አገራት ባፋጠጠው የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ዋነኛ ተዋናዮች እነማን ናቸው?

የኒጀር ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም እና የመፈንቅለ መንግሥት መሪው ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ
የምስሉ መግለጫ, የኒጀር ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም እና የመፈንቅለ መንግሥት መሪው ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ

የኒጀር ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም በመፈንቅለ መንግሥት መሪው ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ ከሥልጣናቸው መወገዳቸው ምዕራብ አፍሪካን ቀጠናዊ ቀውስ ውስጥ ከትቷል።

በቀጠናው በሌላ በወታደራዊ ሁንታ የሚመራ ቡድን መመሥረት በቀጠናው ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኖች እንዳሻቸው እንዲንቀሳቀሱ ሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ይህ መፈንቅለ መንግሥት ከኒጀር እና ከቀጠናው ባሻገር የዓለም ትኩረትን ስቧል። ምዕራባውያን መፈንቅለ መንግሥቱን አጥበቀው ተቃውመዋል።

ለመሆኑ በዚህ መፈንቅለ መንግሥት ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮች እነ ማን ናቸው? በኒጀር የተፈጸመው መፈንቅ መንግሥት ለቀጠናውስ ምን ማለት ነው?

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ

ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ

መፈንቅለ መንግሥቱን የመሩት የ62 ዓመት የጦር ጄኔራል ናቸው። ቺያኒ ከእአአ 2011 ጀምሮ የፕሬዝዳንታዊ የክብር ዘብ ጥበቃ አዛዥ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ከቀድሞ ፕሬዝዳንት መሐመዱ ኢሶፉ ጋር የቀረበ ወዳጅነት አላቸው።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ጄኔራል ቺያኒ እራሳቸውን የኒጀር ወታደራዊ መንግሥት መሪ አድርገው ሾመዋል።

ስለ ቺያኒ የግል ሕይወት፣ የትምህር ደረጃ እና ወታደራዊ ዕድገት በይፋ የሚታጠቀው በጣም ትንሽ ነው። ይሁን እንጂ ግለሰቡ እአአ 2015 በቀድሞ ፕሬዝዳንት መሐመዱ ኢሶፉ ላይ በተመኮረው መፈንቅ መንግሥት ስማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ ነበር።

በእአአ 2018 ፍርድ ቤት ቀርበው በመፈንቅ መንግሥቱ ሙከራ ላይ ምንም አይነት ተሳትፎ የላቸውም ተብለው በነጻ ተሰናብተዋል።

ዘንድሮ የፕሬዝዳንት ባዙምን መንግሥት በኃይል ከገለበጡ በኋላ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው የሚመሩት ጦር የቀድሞ ሲቪል አስተዳደርን ወደ ሥልጣን ለለመስ ለሚደረገው ቀጠናዊ ጫና እንደማይንበረከክ ተናግረዋል።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ
የምስሉ መግለጫ, የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ

ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም

ፕሬዝዳንት ባዙም የቀድሞ የኒጀር መሪ መሐመዱ ኢሶፉን በመተካት ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥልጣን የያዙት እአአ 2021 ላይ ነበር።

ጸንፈኛ እስላማዊ ቡድኖችን በቀጠናው በመዋጋት የምዕራባውያን አጋር የነበሩት ባዙም ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም. በወታደራዊ ቡድን ከሥልጣን በኃይል እንዲነሱ ተደርገዋል።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ባዙም በመዲናዋ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የቁም እስረኛ ሆነው እንደሚገኙ ይታመናል።

የባዙም አስተዳደር በሜዲትራኒያን ባሕር በኩል ወደ አውሮፓ አገራት የሚደረገውን የሰዎች ፍልሰትን ለመግባታት ከምዕራባውያን ጋር አብሮ ይሠራ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ በሊቢያ በእስር ላይ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለመቀበል ከመስማማታቸው በላይ በምዕራብ እና ሰሜን አፍሪካ መካከል ቁልፍ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በሚፈጸምባቸው ስፍራዎች በአዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ ለመወሰድ አስተዳደራቸው ጥረት አድርጓል።

አሁን ላይ የባዙም አስተዳደር በመወገዱ ጸንፈኛ እስላማዊ ቡድኖችን መዋጋት እና የሰደተኞችን ፍልሰት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ቆሟል ማለት ይቻላል።

መፈንቅለ መንግሥት የተደረገባቸው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም
የምስሉ መግለጫ, መፈንቅለ መንግሥት የተደረገባቸው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም
የኒጀር ጦር

