በንግሥት ኤልዛቤጥ መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የቻይና ልዑካን እንዳይገኙ ተከለከሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቻይና መንግሥት ልዑካን በዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳይገኙ መታገዳቸውን ቢቢሲ ከምንጮቹ ለመረዳት ችሏል።
ቻይና በአምስት የዩኬ ምክር ቤት አባላት እና ሁለት ሰዎች ላይ የጣለችውን ዕቀባ ተከትሎ፣ የዩናይትድ ኪንግደም ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት ሰር ሊንድሲ ሆይል የቻይና ልዑካን ለቀብር ሥርዓቱ ወደ ዌስትሚኒስቴር አዳራሽ እንዳይገቡ መከልክላቸውን ፖለቲኮ ነበር መጀመሪያ የዘገበው።
ባለፈው ሳምንት ያረፉት ንግሥት ኤልዛቤጥ በሚቀጥለው ሰኞ በሚካሄድ ሥነ ሥርዓት ቀብራቸው ይፈጸማል።
የዩናይትድ ኪንግደም ምክር ቤት ጉዳዩን በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ የደኅንነት ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ቻይና በአናሳዎቹ የዊጋ ሙስሊም ማልበረሰቦች ላይ ጭቆና ትፈጽማለች የሚል ክስ በመሰንዘራቸው ባለፈው ዓመት ሰባት የፓርላማ አባላትን ጨምሮ ዘጠኝ ብሪታኒያውያን ላይ የጉዞ እና ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ እገዳ መጣሏል።
ይህንንም ተከትሎ በዩናይትድ ኪንግደም የቻይና አምባሳደር ወደ አገሪቱ ፓርላማ እንዳይገቡ ተከልክለው ቆይተዋል።
አሁን ደግሞ ይህ ዕገዳ በንግሥቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘት አክብሮታቸውን ለመግለጽ በሚመጡ የቻይና ልዑካን ላይ ተግበራዊ ይሆናል ተብሏል።
የዩናይትድ ኪንግደም እና የቻይና ግንኙነት ሻክሮ የቆየ ሲሆን፣ ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ የተጣለው ክልከላ የበለጠ ግንኙነታቸውን ያበላሸዋል ተብሏል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከሚታደሙት እንግዶች መካከል ስማቸው የሚገኝ ቢሆንም፣ በቀብሩ ላይ ሊገኙ የሚችሉበት አጋጣሚ ዝቅተኛ መሆኑ ተነግሯል።
ነገር ግን የቻይናው ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ኪሻን በመጪው ሰኞ ከአገሪቱ ፓርላማ ተሻግሮ በሚገኘው በዌስትሚኒስቴር አቤይ በሚካሄደው መንግሥታዊ የቀብር ሥርዓት ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ
በዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ሥርዓተ ቀብር ላይ የቻይና መንግሥት ተወካዮች እንዲገኙ የቀረበው ግብዣ እንዲሰረዝ የዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኞች እና የምክር ቤት አባላት ጠይቀው ነበር።
የቻይና መንግሥት ተወካዮች በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት መጋበዛቸው አሳስቦናል በማለት ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ደብዳቤ ከጻፉት መካከል የወግ አጥባቂው ፓርቲ ጉምቱ አባላት ይገኙበታል።
የምክር ቤት አባላቱ በቻእና አነሳ በሆኑት ዊገር ሙስሊም ማኅብረሰብ አባላት ላይ “የዘር ማጥፋት” ወንጀል የሚያስጽሙት ባለሥልጣንት መጋበዛቸው አሳሳቢ ነው ብለዋል።
የፊታችን ሰኞ መስከረም 09/2015 ዓ.ም. በሚከናወነው የንግሥቲቱ ሥርዓተ ቀብር ላይ እንዲገኙ ለቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ይፋዊ ጥሪ የቀረበ ቢሆንም ፕሬዝዳንቱ ግን ይገኛሉ ተብሎ አይጠበቅም።
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ሳምንት ከሁለት ዓመታት በኋላ በመጀመሪያቸው በሆነው የውጭ አገር የሥራ ጉብኝት ጉዟቸው ወደ ካዛኪስታን እና ኡዝቤኪስታን አቅንተዋል።
የቻይናው 'ሳውዝ ቻይና ሞርኒን ፖስት' ጋዜጣ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ኪሻን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በንግሥቷ ቀብር ላይ ማን ይገኛል?

