በሐማስ ታግተው የነበሩ ተጨማሪ እስራኤላውያን ከሰዓታት ጭንቅ በኋላ ተለቀቁ

የ9 ዓመቷ ኢምሊ ሃንድ፣ የ17 ዓመቱ ኖአም ኦር እና የ52 ዓመቷ ሻሮን አቪግዶሪ
የምስሉ መግለጫ, ቅዳሜ ምሽት ከእገታ ከተለቀቁት እስራኤላውያን መካከል የ9 ዓመቷ ኢምሊ ሃንድ፣ የ17 ዓመቱ ኖአም ኦር እና የ52 ዓመቷ ሻሮን አቪግዶሪ ይገኙበታል።

በእስራኤልና በሐማስ መካከል በተደረሰው የታጋቾችና የእስረኞች ልውውጥ ስምምነት መሠረት ቅዳሜ ዕለት ተጨማሪ እስራኤላውያን ተለቀቁ።

ታጋቾቹ የተለቀቁት ከእገታው ይወጣሉ ከተባለበት ጊዜ ለሰዓታት ዘግይተው ሲሆን ይህም በቤተሰቦቻቸው ዘንድ ከፍተኛ ጭንቀትን ፈጥሮ ነበር።

የእስራኤል ጦር እንዳለው 13 እስራኤላውያን ነጻ የወጡ ሲሆን በዌስት ባንክ ታስረው የነበሩ 39 ፍልስጥኤማውያንም ከእስር ተለቀዋል።ሐማስ ሌሎች አራት የታይላንድ ታጋቾችንም ለቋል።

በኳታር አሸማጋይነት ከተደረሰውና ለአራት ቀናት ከሚቆየው ጊዜያዊ ተኩስ አቁም በኋላ ከሐማስ ታጋቾች መካከል የተወሰኑት በመጀመሪያው ዙር አርብ ዕለት ያለምንም ችግር ተለቀዋል።

ቅዳሜ ዕለት የተለቀቁት እስራኤላውያን ጋዛ ከግብጽ ጋራ በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ለቀይ መስቀል ተላልፈው ይሰጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም መስተጓጎል አጋጥሞት ነበር።

የሐማስ ታጣቂ ቡድን ክንፍ ቃሳም ብርጌድ፣ በሰሜን ጋዛ እርዳታ ከማድረስ ጋር እንዲሁም በእስራኤል ከሚለቀቁ ፍልስጥኤማዊ እስረኞችን መልቀቂያ መስፈርት ጋር በተያያዘ ያጋጠመው ችግር ለመስተጓጎሉ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

እስራኤል ግን ይህን አስተባብላለች።

የሐማስ ቃል አቀባይ ኦሳማ ሃምዳን ከአርብ ዕለት ጀምሮ 340 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መሄዳቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን ሰሜን ጋዛ የደረሱት 65ቱ ብቻ ናቸው ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህም እስራኤል ከተስማማችው ከግማሽ የሚያንስ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። እስራኤል ግን ሰሜን ጋዛ የጦርነት ቀጠና በመሆኑ በስፋራው እርዳታ የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት የተባበሩት መንግሥታት ነው ብላለች።

በኋላ ላይ ለውይይቱ ቅርበት ያላቸው አንድ ከፍተኛ የፍልስጥኤም ባለሥልጣን በኳታር አማካኝነት ውዝግቡ መፈታቱን አረጋግጠዋል።

ሐማስ ከእስራኤል ጋር የተደረሰውን ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንዲቀጥል በማድረጋቸው ለግብፅ እና ለኳታር ምስጋናውን ገልጿል።

በስምምነቱ መሠረት 50 እስራኤላውያን ሕጻናትና ሴት ታጋቾች በአራት ቀናት ውስጥ በሐማስ የሚለቀቁ ሲሆን፣ በእስራኤል ታስረው የነበሩ 150 ፍልስጥኤማውያን እስረኞችም ከእስር ይፈታሉ።

