ከቆቦ ተፈናቅለው በመርሳ የተጠለሉ ነዋሪዎች በችግር ላይ እንደሚገኙ ተናገሩ

የኢትዮጵያ ካርታ

ከሦስት ሳምንት በፊት ባገረሸው ጦርነት ምክንያት ከአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ ተፈናቅለው በመርሳ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ እናቶች፣ አረጋውያንና ህፃናት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናገሩ።

ለወራት ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ መልሶ ከተቀሰቀሰ በኋላ በትግራይ ኃይሎችና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል የሚካሄደው ጦርነት እንደቀጠለ ነው።

ጦርነቱ መልሶ በተጀመረበት ሳምንት ውስጥ ቀዳሚ ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተባቸው ስፍራዎች መካከል አንዱ በሆነውና በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በገባችው የቆቦ ከተማ በርካታ ነዋሪዎች ጦርነት በመሸሽ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሸሻቸው ተዘግቧል።

ከእነዚህ መካከልም በበመርሳ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ሁለት እናቶች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከነልጆቻቸው የምግብ ችግር እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል።

ነፍሰ ጡር እና ልጇን ይዛ ከቆቦ ተፈናቅላ በጊዜያዊው መጠለያ ውስጥ የምትገኝ እናት እንዳስረዳችው ወደ መጠለያው በገቡበት አስከ አራት ቀናት ድረስ የሚያርፉበት መኝታ እንኳን አልነበራቸውም።

ከዚያ በኋላ ግን የሚነጠፉ ሸራዎች የቀረበላቸው ሲሆን ወደ መጠለያው ከገቡ ከሳምንታት በኋላም በዚያ ላይ እንደሚተኙ ተናግራለች።

የምግብ እጥረት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደከተታቸው የምትናገረው ይህች ግለሰብ በቤተሰብ፣ አንድ ወይም ሁለት ኪሎ ሩዝ የሚሰጣቸው ሲሆን “እሱንም ዘይት ባለመኖሩ በባዶ እየቀቀልን ለመመገብ ተገደናል” ብላለች።

ነሐሴ 21/2014 ዓ.ም. ከቆቦ ከተማ ተፈናቅላ መምጣቷን ለቢቢሲ ያስረዳችው ይህች እናት፣ ጦርነቱ ከዚህ በፊት ከነበረው አጠር ያለና ለሁለት እና ለሦስት ቀናት በመካሄዱ ልብስ ቅያሪ እንኳን ሳይዙ ባዶ እጃቸውን እንደወጡ ታስረዳለች።

“በለበስነው ልብስ ነው የወጣነው። በዚያው ወደ ኮምቦልቻ አካባቢ ቤተሰብ ስለነበረን ሄድን። ከዚያ ደግሞ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያችሁ ተመለሱ ሲባል ተመለስን። በአሁኑ ወቅት መንግሥት ባቋቋመው ካምፕ ላይ እንገኛለን” የምትለው ይህች ተፈናቃይ ከእሷና ከልጇ በተጨማሪ የእህቶቿም ልጆች በዚሁ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

በዚህ ጊዜያዊ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ሴቶች፣ አረጋውያ እና ህፃናት የሚገኙ ሲሆን በቁጥርም በርካታ ናቸው ብላለች።

በመጠለያው በመንግሥት በተቋቋመ ጊዜያዊ የህክምና ማዕከል ህክምና ማግኘታቸውን እንደ በጎ ብታየውም “ሁሉ ነገር ፈታኝ ነው” ትላለች።

ከሁሉም በላይ ቤት የለመዱ ህፃናት ምቾት አጥተው ሲንገላቱና ሲያለቅሱ፣ መኝታ በሌለበት ሁኔታ በብርድ ሲቆራመዱ ማየት ለወላጆች እጅግ አሰቃቂ ሁኔታ መሆኑን ገልጻለች።

“ከመብላትም ከመጠጣትም በላይ ተኝተን የምናርፍበት ቦታ ያስፈልጋል፤ ቅያሪ ልብስም ይዘን አልመጣንም። ልጆቹም ቅያሪ ልብስ የላቸውም። በጣም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው” ብላለች።

