የኒጀር አጎራባች አገራት መፈንቅለ መንግሥቱ እንዳይኮላሽ አስጠነቀቁ

የኒጀር ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የኒጀር አጎራባች አገራት ቡርኪናፋሶ እና ማሊ በኒጀር የተከሰተው መፈንቅለ መንግሥት የሚኮላሽ ከሆነ ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ አስጠነቀቁ።

በኒጀር ውስጥ ሊደረግ የሚችል ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በአጎራባች አገራቱ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው ሲሉም የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

በጊኒ የሚገኘው መፈንቅለ መንግሥቱን ያስነሳው ወታደራዊ ጁንታም የአገራቱን ጥሪ ተቀላቅሏል።

የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ሃገራት (ኢኮዋስ) በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን የተወገዱትን የኒጀር ተመራጩን ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙምን ወደ ስልጣን ለመመለስ ሃይል እንደሚጠቀም መዛቱንም ተከትሎ ነው የአገራቱ መግለጫ የተሰማው።

ቡርኪናፋሶ እና ማሊ ኢኮዋስ አደርገዋለሁ ካለው ኃይል መጠቀምን ዝም ብለው እንደማያዩና ጎረቤታቸውንም ደግፈው እንደሚከላከሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከኢኮዋስ አባልነታቸውም እንወጣለን ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙም በክቡር ዘብ መሪያቸው ጄነራል አብዱራህማኔ ቺያኒ ወይም በተለምዶ ኦማር ቺያኒ በተመራ መፈንቅለ መንግሥት ከስልጣናቸው ተነስተዋል።

የቀድሞው የፕሬዚዳንቱ ክቡር ዘብ መሪ የኒጀር አዲሱ መሪ መሆናቸውን አውጀዋል።

ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙም ኒጀር ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በጎሮጎሳውያኑ 1960 ነጻ ከወጣች በኋላ የአገሪቷን መሪ እንዲተኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡ መሪ ናቸው።

በአካባቢው ከሚገኙ ጽንፈኛ ታጣቂዎች ጋር በሚደረገው ውጊያም ምዕራባውያኑ እንደ ቁልፍ አጋር ይቆጥሯቸዋል።

መፈንቅለ መንግሥቱ በአፍሪካ ህብረት፣ የምዕራብ አፍሪካ ቀጠናዊ ቡድን (ኢኮዋስ)፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በአለም አቀፍ አካላት ሙሉ በሙሉ ተወግዟል።

በወታደራዊ አመራር የሚመሩ የሁለቱ አገራት ማስጠንቀቂያ የቀጣናውን የጸጥታ ስጋት ሁኔታ ሊያባብስ የሚችል ከፍተኛ ስጋትን አጭሯል።

እንዲህ ያለው የኢኮዋስ እርምጃ አስከፊና አለመረጋጋትንም እንደሚያስከትል አገራቱ አስታውቀዋል።

ሁለቱም አገራት ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠው ከሩሲያ ጋር አጋርነት መስርተዋል።

እንደ ኒጀር በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የተገዙት ቡርኪናፋሶ እና ማሊ በሳህል ውስጥ ያሉ ጽንፈኞችን እየተዋጉም ቆይተዋል።

በቡርኪናፋሶ እና ማሊ ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥት መደረጉ የሚታወስ ሲሆን በኒጀርም ተመሳሳይ ሁነት መከናወኑ የሳህልን ቀጠና የበለጠ አደጋ ውስጥ ከቶታል።