የፎቶው ባለመብት, EPA
በንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ወደ 500 የሚጠጉ ርዕሳነ ብሔራት እና የውጭ አገር ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አብዛኞቹ መሪዎች በንግድ አውሮፕላን በረራዎች እንዲመጡ የተጠየቁ ሲሆን፤ ምዕራብ ለንደን ከሚገኝ ቦታ በአውቶብስ እንደሚጓጓዙም ተነግሯቸዋል ተብሏል።
በዕለቱ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከሚገኙት መካከል ከመላው አውሮፓ የሚመጡ ንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት ይገኙበታል።
የቤልጂየም፣ የኔዘርላንድስ፣ የስፔን ነገሥታት የሚገኙ ሲሆን፣ የኖርዌይ፣ የስዊድን፣ የዴንማርክ እና የሞናኮ ንጉሣውያን ቤተሰቦችም በቀብሩ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ከአገራት መሪዎች መካከል የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከእነ ባለቤታቸው በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደሚገኙ ዋይት ሐውስ አረጋግጧል።
ከኮመንዌልዝ አገራት መሪዎች መካከል የአውስትራሊ፣ የካናዳ እና የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚንስትሮች ጥሪውን ተቀብለዋል።
የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የፈረንሳይ፣ የደቡብ ኮሪያ፣ የብራዚል እና የቱርክ ፕሬዝዳንቶችም እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ያልተገባዙትስ እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሩሲያ፣ ከቤላሩስ እና ከሚያንማር በዩናይትድ ኪንግደም ንግሥት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙ ባለሥልጣንት የሉም።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በንግሥቲቱ ቀብር ላይ የመገኘት ዕቅድ እንደሌላቸው ቃል አቀባያቸው ቀደም ሲል ተናግረው ነበር።
ዩናይትድ ኪንግደም ከሶሪያ፣ ከቬንዙዌላ እና ከአፍጋኒስታን ጋር ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስለሌላት ከእነዚህ አገራት በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚገኝ አይኖርም።
ሰሜን ኮሪያ፣ ኢራን እና ኒካራጉዋ ደግሞ አምባሳደሮቻቸውን ብቻ እንዲልኩ ተጋብዘዋል።
የዊገር ማኅብረሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቻይና በሚገኙት አናሳ እና ሙስሊም በሆኑት ዊገር ማኅብረሰብ አባላት ላይ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም ይገለጻል።
ከአንድ ዓመት በፊት የዩኬ ምክር ቤት በሰሜን-ምዕራብ ቻይና በማኅበረሰቡ አባላት ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመ ነው ሲል አውጆ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ወደ 1 ሚሊዮን የሚገመቱ የዊገር ማኅብረሰብ አባላት በጀምላ እስር ላይ እንደሚገኙ ይገመታል።
ቻይና ግን ‘በመጠለያ ጣቢያዎች’ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ‘የታህድሶ ትምህርት’ ይሰጣል እንጂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይፈጸምም ትላለች።
የዩናይትድ ኪንግደም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለአገራቸው ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ በቻይና ውስጥ በማኅብረሰቡ አባላቱ ላይ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመ መሆኑን ምክር ቤቱ አረጋግጦ ሳለ፤ ይህን እያስፈጸሙ ያሉትን መጋበዛቸው አግባብ አይደለም በማለት ግብዣው በፍጥነት እንዲሰረዝ ጠይቀዋል።