እስካሁን ድረስ የምግብ እርዳታ የተደረገላቸው በረድዔት ድርጅቶች ሲሆን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት እየመጡ ቢያናግሯውም መፍትሄ ሊያበጁላቸው አልቻሉም ይላሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ችግራቸውን ለጎበኟቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት በተናገሩበት ወቅት “ለረድዔት ድርጅቶች እንደሚያሳውቁና መንግሥት በቻለው አቅም የሚችለውን ያደርጋል፤ እንዲሁም ወደ አካባቢያችሁ ትመለሳላችሁ” የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ባለሥልጣናቱ መጥተው ከማየት በስተቀር ከመንግሥት በኩል ድጋፍ እየተደረገላቸውም እንዳልሆነ በመጠለያው ውስጥ የሚገኙት ተፈናቃዮች ለቢቢሲ ተናገረዋል።

የመጠለያ ማዕከሉ ሁሉንም ለማስተናገድ በቂ ባለመሆኑ ሴቶች፣ አረጋውያን እና ህፃናት ብቻ ናቸው በውስጡ ተጠልለው የሚገኙት። በዚህም ሳቢያ ከቆቦ ተፈናቅለው የመጡ አዋቂ ወንዶች ያለመጠለያ እና እርዳታ በማያገኙበት ሁኔታ በችግር ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በዚህም ሳቢያ ከጦርነቱ ሸሽተው የተፈናቀሉት አዋቂ ወንዶች በኪሳቸው ይዘውት በነበረ ገንዘብ እየኖሩ ሲሆን፣ ወደመጡበት ለመመለስም ጥረት እያደረጉ ናቸው ተብሏል።

ሌላኛዋ ከቆቦ የመጣችና በዚሁ መጠለያ ካምፕ ከሦስት ህፃናት ልጆቿ ጋር የተፈናቀለች እናት በበኩሏ “በካምፑ እርዳታ ብዙም የለም፤ ለቤተሰብም ብር ላኩልን እያልን እያስቸገርን ነው” ትላለች።

“ልጆች ይዘን ምን እናበላለን ብለን ሩቅ ያለ ቤተሰብ ገንዘብ እየጠየቅን ነው” ስትል ለቢቢሲ ያሉበትን ፈታኝ ሁኔታ አስረድታለች።

“ልጅ ይዞ ስደት በጣም ከባድ ነው። ልጆች ደግሞ ፍላጎታቸው ብዙ ነው። ወደ ቤታችን መቼ ነው የምንሄደው?” ስትል ትጠይቃለች።

ይህች እናት ጦርነቱን በመሸሽ በአስቸጋሪ ሁኔታ በእግር ተጉዘው አሁን ካሉበት መድረሳቸውን በመግለጽ፤ “ከቀያችን ያለንን ሁሉ ትተን የወጣነው ሕይወታችን ለማትረፍ ነው” ብላለች።

በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የውሃ እና የምግብ አቅርቦት ችግር ዋነኛ ጉዳይ ሲሆን “የጤና ባለሙያዎች ስላሉ ህክምናው ከሌላው የተሻለ ነው” ትላለች።

“ምግብ፣ መኝታና ልብስ ያስፈልጋል” የምትለው እናት እሷም ብትሆትን “የመንግሥት አካላት መጥቶ ከማናገር ውጪ ያደረጉልን ነገር የለም” ትላለች።

መልሶ ካገረሸው ጦርነት ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት መርሳ አካባቢ ከ50 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ ለቢቢሲ የተናገሩት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን፣ የእርዳታ አቅርቦት ውስንነት አለ ብለዋል።

በአጠቃላይ የአሁኑ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከ150 ሺህ በላይ ሕዝብ ከሰሜን ወሎ ቆቦ እና ወልዲያ አካባቢዎች መፈናቀሉን የጠቀሱት አቶ እያሱ፣ ለእርዳታ ፈላጊዎች የፌደራሉ መንግሥት ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት በኩል መዘግየቶች እንዳሉም አስረድተዋል።

አዲስ የተፈናቀሉትን ሳይጨምር በክልሉ ከ8.7 ሚሊዮን በላይ ነዋሪም አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም ለፌደራሉ መንግሥት ጥያቄ ቀርቧል ብለዋል።

