የማይክል ጆርዳን ማሊያ በ10.1 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቅርጫት ኳስ ኮከቡ ማይክል ጆርዳን እአአ በ1998 የውድድር ዘመን የለበሰው ማሊያ ክብረ ወሰን በሆነ 10.1 ሚሊዮን ዶላር ተሽጧል።
ይህም ከፍተኛ ዋጋ ያወጣ ስፖርት ቁሳቁስ ለመሆን በቅቷል።
አጫራች ድርጅቱ ሰዘቢስ እንዳለው ሽያጩ ለስፖርት አድናቂዎች እና ለማስታወሻ ሰብሳቢዎች “ትልቅ ደስታን” የፈጠረ መሆኑን ተናግሯል።
ጆርዳን ስድስተኛውን እና የመጨረሻውን የናሽናል ባስኬት ቦል አሶሴሽን (ኤንቢኤ) ዋንጫ ማሸነፉን የሚያስታውስ ማሊያ ነው ተብሏል። በውድድር ዓመቱ ዙሪያ ‘ዘ ላስት ዳንስ’ በሚል ኔትፍሊክስ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም አለ።
ሰዘቢስ አጫራች ድርጅ ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቀው ጆርዳን ለቺካጎ ቡልስ ሲጫወት የለበሰው ማሊያ 20 ተጫራቾችን ትኩረት ስቧል።
የሰዘቢስ ኃላፊ ብራህም ዋቸር ተጫራቾች "ብርቅዬውን ታሪካዊ ልብስ ለመውሰድ ጓጉተዋል" ብለዋል።
"የዛሬው ክብረወሰን የሰበረ ሽያጭ '... ማይክል ጆርዳን በማያሻማ መልኩ የምንግዜም ኮከብ መሆኑን የሚያጠናክር ነው። ዛሬም ስሙ እና ወደር የለሽ ትሩፋቱ ከዛሬ 25 ዓመት በፊት እንደነበረው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ዋጋው በ1986 የዓለም ዋንጫ ወቅት በእግር ኳስ ኮከቡ ዲዬጎ ማራዶና ለተለበሰውና 9.28 ሚሊዮን ዶላር ከተሸጠው ማሊያ በልጦ ክበረ ወሰኑን ይዟል።
ጀርዳን የፊት ገጽ ሽፋን ከያዘበት እና እአአ ሰኔ 1998 ከታተመው ስፖርት ኢላስትሬትድ መጽሔት ጋር ነው ለጨረታ የቀረበው።
ጆርዳን በቅርጫት ኳስ ታሪክ ምርጡ ተጫዋች እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል።
አብዛኛውን የጨዋታ ዘመኑን ቺካጎ ቡልስ ጋር አሳልፏል።
በዚህም ዓለም አቀፋዊ ተምሳሌት ከመሆን ባለፈ የኤንቢኤን ስም በዓለም ዙሪያ ከፍ ለማድረግ አግዟል።

የፎቶው ባለመብት, SOTHEBY'S
ቺካጎ ቡልስ በኤንቢኤ የፍጻሜ ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታን በዩታህ ጃዝ ተሸነፈ። የሚቀጥሉትን ሦስት ጨዋታዎች ቡልስ አሸነፈ። አምስተኛውን ጨዋታ ዩታህ ጃዝ በሁለት ነጥብ በልጦ ማሸነፍ ቻለ።
በስድስተኛው ጨዋታ አንገት ለአንገት የተናነቁበት ነበር። ጆርዳን ጨዋታው 5.2 ሰከንዶች ሲቀሩት ቡልሶች 87-86 በሆነ ውጤት እንዲያሸንፉ ያስቻላቸውን ነጥቦች አስቆጠረ። ኮከቡ የመጨረሻውን የኤንቢኤ ዋንጫውን ከፍ ለማድረግ በቃ።
ጆርዳን በሰሜን ካሮላይና የአባቱን መገደል ተከትሎ በ1993 ከቅርጫት ኳስ ራሱን አገለለ። ኮከቡ ቺካጎ ቡልስ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ሻምፒዮን እንዲሆን አስችሏል።
ጆርዳን "ሁሌም አፅንዖት መስጠት እፈልጋለሁ... የመነሳሳት እና እንደ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች አንድ ነገር የማረጋገጥ ስሜት ሲጠፋብኝ ለማቆም ጊዜው አሁን ነው እላለሁ" ብሏል።
59 ዓመቱ ጆርዳን በ2003 ነበር ጫማውን ለመጨረሻ ጊዜ የሰቀለው።












