የጊኒ ቢሳው ዋና ከተማ የመብራት ስላልከፈለች ጨለማ ውጧታል

የፎቶው ባለመብት, AFP
የጊኒ ቢሳው ዋና ከተማ መብራት ጠፍቷል። ምክንያቱ ደግሞ የመብራት ክፍያ በማዘግየቷ ነው።
ለዋና ከተማዋ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያቀርበው ካርፓውርሺፕ የተባለ የቱርክ ኩባንያ ነው።
“ከተማዋ ውዝፍ ዕዳ ስላልከፈለች ባልቦላውን አጥፍቼዋለሁ’’ ብሏል ኩባንያው።
ቢሳው ያልከፈለችው የመብራት ሒሳብ 15 ሚሊዮን ዶላር ነው።
አሁን ከተማዋን ጨለማ ውጧታል። ሆስፒታሎች፣ ራዲዮ ጣቢያዎች ሳይቀሩ ሥራ ለማቆም ተገደዋል።
የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ሱለይማኔ ሴይዲ ችግሩ መፈጠሩን አምነው ዕዳችንን በ15 ቀን ውስጥ እንከፍላለን ብለዋል።
የቱርኩ ካርፓወርሺፕ ኩባንያ ከቢሳው ሌላ ለበርካታ የአፍሪካ አገራት ኃይል በማቅረብ ይታወቃል።
ኃይል የሚያቀርብበት መንገድም የተንሳፋፊ ኃይል አቅርቦት ተብሎ ይጠራል።
በዓለም ግዙፍ ከሚባሉ የኃይል አቅራቢዎች አንዱ የሆነው ይህ ኩባንያ ሒሳብ የማይከፍሉ ከተሞች ላይ ቆራጥ እርምጃ ይወስዳል።
ባለፈው ወር የሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶባት ነበር። 40 ሚሊዮ ን ዶላር ዕዳ ባለመክፈሏ መብራት አጥፍቶ ነበር በፍሪታውን።
ይህ የቱርክ ኩባንያ ለደቡብ አፍሪካ ኃይል ለማቅረብ ስምምነት የደረሰ ሲሆን የአገሪቱን 5 ከመቶ የኃይል ፍላጎት ሊሸፍን ተሰናድቷል።
በደቡብ አፍሪካ የፈረቃ ሥርዓት የተዘረጋ ሲሆን አንዳንድ ሰፈሮች ለ10 ሰዓት ያህል በቀን ኃይል ሳያገኙ ይቆያሉ።
የጊኒ ቢሳው ዋና ከተማ ቢሳው 400ሺህ ሕዝብ ይኖርባታል።
መብራት ሙሉ በሙሉ በመጥፋቱ የሕዝብ ሆስፒታሎች ጄኔሬተር ለመጠቀም ተገደዋል።በበርካታ ሰፈሮችም የቧንቧ ዉሃ ተቋርጧል።
በከተማዋ እስከ 40 ዲግሪ የሚደርስ ሙቀት በመኖሩ ከኃይል መቋረጥ ጋር ተደማምሮ ዉሃ አቅርቦትም በመስተጓጎሉ በቢሳው ሕይወት ፈታኝ ሆኗል።
“ቀን ቤት መግባት የማይሞከር ነው። ማታም እንደዚሁ። ሙቀቱ ኃያል ነው። ምሽት ሰው እስከ እኩለ ሌሊት ደጅ ነው የሚቆየው። ቤት ውስጥ ያለው ሙቀት የሚያስተኛ አይደለም'' ይላል በዚያ የሚገኝ አልቤርቶ ዳቦ የሚባል ጋዜጠኛ።
‘’ራዲዮ ናሽናሌ’’ የተሰኘው የከተማዋ የሬዲዮ ጣቢያ ሥርጭት ለማቆም ተገዷል።
የኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢሱፍ ባልዴ ካለብን ከ15 ሚሊዯን ዶላር ዕዳ 6 ሚሊዮን ከፍለናል፤ ትንሽ ነው የሚቀርብን ብለዋል።
የቱርኩ ኩባንያ ለጊኒ ቢሳው 100 % የኤሌክትሪክ ፍላጎት እያቀረበ ይገኛል። ይህም የጀመረው ከአገሪቱ የዉሃና ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ጋር የአምስት ዐመት ስምምነት ከደረሰ በኋላ ነው።
የኢንርጂ ሚኒስትሩ እንደሚሉት ከቱርኩ ኩባንያ ጋር በታሪክ ጉዳይ በድጋሚ መደራደር ያስፈልጋል። ለመብራት የሚጠይቀው ዋጋ ከጊኒ ቢሳው አቅም በላይ ሆኗል።
ይህ የቱርክ ኩባንያ ለጋና፣ ለጋምቢያ፣ ለአይቮሪኮስት፣ ለሞዛምቢክ፣ ለሴኔጋል እና ሴራሊዮን ኃይል እያቀረ ይገኛል።ቱርክ በአፍሪካ ያላት ተጽእኖ ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል።
ኩባንያው በዓለም የኃይል አቅርቦት ተንሳፋፊ የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት (ፍሎቲንግ ፓወር ፕላንት) በማቅረብ ብቸኛው እንደሆነ ይናገራል።
ይህ አሠራር ብዙም የተለመደ ባይሆንም እንደ መርከብ ተንሳፋፊ የሆነ የኤሌክትሪክ ግሪድ ወደ ከተማዋ ከተጠጋ በኋላ ከዋናው የኃይል ግሪድ ጋር በማገናኘት የሚያመነጭበት ስልት ነው።
ይኸው የቱርክ ድርጅት ከአፍሪካ አገራት ሌላ ለኩባ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት በገጠማት ወቅት በተመሳሳይ ሆኔታ ደርሶላታል።
ጊኒ ቢሳው በዚህ የተንሳፋፊ የኃይል አቅርቦት ስትገለገል የቆየችው ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ ነበር።
ጊኒ ቢሳው ከዓለም እጅግ ድሃ አገሮች ተርታ ትመደባለች።












