የአውሮፓ ኅብረት በመቀለ የተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች የሰላም ተስፋን አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው አለ

መቀለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመቀለ ከተማ መስከረም 04/2015 ዓ.ም. የተፈጸሙ ሁለት የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃቶች በኢትዮጵያ ያለውን የሰላም ሂደት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን የአውሮፓ ኅብረት ገለጸ።

የአውሮፓ ኅብረት ቃለ አቀባይ ረቡዕ ዕለት ባወጡት መግለጫ ጥቃቱ በመነመነው የሰላም ተስፋ ላይ ስጋትን ጋርጧል ብሏል።

ረቡዕ ዕለት በመቀለ ከተማ በተፈጸሙ ሁለት ተከታታይ የድሮን ጥቃቶች 10 ሰዎች መገደላቸውንና 10 ሰዎች እንደቆሰሉ የአይደር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ክብሮም ገ/ሥላሴ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ጥቃቱ የመኖሪያ መንደሮችን ዒላማ ማድረጋቸውን እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የትግራይ አመራር አቶ ጌታቸው ረዳ ጥቃቱን ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

በመቀለ ከተማ ተፈጸመ ስለተባለው የድሮን ጥቃቶች እስካሁን ድረስ ከፌደራል መንግሥቱ በኩል የተባለ ነገር የለም።

የአውሮፓ ኅብረት በተጨማሪም በዚህ ጦርነት ላይ የኤርትራ ጦር ተሳትፎ በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል ብሏል መግለጫው።

በቅርቡ የትግራይ ክልል መንግሥት አስቸኳይ ለሆነ የተኩስ አቁም እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ለሚደረገው የሰላም ሂደት ዝግጁ መሆኑን መግለፁ፣ እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱም ከዚህ ቀደም ሲል በነበረው አቋም መሰረት ይህ ሁኔታ ግጭቶችን ለማስቆም ዕድል መክፈት እንደነበረበትም አፅንኦት ሰጥቶ ይህ ግን አለመሆኑ እንዳሳዛነው ገልጿል።

በዚህም በድርድር ላይ የተመሰረተ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ እንዲሁም ቀጥተኛ ውይይት ማድረግ እንዲቻል መንገድ የሚከፍት ነው ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኅብረቱ ከሳምንታት በፊት ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በመቋረጡ ከዚህም በፊት ከነበረው በላይ የንጹሃን ዜጎች ሕይወትን የመቅጠፍ አደጋ ጋርጧል። በተጨማሪም በምጣኔ ሀብቱና በአጠቃላይ በአገሪቱ እድገት ላይ ከባድ ኪሳራንም የሚያስከትል ነው ብሏል።

“የሰላም ንግግሮች ብቸኛው አማራጭ መንገድ ነው” ያለው የአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያ የጀመረችው አዲስ ዓመት ሰላማዊ ሊሆን እንደሚገባም መልዕክቱን አስተላልፏል።

የአውሮፓ ኅብረት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ይህንን ዕድል በአፋጣኝ ተጠቅመው ጦርነቱን በሰላም እንዲቋጩ እና በድርድር ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱም ጠይቋል።

ኅብረቱ በአህጉራዊው ድርጅት ጥላ ስር ለሚደረገው የሰላም ድርድር ድጋፉን እንደሚሰጥ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር በንቃት ለመሳተፍ ዝግጁ ነኝ በማለት አስምሯል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራው የሰላም ሂደት ቁርጠኛ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለአውሮፓ ኅብረት ተናግረዋል።

ደመቀ መኮንን ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ እንደሚያደርግ ያላቸውንም እምነት የገለጹት ለአፍሪካ የአውሮፓ የውጭ አገልግሎት ዳይሬክተር ሪታ ላራንጂንሃ ጋር ረቡዕ ዕለት ባደረጉት ውይይት ነው።

በተጫማሪም ጦርነቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትሰራለች ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሯ በበኩላቸው ኅብረቱ ስትራቴጂካዊ አጋርነቱን የማጠናከር ፍላጎት አለው ያሉ ሲሆን እንዲሁም ለሰላም ሂደቱ በሚፈለገው ጊዜ ለመርዳት ፍላጎት እንዳለውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት እንደገና ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. አገርሽቷል።

ጦርነቱም በመጀመር አንደኛው ወገን ሌላኛውን የሚከስ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታት ከባድ ውጊያዎች በተለያዩ ግንባሮች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

በ2013 ዓ.ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት የአስር ሺዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል።