ፈረንሳይ በኒጀር ሕጋዊ ስርዓትን ለመመስለ የሚደረገውን ጥረት እደግፋለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, AP
ፈረንሳይ በኒጀር ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓትን ለመመለስ በቀጣናዊ ድርጅቱ የሚደረገውን ጥረት እድግፋለሁ አለች።
ፈረንሳይ ይህን ያለችው የምዕራብ አፍሪካ አገራት ቀጣናዊ ድርጅት የሆነው ኤኮዋስ በኒጀር መፈንቅለ መንግሥት የፈጸመው ቡድን ስልጣን መልሶ እንዲያስረክብ ያስቀመጥው ቀነ ገደብ በሚጠናቀቅበት ዕለት ነው።
የኒጀሩ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዙም ከቀናት በፊት በወታደራዊ ቡድን ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ ኤኮዋስ፤ ቡድኑ እስከ ዛሬ እሁድ ድረስ መልሶ ስልጣን ካላስረከበ ወታደራዊ አማራጭ ሊጠቀም እንደሚችል ማሳሳቢያ ሰጥቶ ነበር።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ካትሪን ኮሎን ባወጡት መግለጫ የኒጀር እና የመላው የምዕራብ አፍሪካ አገራት የወደፊት እጣ ጥያቄ ላይ ወድቋል ብለዋል።
ፈረንሳይ የኤኮዋስን ጥረት እደግፋለሁ ትበል እንጂ ድጋፏ ወታደራዊ አማራጮችን ስለመጨመሩ ገልጽ አይደለም።
ባለፈው ሐሙስ በኒጀር መፈንቅለ መንግሥት የፈጸሙት የወታደራዊ ቡድኑ አባላት ከቀድሞ የኒጀር ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።
መፈንቅለ መንግሥት ፈጸሚዎቹ በአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቶጎ እና ናይጄሪያ ያሏቸውን አምባሳደሮችም ጠርተዋል።
ጎረቤት አገር ጋና ደግሞ ኒጀር ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንድትመለስ እና የአገሪቱ ዜጎች ከአገሪቱ እድገት እና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲጠቀሙ ለኒጄሪያዊያን “አስፈላጊ የሆነውን ድጋፍ” አደርጋለሁ ብላለች።
ይህ ጋና ለኒጀር ዜጎች አደርገዋለሁ ያላቸው አስፈላጊ ድጋፍ ኤኮዋስ የወጠነውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንደሚጨምር ግልጽ አይደለም።
በአንጻሩ ግን የምዕራብ አፍሪካ አገራት ቀጠናዊ ድርጅት የሆነው ኤኮዋስ አባል የሆኑት አይቮሪ ኮስት እና ሴኔጋል ጦራቸውን ወደ ኒጀር ለማዝመት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ሁለቱ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት አገራት በኒጀር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማስፈን በኢኮዋስ ስር ጦራቸውን ወደ ኒጀር ለመላክ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት የአገሪቱን ጦር ወደ ኒጀር ለመላክ ፍላጎት ቢያሳዩም በአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
የኢኮዋስ አባል አገራት መከላከያ ሚኒስትሮች መፈንቅለ መንግሥት ፈጻሚዎቹ እስከ ዛሬ እሁድ ድረስ ስልጣን ለማስረከብ አሻፈረኝ ካሉ ወታደራዊ አማራጭ እንደሚጠቀሙ ማሳሰቢያ መስጠታቸው ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ኮት ዲቯር፣ ዘ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳኡ፣ ላይቤሪያ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሴራ ሊዮን እና ቶጎ 15ቱ የአኮዋስ አባል አገራት ናቸው።
የኢኮዋስ አባል ያልሆነችው ነገር ግን የኒጀር ጎረቤት አገር የሆነችው አልጄሪያ የኢኮዋስን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አጥበቃ ተቃውማለች። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቱቡኔ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አጠቃላይ የሳህል ቀጠናን ችግር ውስጥ የሚከት ነው ካሉ በኋላ አገራቸው አልጄሪያ በጎረቤቷ ላይ ኃይል አትጠቀምም ብለዋል።
ሌላኛዋ የኢኮዋስ አባል ያልሆነችው ነገር ግን የኒጀር ጎረቤት የሆነችው ቻድ በጉዳዩ ላይ ከአልጄሪያ ጋር ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቃለች።
የቻድ መከላከያ ሚኒስትር አገራችን በኒጀር ላይ ጣልቃ ለመግባት ምንም አይነት እቅድ የላትም ብለዋል።
መፈንቅለ መንግሥቱን መርተው እራሳቸውን የኒጀር መሪ ያደረጉት ጄኔራል አብዱራህማሜ ታቺኒ በኒጀር ላይ የሚቃጣን የትኛውንም አይነት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን አጥብቀው ሲኮንኑ ነበር።
በቅርቡ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዙት የቡርኪና ፋሶ እና ማሊ መሪዎች ደግሞ ኒጀር ላይ መፈንቅለ መንግሥት የሚፈጸም ከሆነ ለኒጀር ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።