የኒጀር ጦር

የኒጀር ጦር የፕሬዝዳንቱን መፈንቅለ መንግሥት ደግፏል። በኒጀር የደኅንነት ስጋት ተንሰራፍቷል፣ ድህነት ስር ሰዷል፣ እንዲሁም አስተዳደሩ ተዳክሟል በሚሉ ምክንያቶች ነው የፕሬዝዳንቱን መወገድ ጦሩ በአዎንታዊ መልኩ የተመለከተው።

ጦሩ ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ጣልቃ ገብነትን ቀድሞ ተቃውሟል።

ከፍተኛ የአገሪቱ ጦር አባላት በአሁኑ ወቅት አገሪቱን የሚያስተዳድር “አባት አገርን የሚጠብቅ ብሔራዊ ምክር ቤት” የሚል ተቋም አቋቁመዋል።

የኤም62 ንቅናቄ

በኒጀር ኤም62 የተባለ ሲቪል ማኅበር አለ። ይህ የሲቪል እንቅስቃሴ ፀረ-ፈረንሳይ የተቃውሞ ሰልፎችን በማስተባበር ይታወቃል።

ፕሬዝዳንት ባዙም ሥልጣን ላይ ሳሉ ከማሊ የተባረረው የፈረንሳይ ጦር በኒጀር ዳግም እንዲሰማራ መፍቀዳቸውን በመቃወም ሰፊ የተቃውሞ ሰልፍ አድርጎ ነበር።

ኤም62 በኒጀር የተወገዘ ማኅበር ከመደረጉም በላይ ማኅበሩ መሪ የሕዝብ ሰላምን በማወክ በሚል ለእስር ተዳርገው ነበር።

አሁን በፕሬዝዳንት ባዙም ላይ መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙን ተከትሎ ማኅበሩ ማንሰራራት ጀምሯል። በቅርቡም ከአገሪቱን ጦር ጎን በመሰለፍ መፈንቅለ መንግሥቱን የሚደግፉ ሰልፎችን እያስተባበረ ይገኛል።

ኤኮዋስ

ጎረቤት አገራት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቡርኪና ፋሶ

የኒጀር ጎረቤት የሆነችው ቡርኪና ፋሶ በ2022 ብቻ ሁለት መፈንቅለ መንግሥቶችን አስተናግዳለች።

በቡርኪና ፋሶ ያሉ የጦር መሪዎች ለኒጀር ጦር ድጋፋቸውን ገልጸዋል። የቡርኪና ፋሶ ጦር መሪዎች በኒጀር መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መፈጸም “በቡርኪና ፋሶ ላይ ጦርነት እንደ ማወጅ ይቆጠራል” ብለዋል።

በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ ያለው የቡርኪና ፋሶ መንግሥት ፊቱን ወደ ሩሲያ ያዞረ ሲሆን፣ ምዕራባውያን እና አንዳንድ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ኒጀር ላይ ለመተግባር ያሰቡትን ሕጋዊ ያልሆነ ማዕቀብ አጥብቄ እቃወማለሁ ብሏል።

ማሊ

ጎረቤት አገር ማሊ በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶባታል። በማሊ ያለው ወታደራዊ ቡድንም ከቡርኪና ፋሶ ጋር በመሆን በኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ለፈጸሙት ወታደሮች ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

ልክ እንደ ቡርኪና ፋሶ ሁሉ በማሊ ያለው ወታደራዊ መንግሥትም በኒጀር ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መፈጸም “በማሊ ላይ ጦርነት እንደ ማወጅ ይቆጠራል” ሲል አስጠንቅቋል።

የማሊ ጦር ጄኔራሎች ኒጀር ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ቢፈጸም ቀጠናውን ቀውስ ውስጥ ይከታል ሲሉ ማስፈራሪያ አዘል ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።

ልክ እንደ ቡርኪና ፋሶ ሁሉ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ የወጣው የማሊ ጦር በሩሲያ የሚደግፍ ነው።

ቻድ

ቻድ የኢኮዋስ አባል አይደለችም ነገር ግን የኒጀር ጎረቤት ነች። ቻድ በኒጀር ላይ ወታደራዊ ጣል ገብነት አያስፈልግም የሚል አቋም ይዛለች። የቻድ መከላከያ ሚኒስትር አገራችን በኒጀር ላይ ጣልቃ ለመግባት ምንም አይነት ዕቅድ የላትም ብለዋል።

ይሁን እንጂ ቻድ ጁንታው ቡድን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለተመረጡት ፕሬዝዳንት ባዙም ሥልጣን መልሶ እንዲያስረክብ በፕሬዝዳንቷ በኩል ጥያቄ አቅርባለች።

የኒጀሩ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዞም (ከቀኝ) እና ከቻድ ፕሬዝዳንት ማሓማት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ (ከግራ)
የምስሉ መግለጫ, የኒጀሩ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዞም (ከቀኝ) እና ከቻድ ፕሬዝዳንት ማሓማት ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ (ከግራ) በኒጀር ፕሬዝዳንታዊ ቤተመንግሥት ውስጥ

ናይጄሪያ

የናይጄሪያው አዲሱ ፕሬዝዳንት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ቀጠናዊ ድርጅት የሆነው ኤኮዋስ ሰብሳቢ ናቸው። ናይጄሪያ ከኒጀር ጋር 1500 ኪሎ ሜትር ድንበር እንደመጋራቷ በጎረቤት አገር የሚሆነው ለደኅንነቷ ስጋት ነው።

ለአዲሱ ፕሬዝዳንትም የኒጀር ጉዳይ የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ፈተናቸው ሆኗል ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ በኒጀር መፈንቅለ መንግሥት እንደተፈጸመ በፍጥነት የኤኮዋስ መሪዎችን በፕሬዝዳንታዊ ቪላቸው ስብሰባ ጠርተው ነበር።

ኢኮዋስም መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹ በፍጥነት ሥልጣን ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ባዙም እንዲያስረክቡ አልያም ወታደራዊ ጣል ገብነት እንደሚኖር አሳስበዋል።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት የአገሪቱን ጦር ወደ ኒጀር ለመላክ ፍላጎት ቢያሳዩም በአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

ይሁን እንጂ ቲኑቡ አገራቸው ወደ ኒጀር ትልክ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቋረጥ የኢኮዋስን የምጣኔ ሃብት ማዕቀብ ተፈጻሚ አድርገዋል።

ኤኮዋስ

የምዕራብ አፍሪካ ምጣኔ ሃብታዊ ማኅበረሰብ የተባለው ቀጠናዊው ተቋም ኤኮዋስ መፈንቅለ መንግሥቱን አጥበቆ ተቃውሟል።

የኢኮዋስ አባል አገራት ወታደራዊው ቡድን ሥልጣን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለፕሬዝዳንት ባዙም ካለስረከበ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ይከተላል ሲል አስጠንቅቆ ነበር።

ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኬፕ ቬርዴ፣ ኮት ዲቯር፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳዎ፣ ላይቤሪያ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሴራ ሊዮን እና ቶጎን በአባልነት ያቀፈው ኢኮዋስ ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በቻድ ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

ምዕራባውያን አገራት

ምዕራባዊያን ኃይሎች

ቫግነር ቅጥረኛ ቡድን

የሩሲያው ቅጥረኛ ቡድን ቫግነር መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን የኒጀርን መንግሥት ግልበጣ ድል ነው ሲል በተደጋጋሚ ገልጾታል።

“ኒጀር ውስጥ የተከሰተው ጉዳይ የኒጀር ሕዝብ ከቅኝ ገዢዎች ጋር ያለውን ትግል ማሳያ ነው” ሲል የቫግነር ነው በተባለ የቴሌግራም ገጽ ላይ ተናግሯል።

ነገር ግን ሐሳቡን የሰጠው በእውነትም እሱ ስለመሆኑ በገለልተኛ አካል አልተጠራም።

የቫግነር ቅጥረኛ ወታደሮች በኒጀር ለተከሰተው መፈንቅለ መንግሥት የራሳቸውን አስተዋፅዖ አድርገዋል ተብለው ይወቀሳሉ።

ፕሬዝዳንት ባዙም የቫግነር ቡድን ስለመንግሥታቸው “የተሳሳተ መረጃ አስፋፍቷል” ሲሉ ቅሬታቸውን ከመንግሥት ግልበጣው በፊት አሰምተው ነበር።

ነገር ግን አሜሪካ የቫግነር ቡድን በኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ስለመሳተፉን የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም ትላለች።

የቫግነር አዛዥ የቭጌኔ ፕሪጎዢን
የምስሉ መግለጫ, የቫግነር አዛዥ የቭጌኔ ፕሪጎዢን

ሩሲያ

ክሬምሊን በኒጀር እየሆነ ያለው ነገር “አሳሳቢ ነው” ስትል ሁሉም ወገኖች ውጥረቱን እንዲያረግቡት ጥሪ አቅርባለች።

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛኻሮቫ “ወደ ሲቪል አስተዳደር እና ሰላም ለመመለስ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ብሔራዊ ውይይት ያስፈልጋል” ብለዋል።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎች መካከል አንዳንዶች የሩሲያን ሰንደቅ አላማ ከኒጀር ጋር አብረው ይዘው ታይተዋል።

