ሐማስ ማነው? በጋዛ ሰርጥስ ምን ተፈጠረ? ሊያውቋቸው የሚገቡ ወሳኝ ጥያቄዎች

የፎቶው ባለመብት, ASHRAF AMRA/ANADOLU AGENCY VIA GETTY IMAGES
የፍልስጥኤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ታይቶ የማይታወቅ የተባለለትን የተቀናጀ ጥቃት እስራኤል ላይ ሰንዝሯል። ተዋጊዎቹም በጋዛ ሰርጥ አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎችን ገድለዋል፣ አግተዋል።
ስለተሳታፊዎቹ እና ስለጥቃቱ ቦታዎች ማወቅ ያለብዎት ነገር ወሳኝ መረጃዎችን እንደሚከተለው አጠናቅረናል።
ሐማስ ማን ነው?
ሃማስ የጋዛን ሰርጥ የሚያስተዳድር የፍልስጥኤም እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ነው።
ሃማስ እስራኤልን ለማጥፋት ቃል የገባ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2007 ጋዛን ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ እስራኤል ላይ በተደጋጋሚ ነፍጥ አንስቷል።
በእነዚህ ጦርነቶች ወቅት ሌሎች ቡድኖች ጭምር በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል እንዲተኩሱ አድርጓል ወይም ፈቅዷል። ህይወት የቀጠፉ በርካታ ጥቃቶችንም አድርሷል።
እስራኤልም ሐማስ ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት ፈጽማለች። እአአ ከ2007 ጀምሮ ከግብጽ ጋር በመሆን ለደህንነት ነው በማለት የጋዛ ሰርጥን ከበባ ውስጥ አስገብታዋለች። ማንኛውም እንቅስቃሴንም ያለ አስራኤል ፈቃድ ማድረግን አግዳለች።
ሐማስ እንደ ቡድን ወይም ደግሞ በአንዳንድ ሁኔታዎች ወታደራዊ ክንፉ ለብቻው በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ህብረት፣ በእንግሊዝ እንዲሁም በሌሎች ሃገሮች በአሸባሪነት ተፈርጇል። ሐማስ በኢራን ይደገፋል። የቴህራን ድጋፍ ከገንዘብ እስከ ጦር መሳሪያ እና ስልጠና ይደርሳል።
የጋዛ ሰርጥ ምንድን ነው?
የጋዛ ሰርጥ በእስራኤል፣ በግብጽ እና በሜዲትራኒያን ባህር መካከል 41 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 10 ኪ.ሜ ስፋት ያለው አካባቢ ነው።
2.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መኖሪያ ሲሆን በዓለም ላይ ከፍተኛ ህዝብ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። ለ16 ዓመታት ያህል የቆየ ከበባ ውስጥ ይገኛል
እስራኤል በጋዛ እና በአካባቢው የአየር፣ የመሬት እና የባህር እገዳ የጣለች ሲሆን በድንበሮች በኩል የሚገቡ ሸቀጦችንም ሆነ ዕቃዎች በተመለከተ የእስራኤል መንግሥት ሊፈቅድ ይገባል።
በተመሳሳይ ግብጽ በራሷ ወሰን በጋዛ ድንበር በኩል የሚገቡ እና የሚወጡትን ትቆጣጠራለች።

የፎቶው ባለመብት, SAID KHATIB/AFP
ፍልስጥኤም ብለን የምንጠራው የትኛውን ነው? እነዚህን ክስተቶችስ ከፍልስጥኤም ጋር ምን ያገናኛቸዋል?
የፍልስጥኤም ግዛቶች በመባል የሚታወቁት ዌስት ባንክ እና ጋዛን ጨምሮ ምስራቅ እየሩሳሌም እና እስራኤል ሁሉም ከሮማውያን ዘመን ጀምሮ ፍልስጥኤም በመባል የሚታወቀውን ምድር መሥርተዋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ እነዚህ ቦታዎች የአይሁድ መንግስት አካል የነበሩ እና በአይሁዶች ዘንድ እንደ ጥንታዊ አገራቸው ይመለከቷቸዋል።
እስራኤል እንደሃገር የተመሠረተችው በአውሮፓውያኑ 1948 ነው። እስራኤል በወረራ ነው የያዘቻቸው በሚል እንደ ሃገር ዕውቅና የማይሰጡ አካላት አሁን ድረስ እነዚህን ቦታዎች እንደ ፍልስጥኤም ይቆጥራሉ።
በተጨማሪም ፍልስጥኤማውያን ፍልስጥኤም የሚለውን ስም የሚገልጹት ዌስት ባንክ፣ ጋዛ እና ምስራቅ እየሩሳሌም ግዛቶችን በማካተት ነው።
እስራኤል እና ሐማስ ለምን ይዋጋሉ?