“የፌደራሉ መንግሥት ጥያቄዎቹን ሰምቶ ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት በኩል እግር የመጎተት ጉዳይ አለ” ሲሉ የእረዳታ አቅርቦቱ በሚፈለገው ሁኔታ መቅረብ ያልቻለበትን ምክንያት ገልጸዋል።

ከትራንስፖርት ችግርና ከአቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ በሚል እንዲሁም “በተለያዩ ምክንያቶች በጠየቅነው መጠን ምግቡ ተደራሽ እየሆነ ነው ብለን አናምንም” ብለዋል።

በዚህም በርካታ ተፈናቃዮች የምግብ ችግር ገጥሞናል እያሉ አቤቱታቸውን በተለያዩ መንገዶች መስማታቸውንም ገልጸዋል።

“የፌደራሉ መንግሥት ከዓለም አቀፉ ቀውስም ጋር ይሁን ከተለያዩ ችግሮች ጋር ተያይዞ፣ የምግብ አቅርቦት ውስንነት ያለ ይመስለኛል” ያሉት አቶ እያሱ የክልሉ መንግሥትም የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው ብለዋል።

ከመንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከባለሃብቶችና “ከማኅበረሰቡ የመደጋገፍ እሴት ነው የምግብ ክፍተቱን እየሞላን የተጎጂዎችን ጩኸት መቀነስ የተቻለው” ይላሉ።

መንግሥትም ይሁን እንዲሁም የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ የረድዔት ድርጅቶች እርዳታ በተወሰነ መልኩ ቢያቀርቡም ቀጣይነት ባለው መልኩ አይደለም ይላሉ።

አንዴ እርዳታ ተሰጥቶ ወራቶች የሚያልፉበት ሁኔታና፣ በመደበኝነት አለመቅረብ ችግርም እንዳለ ያስረዳሉ።

ስለዚህም የተፈናቃዮቹ ሁኔታ ለወራት የሚራዘምበት ሁኔታ ሳይሆን አፋጣኝ ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን የገለጹት አቶ እያሱ፣ መንግሥትም ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ከቆቦ ከተማ ተፈናቅለው የመጡ ወንዶች መጠለያ አላገኙም ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል መባሉን በመጥቀስ የተጠየቁት አቶ እያሱ፣ “ቅድሚያ ለእናቶች እና ለህፃናት እንደሚሰጥ አውቃለሁ” ቢሉም ከዚያ ውጪ ያሉትን ግን መጠለያዎቹ አልተቀበሉም የሚለውን ግን መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል። 

ከዚህ በtጨማሪ ሰኔ 18/2014 ዓ.ም. ካገረሸው ጦርነት ጋር ተያይዞ ከቆቦ የተፈናቀሉ ሰዎች በመርሳ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን በዋግ ኽምራ አካባቢ ደግሞ በወለህ ጊዜያዊ መጠለያዎች ይገኛሉ።

በዋግ ኽምራ ከ100 ሺህ በላይ ሕዝብ ድጋፍ እንደሚፈልግና ይሄንንም ሕዝብ ለመደገፍ እና ለማቋቋም በርካታ ሥራዎች እንሚጠይቁና “ከማንኛውም ጊዜ በላይ የማኅበረሰቡ፣ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ከዚህ በፊት በጦርነቱ ከ1.4 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተፈናቅሏል ያሉት አቶ እያሱ፣ ከጦርነቱም ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ የተፈናቀሉ ሰዎችን ትክክለኛውን አሃዝ ለማግኘትም ወደ አካባቢዎቹ ቡድን እንደተላከም አስረድተዋል።

ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት እንደገና ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. አገርሽቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል “የሕዝብን ፍጅት ለማስወገድ ሲባል” ከቆቦ ከተማ ለቅቆ መውጣቱን የገለጸ ሲሆን፣ የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው “በፀረ ማጥቃት ዘመቻ” የቆቦን ከተማ መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል። 

ጦርነቱም በመጀመር አንደኛው ወገን ሌላኛውን የሚከስ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታት ከባድ ውጊያዎች በተለያዩ ግንባሮች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

በ2013 ዓ.ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት የአስር ሺዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል።