜሪካ በኒጀር የጦር ካምፖች ያላቸው ሲሆን በሳህል ቀጠና ጽንፈኞችን እንዋጋለን በሚሉት ዘመቻም መነሻ ሆነው አገልግለዋል።
ከኢኮዋስ አባል አገራት የተውጣጡ ወታደራዊ ባለስልጣናት በኒጀር ለሚደረገው ጣልቃ ገብነት እቅድ ለመንደፍ ቅዳሜ ነሐሴ 6/2015 ይመክራሉ ተብሏል።
ኢኮዋስ ለቀውሱ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለመፈለግ አሁንም ክፍት እንደሆነ ገልጿል።
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኒዩ በበኩላቸው ሐሙስ እለት በሰጡት መግለጫ ቀውሱን ለመፍታት የትኛውንም አማራጭ እንደሚወሰድ ተናግረው፣ በኃይል ጣልቃ መግባት የመጨረሻ እርምጃ እንደሆነም ተናግረዋል።
አሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን በግልጽ ባትደግፍም ነገር ግን የኒጀር ወታደራዊ ኃይል ሥልጣኑን ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት እንዲያስረክብና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ጠይቃለች።
ኒጀርን እያስተዳደረ ያለው ወታደራዊ ኃይል በቅርቡ የኢኮዋስ መሪዎች በሰጡት መግለጫ ላይ አስተያየት አልሰጠም።
የኒጀር ወታደራዊ ኃይል ከሦስት ሳምንት በፊት ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ መሃመድ ባዙም በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን የእርሳቸውም ጤና እና ደህንነት ስጋትም እየጨመረ ነው ተብሏል። እርሳቸውና ቤተሰባቸው “ለበርካታ ቀናት የምግብ፣ የኤሌክትሪክ እና የሕክምና አገልግሎት ተነፍገው ነበር” ሲሉም የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ የሆኑት ጆሴፕ ቦሬል ተናግረዋል።












