በጊኒ ቢሳዎ ምርጫ ከተካሄደ ከሦስት ቀናት በኋላ ወታደሮች ሥልጣን መቆጣጠራቸውን አስታወቁ

ጦር ሠራዊቱ አገሪቱን መቆጣጠሩን ወታደሮች በቴሌቪዥን ቀርበው ሲያሳወቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጦር ሠራዊቱ አገሪቱን መቆጣጠሩን ወታደሮች በቴሌቪዥን ቀርበው ሲያሳወቁ

የጊኒ ቢሳዎ ወታደሮች በአገሪቱ የፕሬዝዳንት ምርጫ ከተካሄደ ከሦስት ቀናት በኋላ ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥር ስር አውለው መላዋ አገሪቱን መቆጣጠራቸውን አስታወቁ።

የጦር መኮንኖቹ ፕሬዝዳንት ኦማሮ ሲሶኮ ኤምባሎን መያዛቸወን ያስታወቁት ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በዋና ከተማዋ ቢሳዎ በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ ከባድ ተኩስ ከተሰማ በኋላ ነው።

ወታደሮቹ እሁድ ዕለት የተካሄደው እና ወጤቱ ሐሙስ ይታወቃል ተብሎ እየተጠበቀ የነበረውን የምርጫ ሂደት በማገድ ሁሉንም የአገሪቱን ድንበሮችን እንዲዘጉ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

የፕሬዝዳንቱ መታሰር እና የወታደራዊ አመራሮች ሥልጣን መያዝ የተሰማው በአገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ዋነኛው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ከውድድር ውጪ መደረጋቸው ከተሰማ ከሦስት ቀናት በኋላ ነው።

የምርጫው ውጤት ነገ ሐሙስ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ ነበረ። ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲስኮ ኤምባሎ እንዲሁም ዋነኛ ተፎካካሪያቸው ፈርናንዶ ዲያዝም በምርጫው እንዳሸነፉ ገልጸዋል።

በዋና ከተማዋ የሚኖሩ የዐይን እማኞች ዛሬ ከሰዓት የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ገልጸዋል። ሆኖም ግን ተኩሱ በማን እንደተጀመረ እና የሞቱ ሰዎች ስለመኖራቸው ግልጽ አይደለም።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እንደዘገበው፤ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእግራቸው እንዲሁም በመኪና ሸሽተዋል።

ሥልጣን የተቆጣጠሩት ወታደራዊ መኮንኖች ኋላ ላይ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው "ሥርዓት አስከባሪ ከፍተኛ ወታደራዊ ዕዝ" የተባለ አካል ተጨማሪ መግለጫ እሰኪሰጥ ድረስ አገሪቱን እንደሚመራ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥራቸው ስር ያዋሉት ወታደሮች በተጨማሪም ሕዝቡ "እንዲረጋጋ" አዝዘዋል።

ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች በወታደሮቹ ቁጥጥር ስር ውለው እንደሆነ አስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ቀደም ሲል የፕሬዝንቱ ቃል አቀባይ የታጠቁ ሰዎቸ ዒላማ ያደረጉት እሁድ ዕለት የተካሄደውን ምርጫ የመራው የምርጫ ኮሚሽን መሥሪያ ቤትን መሆኑን እና ዓላማቸውም ኮሚሽኑ የአወዛጋቢውን ምርጫ ውጤት እንዳያሳውቁ ለማድረግ ነው ብለው ነበር።

በወታደሮቹ ቁጥጥር ስር የዋሉት ፕሬዝዳንት ኦማሮ ሲሶኮ ኤምባሎ በምርጫው ለሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን የተወዳደሩ ሲሆን፣ እርሳቸውም ሆኑ ተፎካካሪያቸው ውጤቱ ከመታወቁ በፊት አሸናፊ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።

ጊኒ ቢሳዎ ከቅኝ ግዛት ከወጣች በኋላ ተደጋጋሚ መፈንቀለ መንግሥት እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሲያጋጥማት ቆይቷል።

ጊኒ ቢሳው ወደ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች አሏት። በዓለም እጅግ ድሃ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ናት።

በፖርቹጋል ቅኝ በተገዛችው ጊኒ ቢሳዎ ከአወሮፓውያኑ 1980 ወዲህ ዘጠኝ መፈንቅለ መንግሥቶች ተካሂደዋል።

ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲስኮ ኤምባሎን ከሥልጣን ለማውረድ ሁለት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተካሂደዋል።

የመጨረሻው የመፈንቅ መንግሥት ሙከራ የነበረው ጥቅምት 2023 ነበር።

ኡማሮ ሲስኮ ኤምባሎ

የፎቶው ባለመብት, Corbis via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኡማሮ ሲስኮ ኤምባሎ