ምዕራባዊያን ታዛቢዎች አዲሱ የኒጀር አመራር የማሊ እና የቡርኪና ፋሶን ፈለግ ይከተላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይገልጻሉ። የኒጀር ጎረቤት የሆኑት ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ከምዕራባዊያን ይልቅ የሩሲያን አጋርነት ይመርጣሉ።

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን
የምስሉ መግለጫ, የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

ፈረንሳይ

የኒጀር ቅኝ ገዢ የነበረችው ፈረንሳይ 1500 ገደማ ወታደሮች ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ውስጥ አሰማርታ ነበር።

ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ ያጋጠመውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ነው ፈረንሳይ መቀመጫዋን ወደ ኒጀር ያዞረችው።

የመንግሥት ግልበጣውን አጥብቃ የምትቃወመው ፈረንሳይ፣ ፕሬዝዳንት ባዙም የኒጀር ብቸኛው ሕጋዊ መሪ ናቸው፤ አዲሱን ወታደራዊ አመራር በፍጹም አልቀበልም ትላለች።

የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “በኒጀር በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው የሲቪል መንግሥት በፍጥነት ወደ ሥልጣን እንዲመለስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረበውን ጥሪ እንደግፋለን” ብሏል።

የፈረንሳይ መከላካይ ሚኒስትር ሴባስቺየን ሌኮርኑ እንደሚሉት ከአንድ ሺህ በላይ የፈረንሳይ ዜጎች እና ሌሎች አውሮፓውያን ከኒጀር እንዲወጡ ተደርገዋል።

አሜሪካ

የአሜሪካ መንግሥት የኒጀርን መፈንቅለ መንግሥት በእጅጉ እንደሚቃወም ገልጿል። አልፎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊከን ፕሬዝዳንት ባዙም በፍጥነት ከቁም እሥር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

አሜሪካ አንድ ሺህ ገደማ ወታደሮች ኒጀር ውስጥ አሏት። አሜሪካ ወታደሮቿን ከ2013 ጀምሮ በኒጀር ያሰፈረችው በቀጣናው የሚካሄደውን ፀረ-ሽብር እንቅስቃሴ ለመደገፍ ነው።

አሜሪካ የድሮን ጥቃት ለማድረግ በአጋዴዝ ከተማ ካላት የአየር ኃይል ውጭ ሌላ ካምፕ የላትም። አጋዴዝ ደግሞ ከኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ ከ800 ኪሎ ሜትሮች በላይ ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት።

አሜሪካ፤ ኒጀር ከሚገኘው ኤምባሲዋ የተወሰኑ ሠራተኞችን አስወጥታለች።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

ጀርመን

ጀርመን በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ የጦር ሠራዊት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አላት። ጀርመን ላልተወሰነ ጊዜ ለኒጀር ማዕከላዊ መንግሥት ታደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጧን አስታውቃለች።

አልፎም ሁኔታዎች እንዴት እንደሚሄዱ እየተመለከተች ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደምትወስድም አስታውቃለች።

የጀመርን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ኒጀር ውስጥ እየሆነ ያለውን “በቅርበት በአንክሮ” እየተከታተለው እንደሆነ ገልጿል።

ቱርክ

ቱርክ ከኒጀር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፈረንጆቹ 1967 ካቋቋመች በኋላ ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋር ያላትን ግንኙነት ስታጠናክር ቆይታለች።

የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው የቱርክ ኤምባሲ በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ ከተከፈተ ጀምሮ ሁለቱ አገራት 29 የሁለትዮሽ ግንኙነት ስምምነቶችን አድርገዋል።

በፈረንጆቹ 2019 ሁለቱ አገራት ያደረጉት የንግድ ልውውጥ 72 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደደረሰ ሚኒስቴሩ ይናገራል። ቱርክ ለኒጀር እና ለማሊ ድሮኖች እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን አድርጋለች።

በ2021 ኒጀር ከቱርክ ስድስት ባይራክታር የተባሉ ድሮኖችን የተከረበች ሲሆን፣ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው “በወታደራዊው የኒጀር ኃይል የተፈፀመውን የመፈንቅለ መንግሥት በአንክሮ እየተከታተልን ነው” ብሏል።

የተለያዩ ተቋማት

የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒጀርን መፈንቅለ መንግሥት ተቃውመዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የኒጀር ጦር በ15 ቀናት ውስጥ ወደ ጦር ሠፈሩ እንዲመለስ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ በአገሪቱ የሚያከናውናቸውን የደኅንነት እንቅስቃሴዎች ማቋረጡን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኃይል ከመንበራቸው ለተነሱት ፕሬዝዳንት ባዙም ያላቸውን ድጋፍ ገልጸው፣ የኒጀር ወታደራዊ አመራሮች በፍጥነት እንዲለቋቸው ጠይቀዋል።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