ትራምፕ አምስት የአፍሪካ መሪዎችን ወደ ዋይት ሐውስ ለምን ጋበዙ?

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአምስት የአፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር በዋሺንግተን ዲሲ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ጉባዔ የጀመሩ ሲሆን፣ ይህ ክስተት ዋይት ሐውስ "ጥሩ" የንግድ እድል አድርጎ ተመልክቶታል።

የትራምፕ እንግዶች የጋቦን፣ የጊኒ ቢሳው፣ የላይቤሪያ፣ የሞሪታኒያ እና የሴኔጋል መሪዎችን ያካተተ ሲሆን አንዳቸውም በአህጉሪቱ ፈርጣማ ኢኮኖሚ አላቸው ከሚባሉት መካከል አይደሉም።

ስብሰባዎቹ በትራምፕ "እርዳታ ሳይሆን ንግድ" ፖሊሲ ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል።

አምስቱም አገራት ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው ዕቃዎች ላይ 10 በመቶ ታሪፍ የተጣለባቸው ሲሆን ይህንን ለማስቀነስ የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ተስፋ አድርገው ሊሆን ይችላል።

ረቡዕ ዕለት በዋይት ሐውስ የተዘጋጀው እና በቴሌቭዥን የተላለፈው የምሳ ግብዣ ላይ እነዚህ መሪዎች የአሜሪካን የኢኮኖሚ አጋርነት በማበረታታት ትራምፕን ሲያወድሱ ተሰምተዋል።

በረዥሙ የእንጨት ጠረጴዛ ላይ ትራምፕ በተቀመጡበት መስመር የተቀመጡት የሞሪታኒያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ኦልድ ጋዙዋኒ የመጀመሪያው ተናጋሪ ነበሩ።

ጋዙዋኒ "ወደ ቢሮ በተመለሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ሰላምን ለማስፈን ነው የጣሩት" ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም በዋይት ሐውስ አሸማጋይነት የተፈረመውን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የሩዋንዳ የሰላም ስምምነትን በመጥቀስም "ለረዥም ጊዜ የቆየውን ችግር ለመፍታት ወደ አፍሪካ ፈጥነው ተመልክተዋል።"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች በቀጥታ ትራምፕ ለኖቤል የሰላም ሽልማት መመረጣቸውን እንደሚደግፉ የተናገሩትን በሚያስተጋባ መልኩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ የጎልፍ ችሎታቸውን አሞካሽተው፣ በሴኔጋል የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ እንዲገነቡ ግብዣ አቅርበዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው "በጣም አመሰግናለሁ፤ በጣም ጥሩ፤አመሰግናለሁ። እንዲህ ባለ ጥሩ ሁኔታ እንደምትመለከቱኝ አላውቅም ነበር። ይህ በጣም ጥሩ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።"ይህንን ቀኑን ሙሉ ማድረግ እንችላለን።"

የአፍሪካ አገራት መሪዎችም ይህንን እድል ተጠቅመው ስለ አገራቸው የተፈጥሮ ሐብቶች እና ጥሬ እቃዎች፣ ብርቅዬ ማዕድናትን ጨምሮ ተናግረዋል። አንዳንዶቹ በቀጥታ ለአሜሪካ ባለሀብቶች እና ለፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ፌይ በዳካር "የቴክኖሎጂ ከተማ" ስለመገንባት እና ስለ ማራኪ "የባህር ዳርቻ ዕይታዎች" ተናግረዋል። አክለውም "በዚህ ላይ እንዲሳተፉ አሜሪካውያን ባለሀብቶችን መጋበዝ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

የጋቦኑ ፕሬዝዳንት ብሪስ ክሎቴየር ኦሊጊ ንጉዌማ በበኩላቸው አገራቸው ብርቅዬ ማዕድናትን ጨምሮ "ብዙ ሐብት አላት" ብለዋል።

"መጥተው ኢንቨስት ቢያደርጉ ደስተኞች ነን፤ ይህ ካልሆነ በእናንተ ፈንታ ሌሎች አገራት ሊመጡ ይችላሉ" ብለዋል ንጉሜ።

በዋሽንግተን የሴኔጋል አምባሳደር የነበሩት ባባካር ዲያኝ ይህ ለአፍሪካ መሪዎች የተደረገው ግብዣ አሜሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አህጉርን በተመለከተ የጀመረችውን የፖሊሲ "ለውጥ" የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በጥር ወር የሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት ትራምፕ አሜሪካ ለአህጉሪቱ ትሰጠው የነበረውን እርዳታ አቋርጠዋል።