በእስራኤል እና ሐማስ መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ የማያቋርጥ ውጥረት አለ።
የቅዳሜው ጥቃት የተፈጸመው ግን ሳይጠበቅ ነው።
ሐማስ በእስራኤል ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ተኩሷል። በደርዘን የሚቆጠሩ ተዋጊዎቹም ድንበር ጥሰው እስራኤልን በመውረር በደርዘን የሚቆጠሩ ሠላማዊ ዜጎችን ገድለው በርካቶችን ደግሞ በምርኮ ወስደዋል።
እስራኤል በምላሹ በጋዛ በሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ያለችውን ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን እየፈጸመች ትገኛለች።
ይህ ጥቃት ምን ያህል ያልተለመደ ነው?
ይህ ሐማስ ከጋዛ የሰነዘረው ከፍተኛ የተቀናጀ ጥቃት ሲሆን እስራኤል ከረዥም ጊዜ በኋላ የገጠማት ከባድ ድንበር ዘለል ጥቃት ነው።
ታጣቂዎች ጋዛን ከእስራኤል የሚለየውን የሽቦ ድንበር እና ማገጃ በተለያዩ ቦታዎች ጥሰው ገብተዋል።
ከ50 ዓመት በፊት ግብጽ እና ሶሪያ ያልተጠበቀ ጦርነት እስራኤል ላይ ከፍተው ነበር። ይህ ጦርነት 50 ዓመት በደፈነ ማግስት ነው የአሁኑ ጥቃት የተሰነዘረው።
ይህ ለእስራኤል የስለላ ተቋማት እንደውድቀት ይቆጠራል?
አዎ ይላል የቢቢሲው የደህንነት ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር። የእስራኤል የሃገር ውስጥ የስለላ ድርጅት ሺን ቤት ይባላል። ከሃገር ውጭ ያለውን የስለላ ተግባር ደግሞ ሞሳድ በበላይነት ይመራዋል።
የእስራኤል መከላከያ አደረጃጀቶችን ጨምሮ ሁለቱ የስለላ ተቋማት ጥቃቱ እንደሚፈጸም አለማወቃቸው እና ምንም እርምጃ በፍጥነት አለመውሰዳቸው አስገራሚ ነው ሲል አክሏል።
እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ ካሉ ሃገራት እጅግ በጣም ትልቅ እና በከፍተኛ ገንዘብ የተደገፈ የስለላ ድርጅት አላት። መረጃ አቀባዮችንም በፍልስጥኤም ታጣቂ ቡድኖች ውስጥ ያላት ሲሆን በሊባኖስ፣ ሶሪያ እና ሌሎች ሃገራትም ወኪሎች አሏት ።
በጋዛ እና በእስራኤል መካከል ባለው እና በውጥረት በተሞላው የድንበር አጥር ላይ ካሜራዎች፣ እንቅስቃሴ የሚለዩ ማሽኖች እና መደበኛ የጦር ሰራዊት ጥበቃ አይለየውም።
በአደገኛ ሽቦ የተሸፈነውን አጥር ሰርጎ ለመግባት ከባድ እንደሆነ ይታሰብ ነበር።
ሆኖም የሐማስ ታጣቂዎች በቀላሉ በቡልዶዘር አፍርሰው፣ ሽቦውን በቆርጠው ወይም በባህር እና በበራሪ መሣሪያዎች ተጠቅመው ወደ እስራኤል ገብተዋል።
ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ይችላል?
የሐማስ ታጣቂዎች አዛዥ መሐመድ ዴይፍ ፍልስጥኤማውያን እና ሌሎች የአረብ ታጣቂዎች “የእስራኤልን ወረራ ለመመከት” የሚወስደውን እርምጃ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቀጣዩ ጥያቄ በዌስት ባንክ እና በምስራቅ እየሩሳሌም የሚገኙ ፍልስጤማውያን ጥሪውን ይቀበሉታል ወይ የሚለው ነው።
እስራኤል ያለጥርጥር በበርካታ አቅጣጫዎች ጥቃት ሊፈጸምባት እንደሚችል ትገምታለች።
ጠንካራው የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ተሳታፊ ከሆነ ጉዳዩን ሊያባብሰው ይችላል።
እሑድ ጠዋት ላይ ሄዝቦላህ በርካታ ሚሳኤሎችን ወደ ሰሜን እስራኤል ተኩሷል። በጥቃቱ ግን እስካሁን ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች አለመኖራቸው ታውቋል።
እስራኤል ጦሯ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጠናከር ትዕዛዝ አስተላልፋለች። በጋዛ ከምትፈጸመው ከባድ የአየር ጥቃት በተጨማሪ በምድርም ዘመቻ ለማድረግ ማቀዷ ተመላክቷል።