የእስራኤል መንግሥት በአንድ ቀን 10 እስራኤላውያን የሚለቀቁ ከሆነ ጊዜያዊ የተኩስ አቁሙ ሊራዘም ይችላል ብሏል።ሆኖም ሐማስን ለማጥፋት ቃል የገባ ሲሆን ስምምነቱም ጊዜያዊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥቶ ገልጿል።

እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ሐማስ የእስራኤልን ደቡባዊ ክፍል ሲወር 240 የሚጠጉ እስራኤላውያንን አግቶ መውሰዱንና አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ 1 ሺህ 200 ሰዎችን መግደሉን እስራኤል ማስታወቋ ይታወሳል።

በኢራን የሚደገፈው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን በእስራኤል፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ በሽብርተኝነት ተፈርጇል።

እስራኤል ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ በቡድኑ ለተፈፀመባት ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ለመስጠትም ጋዛን በማያባራ ቦምብ አጋይታለች፤መሠረተ ልማቶችን አውድማለች።

ሐማስ እንዳለው እስካሁን በርካታ ሕጻናትን ጨምሮ ወደ 15 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል። ምግብ ፣ ውሃ እና የንጽሕና መጠበቂያዎች ጨምሮ ነዋሪዎች በከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ እጦት እየተሰቃዩ ነው።

በቴል አቪቭ ድምጻቸውን ለማሰማት የወጡ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቅዳሜ ዕለት 50 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች ‘ወደ ቤታቸው መልሷቸው’ የሚል መፈክሮችን በመያዝ በቴል አቪቭ አደባባይ ለታጋቾች ድምጻቸውን አሰምተዋል።

የእስራኤል መንግሥት ቅዳሜ ዕለት የተደረገው ርክክብ፣ ሁለት በአስራዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ የኦር ቤተሰብ አባላት ፣ የ53 እና የ18 ዓመት እድሜ ያላቸው ሁለት የዌስ ቤተሰብ አባላት፣ የ52 እና የ12 ዓመት የአቪግዶሪ ቤተሰብ አባላት እና የሦስት እና የስምንት ዓመት ሕጻናትን ጨምሮ አራት የሐራን እና ሾሃም ቤተሰቦች አባላትን ነጻ አውጥቷል ብሏል።

ከታጋቾች መካከል አንዷ የሆነችው የዘጠኝ ዓመት ልጅ ኢሚሊ ሃንድ አባት፣ ልጃቸው በሕይወት በመመለሷ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ አሁንም ድረስ ታግተው ያሉ ሰዎችን ወደ ቤታቸው ለመመለስ የተቻላቸውን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ቅዳሜ ዕለት የተለቀቁትን ፍልስጥኤማውያን እስረኞች ለመቀበልም በቤቱኒያ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ነበር።

የቢቢሲ ዘጋቢ ሉሲ ዊሊያምሰን እንደዘገበችው በርካቶችም የሐማስን አረንጓዴ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ታይተዋል።

ከተለቀቁት እስረኞች መካከል በአውሮፓውያኑ 2015 በእየሩሳሌም በተፈፀመው ጥቃት ተሳትፋለች በሚል ተጠርጥራ የታሰረችው የ23 ዓመቷ ኖርሃን ትገኝበታለች።

ኖርሃን የ10 ዓመታት እስር ተፈርዶባት የነበረ ሲሆን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ሲቀራት ነው ቅዳሜ ዕለት የተለቀቀችው።

ኢስራ ጃቢስም በዌስት ባንክ ፈጣን መንገድ ላይ ከፍተሻ ጣቢያ በ1.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መኪናዋ ከተበላሸ በኋላ ከ2015 ጀምሮ በእስር አሳልፋለች።በወቅቱ የቦምብ ጥቃት ለመፈፀም ሙከራ እንደነበር እስራኤል የገለጸች ሲሆን ጉዳዩ አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ስሬታ ታቪሲን ቅዳሜ ዕለት ከእገታ የተለቀቁት አራት የታይላንድ ዜጎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።