ለዚህም የሰጡት ምክንያት አባካኝ እና ከ"አሜሪካ ትቅደም" ፖሊሲ ጋር የማይጣጣም ነው በማለት ነበር።

ትራምፕ እና የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ በሆኑባት አሜሪካ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ አፍሪካውያን ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ የሚፈቅደውን እድል፣አጎዋ፣ ያድሳሉ የሚለውን መገመት አጠራጣሪ ነው።

አምባሳደር ዲያኝ ለቢቢሲ "ቀድሞ ከዲሞክራቶች ጋር እንደነበረው አይደለም። ከእነርሱ ጋር ሁለት ጠንካራ ነጥቦች ነበሩ፤ በአጎዋ እና በሌሎች ድጋፎች ድህነት ቅነሳ እና የልማት ጉዳዮች።ያ ሁሉ አክትሟል" ብለዋል።

እንደቀድሞው ዲፕሎማት ከሆነ የትራምፕ አስተዳደር አቋም የዩክሬኑ መሪ ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን ያስተናገዱበት መንገድ ጋር የሚነጻጸር ነው።

ዲያጅ "ንጹህ ንግድ።ሁለቱም ወገን አሸናፊ የሚሆኑበት ሰጥቶ መቀበል። በዩክሬን ያንን አይተናል። የማዕድን ስምምነት ፈርማችሁ ከጎናችን ትሆናላችሁ፤ አለበለዚያ ሁሉንም ነገር እርሱት" ሲሉ አክለዋል።

ባለፈው ወር በሩዋንዳ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መካከል በዋሽንግተን የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፤ የንግድ ዲፕሎማሲ አሜሪካ ከፍተኛ የሆነ የማዕድን አቅርቦት እንድታገኝ የሚያስችል ነው።

በነዳጅ ዘይት የበለፀገችው ጋቦን ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሪ የሆኑት ኒኬይዝ ሙሉምቢ እንደተናገሩት በርግጥም የትራምፕ አስተዳደር የአፍሪካ የተፈጥሮ ሐብትን በተመለከተ የሚሰጡት ትኩረት ከቻይና እና ሩሲያን ጨምሮ ካሉ ሌሎች ተፎካካሪ ኃይሎች ጋር የሚያደርጉት ውድድር እየጨመረ ነው።

"እነዚህ ሁሉ [የተጋበዙት] አገሮች ሴኔጋል፣ ሞሪታኒያ እና ጋቦን በተለይ ጠቃሚ ማዕድናት አላቸው፤ ወርቅ፣ ነዳጅ፣ ማንጋኒዝ፣ ጋዝ፣ እንጨት እና ዚርኮን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጋቦን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቀው የማንጋኒዝ ክምችት ሩብ ያህሉን ትይዛለች። ለቻይና 22 በመቶ ማዕድን ታቀርባለች። ይህም ባትሪ እና ስቴይነለስ ስቲል ለማምረት ያገለግላል።

የነዳጅ ማውጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሞሉምቢ አክለውም ዩናይትድ ስቴትስ ከጋቦን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በጣም ትፈልጋለች፤ ምክንያቱም እንደ ማንጋኒዝ እና ዩራኒየም እንዲሁም ነዳጅ ያሉ "ስልታዊ" ማዕድናት ስላሏት ብቻ ሳይሆን በጊኒ ባሕረ ሰላጤ 800 ኪ.ሜ የሚሸፍን የባህር ጠረፍ ላይ ስልታዊ ስፍራ ላይ ስለምትገኝ ጭምር ነው።

አሜሪካ በአካባቢው ለመገንባት ያቀደችውን የጦር ሰፈር ማስተናገድ ትችላለች ሲሉ ሙሉምቢ ተናግረዋል።

"በጊኒ ባሕረ ሰላጤ ያለው የባህር ላይ ሽብርተኝነት ለአሜሪካ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል" ሲሉም አምባሳደር ዲያኝ ስለ የባህር ላይ ውንብድና ተመሳሳይ ነገር አንስተዋል።

ነዳጅ እና ጋዝ የጫኑ ብዙ መርከቦች በጊኒ ባሕረ ሰላጤ በኩል ያልፋሉ። ይህም ለበርካታ ዓመታት በባህር ላይ ውንብድና የሚታወቅ ስፍራ ነው።

የምዕራብ አፍሪካ የምርምር ማዕከል ኃላፊ ኦስማን ሴኔ ደግሞ ለሞሪታንያ እና ሴኔጋል ስደት የውይይታቸው ማዕከል ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

"ከ2023 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ20,000 ያላነሱ ወጣት ሞሪታኒያውያን በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሴኔጋላውያን ወጣቶች ጋር በኒካራጓ በኩል ወደ አሜሪካ መሄዳቸውን አንዘንጋ።"

