እስራኤል የምትለቃቸው ፍልስጤማውያን እስረኞች እነማን ናቸው? ለምንስ ታስረው ቆዩ?

በእስራኤል ታስረው የሚገኙ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ፎቷቸውን ይዘው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል ታስረው የሚገኙ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ፎቷቸውን ይዘው

እስራኤል እና ሐማስ እስረኞችን እና ታጋቾችን ለመለዋወጥ ተስማምተዋል። ለአራት ቀናት ውጊያ ለማቆም ከስምምነት ደርሰዋል።

እስራኤል ሊፈቱ የሚችሉ 300 ፍልስጤማውያንን ስም ዝርዝር አሳውቃለች። አብዛኞቹ ዕድሜያቸው 17 ወይም 18 ናቸው። አጠቃላይ ግን ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 59 ይደርሳል። 274 ያህሉ ደግሞ ወንዶች ናቸው።

ስም ዝርዝሩ ይፋ የሆነው በእስራኤል ውስጥ ባለው ሕጋዊ አሠራር ምክንያት ነው። ማንኛውም እስረኛ ከመፈታቱ በፊት፣ የእስራኤል ዜጎች ስሞቹን አይተው ለእስራኤል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማለት 24 ሰዓት ሊሰጣቸው ይገባል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ሐማስ በየቀኑ 12 ሰዎችን በመልቀቅ በአጠቃላይ 50 ሴቶች እና ሕጻናት ታጋቾችን ይለቃል። ከዚያም እስራኤል 150 ፍልስጤማውያንን ትፈታለች።

በሁለተኛው ምዕራፍ 10 ታጋቾች በተፈቱ ቁጥር የተኩስ አቁሙ በአንድ ቀን ይራዘማል። እስራኤል እስከ 50 የሚደርሱ ታጋቾች ከጋዛ ከተለቀቁ እስከ 150 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትፈታለች።

በኳታር ሸምጋይነት የተደረሰውን ስምምነት የዓለም መሪዎች በደስታ ተቀብለውታል።

በአውሮፓ ኅብረት፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ በአሸባሪነት የተፈረጀው ሐማስ መስከረም 26 ባደረሰው ጥቃት፣ ከአንድ ሺህ 1400 በላይ ሰዎችን ገድሎ ከ200 በላይ የሚሆኑትን አግቷል።

ከዚያ ወዲህ በጋዛ ሰርጥ የሚኖሩ ከ14 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን በእስራኤል የአየር ጥቃት እና በምድር ዘመቻ ተገድለዋል።

የእስራኤላዊ ታጋች ቤተሰብ መንግሥት ታጋቾችን ወደ ቤታቸው እንዲመልስ ከሚጠይቅ ጽሁፍ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤላዊ ታጋች ቤተሰብ መንግሥት ታጋቾችን ወደ ቤታቸው እንዲመልስ ከሚጠይቅ ጽሁፍ ጋር

የእስረኞች መለዋወጥ ታሪክ

እስራኤል ሊፈቱ የሚችሉትን 300 ፍልስጤማውያን እስረኞች ፈጽመውታል ያለችውን ወንጀሎች እና ጥፋቶች ዘርዝራለች።

በዚህም የግድያ ሙከራ፣ ቦምብ መወርወር፣ ፈንጂ ወይም ተቀጣጣይ ነገር መሥራት፣ ድንጋይ መወርወር፣ ከጠላት ቡድን ጋር መገናኘት፣ ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ እና የዜጎችን ንብረት በማቃጠል የታሰሩ መሆኑን አስታውቃለች።

ከቀድሞዎቹ የእስረኞች ልውውጦች በተለየ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ሰዎች መካከል አንዳቸውም እስራኤላውያንን በመግደል ወንጀል አልተከሰሱም።

ጥቅምት 2011 (እአአ) እስራኤላዊውን ወታደር ጊላድ ሻሊት በሐማስ ምርኮ ውስጥ ከቆየ ከአምስት ዓመታት በኋላ ነጻ የወጣበት መንገድ እጅግ በርካታ እስረኞችን በመልቀቅ የተፈጸመ ነው።

በእስራኤል እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት አንድ ወታደር ለ1027 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ተለዋውጠዋል።

ከተፈቱት እስረኞች መካከል የተወሰኑት በግድያ ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን፣ በጋዛ ሰርጥ የሐማስ መሪ የሆነውና በመስከረም 26ቱ ጥቃት እስራኤል ተጠያቂ የምታደርገው ያህያ ሲንዋር ይገኝበታል።

በጥር 2004 (እአአ) በተመሳሳይ ከፍተኛ የሚባል እስረኛ ልውውጥ ተከናውኗል። መቀመጫውን በሊባኖስ ባደረገው እና በኢራን ከሚደገፈው ታጣቂ ሄዝቦላህ ጋር በተደረገ ስምምነት እስራኤል 436 ፍልስጤማውያን እና ሌሎች የአረብ እስረኞችን ልውውጥ አካሂዳለች።

ይህም በድንበር ኬላ ላይ ታፍነው የተወሰዱ ኤልሃናን ታኔንባም የተባለውን እስራኤላዊ ነጋዴ እና ሦስት የሞቱ የእስራኤል ወታደሮችን አስከሬን እንዲመለሱ በር ከፍቷል።

እስራኤል በበርካታ ፍልስጤማውያንን በመልቀቅ በምትኩ ከሐማስ ነጻ ያወጣችው ጊላድ ሻሊት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር

የፎቶው ባለመብት, Israel Defense Force

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በበርካታ ፍልስጤማውያንን በመልቀቅ በምትኩ ከሐማስ ነጻ ያወጣችው ጊላድ ሻሊት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር

የእስረኞች ቁጥር እየጨመረ ነው

የፍልስጤም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አዳሚር እንዳለው በእስራኤል የሚገኙ ፍልስጤማዊያን እስረኞች ቁጥር እየጨመረ ነው። እስከ መስከረም 25 ድረስ ብቻ ሰባት ሺህ ፍልስጤማውያን በእስራኤል በሚተዳደሩ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረዋል።

ይህም 80 ሴቶችን እና 200 የሚደርሱ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ያጠቃልላል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ ካደረሰው ጥቃት በኋላ ከሦስት ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ታስረዋል ሲል መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት አስታውቋል።

እስራኤል አዳሜርን ጨምሮ ስድስት የፍልስጤም ሲቪል መብቶች ቡድኖችን “አሸባሪ” ስትል በ2021 ፈርጃቸዋለች። የተባበሩት መንግሥታት እና የዓለም አቀፍ የመብቶች ቡድኖች ግን ፍረጃውን አይቀበሉትም።

በመስከረም 2023 መገባደጃ ላይ የእስራኤል እስር ቤት አገልግሎት 146 ታዳጊ ፍልስጤማውያንን በእስር ወይም በማረሚያ ቤት “ለደኅንነት” ብሎ በገለጸው ምክንያት አስሮ እንደነበር የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ቤተሰሌም ገልጿል።

በተመሳሳይ 34 ታዳጊ ፍልስጤማውያን በሕገወጥ መንገድ እስራኤል ውስጥ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበርም አገልግሎቱ አክሏል።

ሌላኛው የፍልስጤም መብት ድርጅት የፍልስጤም እስረኞች ክለብ ከሐማስ ጥቃት ወዲህ ስድስት እስረኞች በእስራኤል እስር ቤቶች መሞታቸውን ገልጿል።

ከሟቾቹ መካከል አምስቱ ከመስከረም 26 በኋላ የታሰሩ ናቸው።

በርካታ በእስራኤል እስር ቤት የሚገኙ ፍልስጤማውያን ድንጋይ መወርወርን ጨምሮ በቀላል ጥፋቶች የተከሰሱ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በርካታ በእስራኤል እስር ቤት የሚገኙ ፍልስጤማውያን ድንጋይ መወርወርን ጨምሮ በቀላል ጥፋቶች የተከሰሱ ናቸው

ክስም ፍርድም የለም

እስራኤል አንድ ሰው የቀረበበትን ክስ ሳይሰማ ወይም ችሎት ሳይቀርብ ሊታሰር የሚችልበት ‘አስተዳደራዊ እስር’ የሚባል አሰራር አላት። በዚህ የሚታሰሩት በዋናነት ፍልስጤማውያን ናቸው።

የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሃሞክድ እንዳለው እስራኤል ውስጥ 1070 ፍልስጤማውያን የአስተዳደር እስረኞች ነበሩ። ይህ ቁጥር በሐማስ ጥቃት ወቅት 1319 ነበር።

የሃሞክድ ዋና ዳይሬክተር ጄሲካ ሞንቴል ስምምነቱን በደስታ ተቀብለዋል።

“ሰዎችን አግቶ መያዝ በራሱ ሕገወጥ ነው፣ የጦር ወንጀል ነው። ሐማስ ሁሉንም ታጋቾች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መልቀቅ አለበት” ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል። “ይህን ዓላማ ለማሳካት እስራኤል እስረኞችን መፍታት አለባት” ብለዋል።

በእስራኤል እና ሐማስ ስምምነት መሠረት በአስተዳደራዊ እስር ላይ የሚገኙት ፍልስጤማውያን ሴቶች እና ሕጻናት እንደሚፈቱም ተናግረዋል።

“እነዚህ ሰዎችም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት ነበረባቸው። ስለዚህ የእስራኤል ታጋቾችን እና የፍልስጤም አስተዳደር እስረኞችን ለመፍታት የተደረገው ስምምነት ደስ የሚያሰኝ ነው።”

የተባበሩት መንግሥታት ትችት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፉት ዓመታት በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ትችት ሲሰነዝር ቆይቷል። ፍልስጤማውያን “በእስራኤል ወረራ” ስር “ሰፊ እና ስልታዊ የነፃነት እጦት” ገጥሟቸዋል ብሏል።

“ከ1967 (እአአ) ጀምሮ ሕጻናትን ጨምሮ ከ800 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደሮች በተደነገጉት፣ በተተገበሩት እና በተወሰኑት አምባገነናዊ ሕጎች በመሠረት ታስረዋል” ሲል ከ1967 ጀምሮ የፍልስጤም የተያዙ ግዛቶችን የተመለከተው የፍራንቸስካ አልባኒዝ ልዩ ራፖርት ገልጿል።

የተወረረችውን ዌስት ባንክን እንድትጎበኝ ባይፈቀድላትም ወደ ዮርዳኖስ ተጓዛ እና ከስድስት ወራት በላይ ቃለ መጠይቅ እንዳደረገች ተናግራለች።

እስራኤል ሪፖርቱን ከለመቀበል ባለፈ ተልዕኮዋ “በእስራኤል እና እስራኤላውያን ላይ አድልኦ” ያዘለ ዓላማ አለው ብላለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሴቭ ዘ ችልድረን የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በየዓመቱ ከ500 እስከ 700 የሚደርሱ ፍልስጤማውያን ሕጻናት ወደ እስራኤል ወታደራዊ እስር ቤት ይገባሉ ብለዋል።