ሐማስ ማንም ይሆናል ብሎ ያላሰበውን መብረቃዊ ጥቃት እንዴት ሊፈፅም ቻለ?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጥቃቱ ሲጀምር በርካታ እስራኤላውያን ተኝተው ነበር።
ቅዳሜ የአይሁዶች የእረፍት ቀን እንዲሁም ቅዱስ የበዓል ቀን ነው።
በዚህ ዕለት ቤተሰቦች በቤት ውስጥ አሊያም በጋራ ፀሎት በሚያካሂዱበት ቦታ ተሰባስበው ያሳልፋሉ፤ ጓደኛማቾችም ተገናኝተው የሚዝናኑበት ዕለት ነው።
ነገር ግን ማለዳው በድንገተኛ ሮኬቶች ተኩስ ተጀመረ።ይህ መጠነ ሰፊ እና ቅንጅት ያለው ጥቃት ይፈጠራል ብሎ ያሰበ አልነበረም።
ለዓመታት እስራኤል በራሷ እና በፍልስጥኤም የጋዛ ግዛት መካከል ያለውን ድንበር ያጠናከረች ቢሆንም በሰዓታት ውስጥ በተፈፀመው በዚህ ጥቃት አይደፈሬነቷ ጉድለት እንዳበት ተጋልጧል።
ቢቢሲ ሐማስ እንዴት የተቀናጀ እና ውስብስብ የሆነ ጥቃት ከጋዛ ሊፈፅም እንደቻለ የሚያሳዩ በታጣቂዎች እና በሰላማዊ ሰዎች የተቀረጹ ምስሎችን ተንትኗል።
የጥቃቱ አጀማመር
ሮኬቶች መወንጨፍ የጀመሩት በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት 12፡30 አካባቢ ነው።
ጋዛን የሚቆጣጠረውና በዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም በሌሎች አገራት በአሸባሪነት የተፈረጀው የእስላማዊ ታጣቂ ድርጅት ይህን ስልቱን በተደጋጋሚ ተጠቅሟል።
መጀመሪያ ላይ የተተኮሱት ሮኬቶች የእስራኤልን ዘመናዊ የሚሳይል መከላከያ ሥርዓት ለማለፍ ብዙ ጊዜ ታግለዋል።
ሆኖም የሐማስ ታጣቂዎች ይህንን ሥርዓት ለማጨናነቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ተኩሰዋል።ይህም ለወራት የታሰበበት እና የታቀደበት እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
ሐማስ በመጀመሪያው ዙር 5 ሺህ ሮኬቶችን መተኮሱን ገልጿል።እስራኤል ግን የተተኮሰው የሮኬት ብዛት የዚህ ግማሽ ነው ብላለች።
ሐማስ የፈጸመውን ዓይነት ውስብስብ እና የተቀናጀ ጥቃት ለመፈፀም ጥንቃቄ የተሞላበትና ዝግጅት ማድረግ የሚፈልግ እንደሆነ ይታመናል።
ለዚህም ከእስራኤል የስለላ እና የመከላከያ አፍንጫ ሥር በመሆን የተተኮሱትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን የማንቀሳቀስ እና የማከማቸት ሥራ በሐማስ በኩል እጅግ ለየት ያለ ጥንቃቄን የሚፈልግ የደኅንነት ተልዕኮን የሚጠይቅ ነው።
ይህ ጥቃት ከ50 ዓመት በፊት በእስራኤል ላይ የተፈጸመው የዮም ኪፑር ጥቃት ጋር በተመሳሳይ ዕለት መፈጸሙ እንዴት ሊሆን ቻለ በማለት የእስራኤል የመገናኛ ብዙኃን የአገራቸው ወታደራዊ እና የፖለቲካ መሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ እየጠየቁ ነው።
ቅዳሜ ማለዳ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ድምጾች ከጋዛ በ60 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ቴል አቪቭ መሰማት የጀመረ ሲሆን ጥቃቱ ከተፈፀመባቸው ከተሞች ጭስ ሲወጣም ታይቷል።
የሮኬቶቹ ጥቃት ተጠናክሮ ሲቀጥል ተዋጊዎቹ የጋዛን ጥብቅ አጥር አልፈው ለመግባት በማሰብ እየተሰባሰቡ ነበር።
ምንም እንኳን እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ በ2005 ወታደሮቿን እና ነዋሪዎቿን ከጋዛ ብታስወጣም የአየር ክልሏን፣ የጋራ ድንበሯን እና የባህር ዳርቻዋን ትቆጣጠራለች።
በዚያም አካባቢ መደበኛ ወታደራዊ ጥበቃዎችንም ታካሂዳለች። ከዚህም በተጨማሪ ወረራን ለመከላከል በኔትወርክ የሚሰሩ ካሜራዎችና ሴንሰሮችን ገጥማለች።
ይሁን እንጂ በሰዓታት ውስጥ ይህ ጥብቅ አጥር በተደጋጋሚ ተጥሷል።
ሐማስ አጥሩን ጥሶ እንዴት ሊገባ ቻለ?
