ኳታር ደመኞቹን እስራኤልን እና ሐማስን እንዴት ከስምምነት እንዲደርሱ አስቻለች?

ኳታር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኳታር ትንሽ አገር ናት። ልቧ ግን ትልቅ ነው።

ኳታር ድሃ አገር ነበረች። አሁን ታሪክ ተቀይሯል።

ኳታር የምዕራቡ ዓለም ወዳጅ ናት። አሸባሪ የሚባሉ ቡድኖችም አለኝታችን ይሏታል። መጠጊያችን ይሏታል።

‘በአሸባሪም’ እና ‘በተሸባሪም’ መወደድ መቻል መታደል ነው። በሁለቱም መወደድ እና መታመን መታደል እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

ውሃ እና ዘይትን ቀላቅሎ የሰመረለት እንደ ዶሃ ማን አለ?

ለዚህም ነው የአሁኑን አይነት አገራትን ወይም ዓለምን ያስጨነቀ ቀውስ በተፈጠረ ተቀናቃኞችን ለማገናኘት ድልድይ በመሆን ኳታር ተሳክቶላታል።

እርግጥ ማደራደር ለኳታር አዲስ አይደለም። ሐማስ እና እስራኤልን ቀርቶ ትራምፕን ከታሊባን ጋር አደራድራ ሰምሮላታል።

ትራምፕ እና ታሊባን ማለት ደግሞ እሳትና ጭድ፣ ሰሜን ዋልታ እና ደቡብ ዋልታ እንደማለት ናቸው። የሁለት ዓለም ሰዎች።

ሐማስ እና እስራኤልም እንደዚያው ናቸው።

ምዕራባውያን እና እስራኤል ደመኛ ጠላቶቻችን የሚሏቸው የፖለቲካ እና የሃይማኖት ቡድኖች መቀመጫቸው ኳታር ነው።

ታሊባን በዶሃ ቢሮ የከፈተው ድሮ ነው። ሐማስም እንዲሁ።

የሐማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ያለው ዶሃ ነው። ኢስማኤል ሃኒያን እስራኤል በነፍስ ትፈልገዋለች። ግን ደግሞ ዕድሜ ለኳታር አስጠልላዋለች።

ኳታር ውሃ እና ዘይትን ማወደድ ብርቋ አይደለም።

ከዚህ ቀደም የደኅንነት ቁልፍ ሰዎቻቸውን በመጠቀም በኢራቅ እና በሶሪያ አይሲስ ያገታቸውን ምዕራባውያንን ለማስለቀቅ ቁልፍ ሚና ነበራት።

ሩሲያ እና ዩክሬንን ሳይቀር አቀራርባ ታውቃለች።

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በቀጥታ መነጋገር ስለማትችል ውክልናውን የሰጠችው ለትንሿ የባሕረ ሰላጤ አገር ኳታር ነበር።

የኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሐማድ አል ታኒ

የፎቶው ባለመብት, AP

የምስሉ መግለጫ, የኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሐማድ አል ታኒ

ሁሉም ተስፋ ያደረጉባት ኳታር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ መቅሰፍት የመሰለ የጋዛ እስራኤል ጦርነት ሲጀመር ሁሉም ደንግጧል። ጠላትም ወዳጅም ቶሎ ስልክ የመታው ግን ወደ ኳታር ነበር።

ፍልስጤማውያን የእስራኤል እሳት ጋብ እንዲል ለተኩስ አቁም ተስፋ ያደረጉባት፣ ምዕራባዊያን የታገቱትን ልጆቻቸው በሰላም እንድታስመልስላቸው አደራ ሰጥተዋታል - ለኳታር።

ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ ያቺ ትንሽ አገር ከእነዚህ ትልልቅ ተስፋዎች ምን ያህሉን እንደምታሳካ ዓለም በጉጉት ሲጠብቅ ነበር።

የሁለት በነፍስ የሚፈላለጉ ቡድኖች ‘ወዳጅ’ አገር ናት ኳታር አላሳፈረችም። በሁለት ጠላቶች እምነት የሚጣልባት ኳታር በመጨረሻ ተሳክቶላታል።

ዛሬ አርብ ጠዋት ሺዎችን ለሞት የዳረገው እና ሚሊዮኖች የጋዛ ነዋሪዎችን በመሠረታዊ አቅርቦት መቋረጥ ምክንያት እልቂት አፋፍ ላይ ያደረሰው የእስራኤል ኃያል ወታደራዊ ዘመቻ ገብ እንዲል አስችላለች።

ይህንን ተከትሎ ደግሞ ሐማስ አግቶ ከእስራኤል ከወሰዳቸው ከ200 በላይ ሰዎች መካከል የተወሰኑትን ሴቶች እና ሕጻናትን እንደሚልቅ ይጠበቃል።

ይህም ከአንድ ወር በላይ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን የምድር፣ የአየር እና የባሕር ወታደራዊ ዘመቻን ለቀናትም ጋብ ያደርጋል ተብሏል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛውን ምስጋና የምታገኘው ትንሿ ግን ኃያል እየሆነች ያለችው ኳታር ናት።

ስምምነቱ ለቀናት ሰብአዊ እርዳታን ለማድረስ ከማስቻሉ ባሻገር ለቀጣይ ድርድር በር ይከፍታልም ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ምንም እንኳን አስራኤል ቀዳሚ ግቤ የታገቱ ሰዎችን ማስለቀቅ ከዚያም ሐማስን ከምድረ ጋዛ መጠራረግ ነው ብትልም ኳታር ዘላቂ ስምምነት እንዲደረስ መጣሯን ትቀጥላለች።

ይህ የተኩስ አቁም ፋታ በከባድ ሰቆቃ ውስጥ ላሉት ፍልስጤማውያን እርዳታ እና እፎይታን እንዲሁም በእገታ ስር ላሉት ነጻነትን ከማስገኘቱ ባሻገር የኳታርን ስምም በበጎ እንዲነሳ እያደረገ ነው።

ባለጸጋዋ ኳታር ከዓመታት በፊት ቢሊዮኖችን አፍስሳ አልጀዚራን የመሰለ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን ከፍታ መላው ዓለምን በመድረስ መልካም ስሟን ስትገነባ ቆይታለች።

ባለፈው ዓመት ደግሞ የምድራችንን ታላቁን የእግር ኳስ ውድድር በስኬት አስተናግዳ የዓለምን አድናቆት ለመግኘት ችላለች።

አሁን ደግሞ ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጀምሮ የዓለምን ቀልብ ሰቅዞ በመያዝ ስጋትን ፈጥሮ የሰነበተውን የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ጋብ እንዲል ለማድረግ አስችላለች።