ኒጀር፡ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ‘በተጠንቀቅ የሚጠብቅ’ ጦር ለማቀናጀት ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወደ ኒጀር ጦር ለመላክ የተስማሙት የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት “በአስፈላጊው ጊዜ” የሚዘምት ጦር ለማቀናጀት መነጋገራቸውን የአይቮሪ ኮስት ፕሬዝደንት ገለጡ።
ኤኮዋስ የተሰኘው ቀጣናዊ ድርጅት አባላት የሆኑት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ስብሰባቸውን ሲያጠናቅቁ “በተጠንቀቅ የሚጠብቅ” ጦር ለማሰናዳት ተስማምተዋል።
የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ቦላ ቲኑቡ የጦር ኃይል መጠቀም “የመጨረሻው አማራጭ ይሆናል” ብለዋል።
በኒጀር ወታደራዊ ጁንታ መፈንቅለ መንግሥት ፈጽሞ ሥልጣን የያዘው ሐምሌ 19 ነበር።
ዩናይትድ ስቴትስና የተባበሩት መንግሥት ከሥልጣን ተወግደው ከሁለት ሳምንት በላይ በቁም እሥር ላይ የሚገኙት የፕሬዝደንት ሞሐመድ ባዙም ደኅንነት አሳስቦናል እያሉ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ዋን ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የቀድሞው ፕሬዝደንት ባዙም እና ቤተሰቦቻቸው “አስከፊ በሆነ ሁኔታ” ውስጥ በመሆናቸው ስጋታቸውን ገልጠዋል።
የአይቮሪ ኮስቱ መሪ አላሳኔ ኦዋታራ ከኤኮዋስ ስብሰባ በኋላ ከዚህ ቀድም ይህ ቀጣናዊ ድርጅት በአፍሪካ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ለማስፈን ተሰማርቶ እንደነበር አውስተዋል።
“ዛሬ ተመሳሳይ ነገር ኒጀር ውስጥ ገጥሞናል። እኔ መናገር የምፈልገው ኤኮዋስ ይህንን እንደማይፈቅድ ነው” ብለዋል።
የአይቮሪ ኮስቱ ፕሬዝደንት እንደሚሉት ሃገራቸው ከ850 እስከ 1100 የሚሆን ጦር ታዋጣለች፤ ናይጄሪያ እና ቤኒንም እንዲሁ ወታደሮች ያዋጣሉ።
የኤኮዋስ ፕሬዝደንት የሆኑት ኦማር ቱሬ የሕብረቱ አባላት “በኒጀር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን በተጠንቀቅ የሚጠብቅ ጦር ለማቀናጀት ከስምምነት ደርሰዋል” ይላሉ።
ይህ በተንጠቀቅ ይጠብቃል የተባለው ጦር ምን ዓይነት መልክ እንደሚኖረውና ምን ዓይነት ተግባር እንደሚፈፅም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጠበዋል።
ከስብሰባው በፊት ናይጄሪያና ኒጀር በሚዋሰኑበት የሰሜን ናይጄሪያ ክፍል ያሉ ሙስሊም አባቶች ፕሬዝደንት ቲኑቡ የመፈንቅለ-መንግሥቱ መሪዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዳይወስዱ ተማፅነዋል።
ነገር ግን ከስብሰባው በኋላ የናይጄሪያው መሪ “ሁሉንም አማራጭ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠናል። ኃይል መጠቀም የመጨረሻው አማራጭ ቢሆንም ከምርጫው መሐል አለ” ብለዋል።
“እኛ ካላደረግነው፤ ማንም ሊያደርግልን አይችልም።” ብለዋል ቲኑቡ።
የመፈንቅለ-መንግሥቱ መሪዎች ማንኛውም ዓይነት ወረራ ቢካሄድባቸው ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጠዋል።
ኤኮዋስ ባለፈው እሑድ ድረስ የፀና ቀን-ገደብ ለወታደራዊው ጁንታ ሰጥቶ ኒጀር ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንድትመለስ ቢጠይቅም ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
የኒጀር ወታደራዊው ጁንታ እንደውም አዲስ ካቢኔ ማቋቋሙን ይፋ አድርጓል።
አሜሪካ እና ፈረንሳይ ኒጀር ውስጥ ወታደራዊ መቀመጫ አላቸው። እኚህ የጦር ሰፈሮች የተቋቋሙት በቀጣናው ያለውን ጂሃዳዊ እንቅስቃሴ ለመመከት ነው።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከቀናት በፊት “በኒጀር ያለውን አለመረጋጋት የሩሲያው ቫግነር ቡድን እንደ አጋጣሚ እየተጠቀመው ሳይሆን አይቀርም” ሲሉ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።












