አፍሪካዊያን ወጣቶችን መፈንቅለ መንግሥት ለምን ያስፈነድቃቸዋል?

ሰዎች ደስታቸውን ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሰዎች ደስታቸውን ሲገልጹ

የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ገና 5ኛ ሳምንቱን ሳይደፍን ጋቦን ተከተለች።

የኒጀሩ ፕሬዝዳንት መሐመድ ባዙም ዛሬም የቁም እስረኛ ናቸው። የጋቦኑ አሊ ቦንጎም የቁም እስረኛ ሆነዋል።

“ወገኖቼ ድረሱልኝ! ድምጽ ሁኑኝ!” ሲሉ የተማጸኑበት ቪዲዮ ጋቦናዊያን ወጣቶችን ከማስገረም አልፎ አበሳጭቷቸዋል።

የአፍሪካ ወጣቶች ነጭ ጸጉር እስኪያበቅሉ ድረስ በዙፋናቸው የተወዘፉ አምባገነኖችን በእጅጉ ይጸየፋሉ። አሊ ቦንጎና ቤተሰባቸው ጋቦንን እንደግል ንብረታቸው ነበር የሚቆጥሯት።

ቅንጡ አፓርትመንቶችን በፓሪስ እየገዙ፣ ቁጥር ስፍር የሌለው ሃብት እያሸሹ በርካታ ጋቦናዊያን ግን በሥራ አጥነት ሲንከላወሱ ወጣትነታቸው አልፏል።

ጋቦን ነዳጅ አላት። ጠቅላላ የሕዝብ ብዛቷ 2 ሚሊዮን ተኩል ነው። ሕዝቧ የአገሪቱን ሃብት በፍትሐዊነት ቢካፈለው ምናልባት የነጣ ድሃ በዚያች አገር ባልኖረ ነበር።

ጋቦናዊያን ወጣቶች በቦንጎ ቤተሰብ ተሰላችተዋል። ጎልማሶች ዕድሜ ዘመናቸውን ከቦንጎ ቤተሰብ ሌላ አያውቁም።

አሊ ቦንጎ ምርጫ አሸንፈዋል የሚል ዜና ረቡዕ ዕለት ተላለፈ። ከደቂቃዎች በኋላ ስምንት ወታደሮች በቴሌቪዥን ቀርበው የቦንጎ ዘመን ማብቃቱን አበሰሩ።

የጋቦን ወጣቶች ሆ ብለው አደባባይ ለመውጣት ደቂቃ አልወሰደባቸውም።

አሊ ቦንጎ በሆነው ነገር ፍጹም ግራ መጋባታቸውን በዚያ በቁም እስር ሆነው በለቀቁት ‘የድረሱልኝ’ ጥሪ ተናግረዋል።

ምናልባት አገሪቱ ርስታቸው እንደሆነች ስላሰቡ ይሆን መገረማቸው?

የኒጀሩ መሐመድ ባዙም መካከለኛውና ምዕራብ አፍሪካን መፈንቅለ መንግሥት ይንጣታል ብለው ተንብየው ነበር።

አልተሳሳቱም።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ጥር የቡርኪና ፋሶው ሮች ማርክ ክርስቲያን ካቦሬ በተመሳሳይ ተነሱ። ከ 8 ወር በኋላ መፈንቅለ መንግሥት የመራው ሰው ራሱ በመፈንቅለ መንግሥት ተነሳ።

የስዒረ መንግሥቱ አዙሪት ቀጥሏል።

ከ2021 ዓ/ም በፊት ደግሞ በማሊ መፈንቅለ መንግሥት ነበር። ኮሎኔል አሲም ጎይታ ነበር የመራው። የማሊ ወጣቶች ደስታቸው ወደር አልነበረውም።

በዚያው ዓመት መስከረም የጊኒ ልዩ ኃይል ወደ ኮናክሪ ቤተ መንግሥት አቀና። ፕሬዝዳንት አልፋ ኮናሬን ሊፈነቅል። ወጣቶች ደስታቸው ገደብ አልነበረውም።

በቻድም ተመሳሳይ ነገር ሆኖ ነበር።

በፈረንሳይ ቅኝ ተገዢዎች ዘንድ መፈንቅለ መንግሥት ለምን በረታ?

ከስድስት ዓመት በፊት የጋምቢያው ተሸናፊ መሪ ያህያ ጃሚህ ተገደው ሲሰደዱ ምዕራብ አፍሪካ ወደ ብዙ ፓርቲ ሥርዓት መሸጋገሯ እንደሆነ ታምኖ ነበር።

ያህያ ጃሚህ ከሥልጣን ሲወገዱ ከ60ዎቹና ከ70ዎቹ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አፍሪካ ወደ ዲሞክራሲ እየተሸጋገረች እንደሆነ ብዙዎች አምነው ነበር።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን ነገሩ መልሶ አገረሸ።

ወታደሮች ወደ ቤተ መንግሥት አቅንተው መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ የልብ ልብ የሚሰጣቸው የሕዝባቸው ተስፋ አልባ ሕይወት ነው። በተለይ ወጣቶች መፈንቅለ መንግሥቱን እንደሚደግፉ ያውቃሉ። ምክንያቱም ተስፋ ያጡ ወጣቶች ለውጥን ይሻሉ።

በምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ ወጣቶች ዕድሜያቸውን ያለ ሥራ፣ አእምሯቸው ያለ ተስፋ እያሳለፉ መቆዘም ትክት ብሏቸዋል።

በማሊ መፈንቅለ መንግሥት ብዙ ወጣቶች ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በማሊ መፈንቅለ መንግሥት ብዙ ወጣቶች ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር

እንኳንስ በአምባገነኖች በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን በያዙ መሪዎቻቸው ራሱ ደስተኛ አይደሉም።

ምክንያቱም ወጣቶች የሚሹትን ለውጥ በአገራቸው ማየት አለመቻላቸው ነው። አሁን ወጣቶች ተስፋን ማየት ይሻሉ። ሕይወታቸው ቶሎ እንዲለወጥ ይጓጓሉ። መሪዎቻቸው ይህን ሊያሳኩ አይፈቅዱም ወይም አይችሉም።

ወጣቶች በባለሥልጣናት የሚዘረፈውን ሃብት ይመለከታሉ። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ከኮሌጆች ተመርቀው ሥራ ሳያገኙ ዓመታት ይንከራተታሉ።

አሁን ያሉ ወጣቶች ዓለም ላይ ምን እየሆነ እንዳለ መረጃ የሚያገኙበት ፍጥነት አስገራሚ ነው። በሌላው ዓለም ያሉ እኩዮቻቸው ምን እንዳሳኩ ይረዳሉ። አገራቸው ለነርሱ ቦታ እንደሌላት ሲረዱ ከቻሉ ይሰደዳሉ፤ ካልቻሉ ግን ቂም አርግዘው ነው የሚቀመጡት።

ይህን ሊለውጥ የሚችል ማንኛውም አገሪቱ ላይ የሚታይ ፖለቲካዊ ለውጥ ያስደስታቸዋል። ተስፋቸውን ያለመልመዋል።

የጋቦን ወጣቶች ከ14 ዓመት በፊት አሊ ቦንጎ ለምርጫ ሲቀርቡ ተስፋ ያደረጉት ሌላ ነበር።

ያኔ አባታቸው ኦማር ቦንጎ ሲሞቱ አሊ ቦንጎ ለሕዝባቸው ተስፋ ሰጡ። ያኔ ወጣት የነበሩት ጋቦናዊያን አንድም ለውጥ ሳይመለከቱ ከወጣትነታቸው ተሰናበቱ።

ኦማር ቦንጎ ለ40 ዓመታት አገሪቱን ሲመሩ ሁለት ትውልድ ወጣቶች ተስፋቸው ሳይለመልም ነው ዕድሜያቸው ያለፈው።

አሊ ቦንጎ ከአራት ዓመት በፊት በስትሮክ በመመታታቸው ጤናቸውም ለመሪነት የሚያበቃ አልነበረም።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአፍሪካ የተደረጉ መፈንቅለ መንግሥት
የምስሉ መግለጫ, ባለፉት ሦስት ዓመታት በአፍሪካ የተደረጉ መፈንቅለ መንግሥት

አሊ ቦንጎ አባታቸው ተክተው የመጡ የመጀመርያው ዓመታት የተስፋ ጭላንጭል ታይቶ ነበር። አገሪቱን ለማዘመን ያደረጉት ጥረት፣ ማኅበራዊ ፍትሕን እና እኩልነት ለማረጋገጥ፣ የአገሪቱን ደን እና ብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅ ተፍ ተፍ ማለታቸው ተወዶላቸው ነበር። ይህ ግን ብዙ ዓመት አልዘለቀም።

አሊ ቦንጎ ምርጫ በደረሰ ቁጥር ገለልተኛና ተአማኒ ምርጫ ለማድረግ አለመፍቀዳቸው ሕዝባቸውን አስቆጣ።

ተቃዋሚያቸው አንድሬ እምባ ኦባሜ በ2009 ዓ/ም አሊ ቦንጎን እንደረቷቸው ብዙ ሕዝብ ያውቃል። ነገር ግን እኔ ነኝ ያሸነፍኩት ብለው በሥልጣን ቆዩ።

በቅርብ በተደረገው ምርጫም ቦንጎ 64% ድምጽ አግኝቻለው ቢሉም ሕዝባቸው በተለይም ወጣቱ ይህ እውነት እንዳልሆነ አሳምሮ ያውቃል።

የጋቦን ወጣት ይህ ነገር እስከመቼ ነው የሚቀጥለው እያለ በሚብሰለሰልበት ሰዓት ነው ወታደራዊ መኮንኖች በቴሌቪዥን ከተፍ ብለው የቦንጎ ሥርወ መንግሥት ማብቃቱን ያበሰሩት።

የጋቦን ወጣት ወደ አደባባዮች ተመመ። በመንገድ ላይ ወታደሮቸን እያቀፈ አገላብጦ ሳመ። ነገ የተሻለ ይሆናል በሚል ተስፋ።

ታሪክ እንደሚነግረን ግን ወታደሮች በመፈንቅለ መንግሥት መጥተው ዲሞክራሲን፣ ፍትሕን እኩልነትን እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ሲያረጋግጡ ታይቶ አይታወቅም።

የአፍሪካ ወጣቶች ደስታቸው፣ መፈንደቃቸው ለውጥን ከመሻት ብቻ ነው። ስለነገ ነገ ያውቃል።