"እነዚህ ሁሉ አገራት ለሕገወጥ ስደት መነሻዎች ናቸው" ሲሉም አክለዋል።

"ይህ በእርሱ [የትራምፕ] የስደት ፖሊሲ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነጥብ ነው፤ እና በየቀኑ ሰዎች ከድንበር ላይ ይመለሳሉ።"

ከአምስቱ አገራት መካከል ሞሪታኒያ ከአሜሪካ አጋር እስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሌላት ብቸኛዋ አገር ነች።

እስራኤል እአአ በ2009 በጋዛ ላይ በከፈተችው ጥቃት ምክንያት ያቋረጠችውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደነበረበት መመለስ በዋይት ሐውስ የሚደረገውን ድርድር አጣብቂኝ ውስጥ ሊከትተው ይችላል።

ለጋቦን እና ለላይቤርያ ደግሞ ከቪዛ ቀነ ገደብ በላይ መቆየት ሌላው መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው።

ሁለቱም አገራት ከቡሩንዲ የበለጠ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲሆን ይህም ባለፈው ወር አሜሪካ የጉዞ እገዳ ስትጥል እንደ ቁልፍ ምክንያት ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው።

በላይቤርያ የሕክምና አገልግሎት የሚጠባበቁ እናቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ላይቤሪያ ወንጀለኞችን ጨምሮ ከአሜሪካ የሚባረሩ ሰዎችን ለመቀበል ዩናይትድ ስቴትስ የምታቀርበውን ሀሳብ ልታጤነው ትችላለች።

ከአሜሪካ ጋር የጠበቀ ታሪካዊ ግንኙነት ያላት ላይቤርያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ጉዳይ ላይ ካቀረበቻቸው የአገራት ዝርዝር ውስጥ ተካታለች ተብሏል።

ለ14 ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ከዚያም ከአሥር ዓመታት በፊት በተከሰተው አስከፊ የኢቦላ ወረርሽኝ ምክንያት የተሽመደመደችው ላይቤርያ በአሜሪካ የእርዳታ መቋረጥ ክፉኛ ተጎድታለች።

በተለይም ተጽኖው የተሰማው ደካማ በሆነው የጤና ስርዓቷ ላይ ነው።

የአገሪቱ የጤና ስርዓት 48 በመቶ የሚሆነውን በጀት የሚያገኘው ከአሜሪካ ድጋፍ ላይ ነው።

ለዓመታት ተከታታይ መፈንቅለ መንግሥት እና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የደረሰባት ጊኒ ቢሳው የአሜሪካ ኤምባሲ በዋና ከተማይቱ ቢሳው እንዲከፈት ፍላጎት እንዳላት ተነግሯል።

የአሜሪካ ኤምባሲ በጊኒ ቢሳዋ የተዘጋው እአአ በ1998 ነው።

ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ከበርካታ ዓመታት በፊት አገራቸው ከላቲን አሜሪካ ወደ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ የኮኬይን መሸጋገሪያ ዋና ማዕከል በመሆኗ የተነሳ፣ በአሜሪካ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "የናርኮ ግዛት" የሚል ስያሜ ከተሰጣት በኋላ በዋይት ሐውስ መጋበዛቸው ኩራት እንዲሰማቸው ያደርጋል።

ወደ ዋሽንግተን ከመሄዳቸው በፊት በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ "ጊኒ ቢሳው አሁን ከስርዓት አልበኝነት ወጥታ እውነተኛ አገር ሆናለች። አሜሪካኖች የትኛውንም ግዛት ወደ አገራቸው አይጋብዙም። በደንብ የተዋቀረ መንግሥት ብቻ" ማለታቸው ተዘግቧል።

እርሳቸው እና አጋሮቻቸው የጋቦኑ ብሪስ ክሎቴየር ኦሊጊ ንጉሜ፣ የላይቤሪያው ጆሴፍ ቦአካይ፣ የሞሪታኒያው ሞሃመድ ኦልድ ጋዙዋኒ እና የሴኔጋሉ ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ ከትራምፕ ጋር ስምምነት ለማድረግ ተስፋ ያደርጋሉ።

በግንቦት ወር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እና ትራምፕ በኦቫል ኦፊስ ያደረጉትን ዓይነት ስብሰባ በድጋሚ እንዲታይ አይፈልጉም።

ያ የከፍተኛ ባለስልጣኖች ስብሰባ በአገራቱ መካከል ያለውን ውጥረትን ከማርገብ ይልቅ የአፍሪካ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ የሆነቸው ደቡብ አፍሪካ ላይ የ30 በመቶ ታሪፍ እንዲጣልባት አድርጓል።