አንዳንድ የሐማስ ተዋጊዎች ሙሉ በሙሉ አጥሩን አልፈው ለመግባት ሞክረው ነበር።አንድ በቢቢሲ ያልተረጋገጠ ቪዲዮ እንደሚያሳየውም ቢያንስ ሰባት ወታደሮች በፓራሹት መሳይ መንሳፈፊያ በአጥሩ ላይ በመንሳፈፍ እንዲሁም በጀልባ አቋርጠው ገብተዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሐማስ በባህር ዳርቻው ላይ መርከቦችን በማሳረፍ ወደ እስራኤል ለመግባት ያደረገውን ሁለት ሙከራዎች እንዳከሸፈ ገልጿል።
ሆኖም ይህንን ጥቃት ለየት የሚያደርገውም በድንበር ማቋረጫ ቦታዎች ላይ የተፈፀሙት በርካታ የተቀናጁ ቀጥተኛ ጥቃቶች ናቸው።
ማለዳ 11፡50 አካባቢ ከሐማስ ታጣቂ ክንፍ ጋር ግንኙነት ያለው የቴሌግራም ገጽ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ የሚያሳየውንና በኬረም ሻሎም የተነሳ የመጀመሪያውን ምስል አጋርቷል።ይህ አካባቢ በጋዛ ድንበር ደቡባዊ ክፍል የሚገኝ ነው።
በምስሉ ላይ ታጣቂዎች ሲሮጡ እና በደም የተለወሱ የእስራኤል ወታደሮች አስክሬን መሬት ላይ ወድቀው ታይተዋል።
ሌላ ምስልም እያንዳንዳቸው ሁለት ታጣቂዎችን ያሳፈሩ ቢያንስ አምስት ሞተር ሳይክሎች በሽቦ በታጠረው ድንበር ላይ ባለው ቀዳዳ ሲያልፉ አሳይተዋል።
ብዙ ጥበቃ በሌለው አቅጣጫም በሽቦ የታጠረው አጥር በቡልዶዘር ሲፈርስ ታይቷል።
በርካታ ያልታጠቁ የሚመስሉ ሰዎች እዚያ ተሰብስበው የነበረ ሲሆን የተወሰኑት በክፍተቱ እያለፉ ሲሮጡም ነበር።
ሐማስ ከጋዛ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ከኬረም ሻሎም በ43.4 ኪሎ ሜትር በሚርቀው ኤረዝ ሌላ መግቢያም ፈጥሮ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA
ይህ ምስል በታጣቂ ቡድኑ የፕሮፖጋንዳ ማስተላለፊያ ሚዲያ ላይ ተጋርቷል።
በምስሉ ላይ በኮንክሪት አጥሩ ላይ ፍንዳታ ሲከሰት እና ተዋጊዎች ወደ ፍንዳታው ቦታ እንዲመጡ ምልክት ሲሰጡ ታይቷል።
ከዚያም የጥይት መከላከያ ሰደርያ የለበሱ እና ጥይት የያዙ ስምንት ወንዶች ጥብቅ ቁጥጥር ወደሚደረግበት ፍተሻ ጣቢያ በመሮጥ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ተኩሰዋል።
በኋላ ላይ በቪዲዮው ላይ ታጣቂዎቹ ከክፍል ክፍል እየተዘዋወሩ ግቢውን ሲያስሱ እና የእስራኤል ወታደሮች መሬት ላይ ወድቀው ታይቷል።ይህም በግልጽ የተደራጁ እና የሰለጠኑ መሆናቸውን ያሳያል።
ጋዛ ሰባት የሚደርሱ ይፋዊ መሻገሪያዎች አሉት።ስድስቱ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ሲሆኑ ወደ ግብፅ የሚያሻግረው አንደኛው ደግሞ በካይሮ ቁጥጥር ሥር ይገኛል።
ሆኖም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ባገኘው ክፍተት ሐማስ በረዥሙና በማይደፈረው አጥር አልፎ ወደ እስራኤል ዘልቆ መግባት ችሏል።

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA
ጥቃቱ ወደ እስራኤል ግዛት ዘልቆ ገብቷል
የሐማስ ተዋጊዎች በሁሉም አቅጣጫ ከጋዛ ተጠራርገው ወጥተዋል። የእስራኤል ባለሥልጣናት እንዳሉት 27 የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን ያገኙትን ሰው እንዲገሉ የታዘዙ ይመስላሉ።
ሐማስ ራቅ ወዳለው የእስራኤል ግዛት ዘልቆ በመግባት ጥቃት የፈፀመው ከጋዛ በስተምስራቅ 22.5 ኪሎሜትር በምትርቀው በኦፋኪም ከተማ ላይ ነው።

በስዴሮት ውስጥ ታጣቂዎች በፒክ አፕ መኪና ላይ ቆመው ወደ ከተማዋ ሲገቡም ታይተዋል። ስደሮት ከምስራቃዊ ጋዛ 3 ኪሎ ሜትር የምትርቅ ከተማ ነች።
በርካታ የታጠቁ ተዋጊዎችም ጭር ባሉት የአሽኬሎን መንገዶች ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል።
ተመሳሳይ ሁነቶችም በደቡባዊ እስራኤል የታዩ ሲሆን፣ሰላማዊ ሰዎች ቤት ውስጥ እንዲደበቁ በታጣቂዎቹ ተነግሯቸዋል።
በሬኢም አቅራቢያ በተካሄደው የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ በታደሙ ወጣቶች ላይም ታጣቂዎቹ የተኩስ ሩምታ ከፍተዋል።
አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ መሳሪያ የጫነ መኪና ሲያሽከረክሩ የነበረ ሲሆን ሌሎች እስራኤላውያንን ኢላማ ለማድረግ ሦስት ሰዓታት የፈጀ አሰሳ አድርገዋል።
ወታደሮች እና ሰላማዊ ሰዎች ታግተዋል
ከሙዚቃ ድግስ ላይ እንዲሁም ከሌሎች አካባቢዎች ሰዎች ታግተው ወደ ጋዛ መወሰዳቸውን ቢቢሲ መረዳት ችሏል። እስራኤል 100 የሚሆኑ ወታደሮች እና ሰላማዊ ሰዎች ተጠልፈው መወሰዳቸውን አስታውቃለች።
በቤሪ ከተማ የተቀረጸና በቢቢሲ የተረጋገጠ ምስል አራት ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች ተገደው ሲወሰዱ አሳይቷል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚዘዋወሩ በርካታ ቪዲዮዎችም እስራኤላውያን፣አንዳንዶቹ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው በጋዛ የተጨናነቁ መንገዶች ተይዘው ሲወሰዱ አሳይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA
ሐማስ የእስራኤል ማኅበረሰቦችን ኢላማ ከማድረግ በተጨማሪ በዚኪም እና ሬኢም በሚገኙ ሁለት የእስራኤል የጦር ሠፈሮች ላይ ጥቃት ፈፅሟል።
ከሬኢም አቅራቢያ የተነሱ ምስሎች በርካታ የተቃጠሉ መኪናዎችን ጨምሮ ከጥቃቱ በኋላ ያለውን ሁኔታ አሳይተዋል።ይሁን እንጂ በዚህ ግጭት ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ግልጽ አይደለም።
የሐማስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በተደጋጋሚ የሞቱ የእስራኤል ወታደሮችን ምስል አጋርተዋል ።ሆኖም ምስሎቹ በቢቢሲ አልተረጋገጡም።
የሮኬት ጥቃቱ ሲጀመር በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ሞተዋል።ይህም ማንም ሰው ይሆናል ብሎ ባለሰበው መንገድ የተፈፀመ ነው።
በጥቃቱ ክፉኛ በተመታችው ደቡባዊ ክፍሏ በፍጥነት እርዳታ ማቅረብ የተጀመረ ሲሆን፣ሐማስ ለተወሰነ ጊዜ ከጋዛ ውጭ ያሉ አነስተኛ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ ነበር ።
በፍጥነቱ እና በገዳይነቱ ያልተጠበቀው ድንገተኛ ጥቃት እስራኤልን አስደንግጧታል።ምን አልባት ይህ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ የዓመታት ጥያቄ ሆኖ ሊዘልቅ ይችላል።
ጥቃቱ በተጀመረበት ቀን ረፋድ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ ጦርነት ላይ ነን!” ሲሉ አውጀዋል።












