የቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን መሥራቹ እስረኞችን ለሩሲያ ጦር ሲመለምል ነበር ተባለ

የፎቶው ባለመብት, LEAKED VIDEO
የሩሲያው የቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ‘ዋግነር ግሩፕ’ መሥራች እና መሪ በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ለሩሲያ የሚዋጉ ወታደሮችን ከእስረኞች መካከል ሲመለምል ሾልኮ በወጣ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ታየ።
ቢቢሲ ባረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የዋግነር ቡድን መሥራች የይቬጌኒይ ፕሪጎዝሂን ለበርካታ እስረኞች ንግግር ሲያደርግ ይታያል።
ፕሪጎዝሂን ለእስረኞች ባደረገው በንግግሩ በሚመራው ቡድን ተካተው ለሩሲያ የሚዋጉ ከሆነ የእስር ጊዜያቸው እንደሚቀነስላቸው ይገልጻል።
ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ሩሲያ የወታደር ቁጥሯን ለመጨመር ጥፋተኛ ተብለው የእስር ጊዜ እያሳለፉ ያሉ እስረኞችን በውትድርን ለማሳለፍ ጥረት እያደረገች ነው የሚሉ መረጃዎችን ያረጋገጠ ሆኗል።
ምንም እንኳ የሩሲያ ሕግ የውትድርና አግልግሎት መስጠት የፍርድ ብይን እንዲቀነስ ባይፈቅድም፤ የዋግነር ቡድን መሥራች ግን “ማንም ወደ እስር ቤት አይመለስም” ሲል ይደመጣል።
“ለስድስት ወራት ካገለገላችሁ (ለዋግነር ቡድን)፤ ነጻ ናችሁ” ካለ በኋላ ለመዋጋት ከተስማሙ በኋላ ክህደት በሚፈጽሙት ላይ ከባድ ቅጣት እንደሚኖር ፕሪጎዝሂን ሲያስጠነቅቅ ይሰማል።
“ዩክሬን ደርሳችሁ ይህ አይመለከተኝም ካለችሁ፤ እንገድላችኋለን።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቡድኑ መሪ በመቀጠልም የዋግነር ሕግጋትን ሲያስረዳ ይደመጣል። ፕሪጎዝሂን አልኮል እና አደንዛዥ እጽ መጠቀም የተከለከለ መሆኑን ገልጾ፤ “ከአካባቢው ሴቶች ጋር ጾታዊ ግንኙነት ማድረግ” አይፈቀድም ይላል።
ቢቢሲ የተንቀሳቃሽ ምስሉ በሩሲያዋ ማሪያ ኤል ሪፐብሊክ ግዛት መቀረጹን ያረጋገጠ ሲሆን ተንቀሳቃሽ ምስሉ ግን መቼ እንደተወሰደ ማወቅ አልተቻለም።
የ61 ዓመቱ ግለሰብ የሚመራው ቡድን በተለይ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ቅጥረኛ ወታደሮችን የሚያሰማራ ሲሆን፣ በግድያ እና በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ይደረጋል።
ሩሲያ ከዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን ጋር ግንኙነት የለኝም ስትል ታስተባብል እንጂ፣ የቡድኑ መሥራች ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ቅርብ ግንኙነት አላቸው።
በዚህ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ መሥራቹ እራሱን “የግል የጦር ኩባንያ ተወካይ” ብሎ ካስተዋወቀ በኋላ፤ “ምናልባት ዋግነር ግሩፕ የሚባል ስም ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል” ብሎ እስረኞቹን ሲጠይቅ ይሰማል።
የ61 ዓመቱ ግለሰብ ከዚህ ቀደም ሌሎች እስረኞች በዩክሬን ተሰማርተው እንደነበረ ገልጾ፤ አዲሶቹ ምልምሎች በጠላት ኃይል የመማረክ ዕጣ ከተጋረጠባቸው እራሳቸውን በቦምብ መግደል እንዳለባቸው ያሳስባል።
ይህ የቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን እአአ 2014 ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ማንነቱ ይፋ የሆነው። ያን ጊዜ ከዩክሬን መገንጠል የሚፈልጉ የሩሲያ ደጋፊ ኃይሎችን በማገዝ ለውጊያ የጦር ድጋፍ ሲሰጥ እንደነበረ ተዘግቧል።
ከዚያ በኋላ ይህ የቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን ስሙ በሩሲያ፣ በሞዛምቢክ፣ በሱዳን እና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሊቢያ እና በማሊ ተደጋግሞ ሲነሳ ቆይቷል።
እጅግ ምስጢራዊ እንደሆነ የሚነገረው ዋግነር የቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን፤ በሊቢያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ እንደነበረው ይነገራል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ጊዜ ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከፍተኛ የሠራዊት አባላቶቿን ማጣቷ ይነገራል።
ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ላይ የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ሩሲያ በጦርነቱ ከ80 ሺህ የማያንሱ ወታደሮቿ ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ብለው ነበር።












