ትራምፕ ከብሪክስ ጥምረት ጋር የሚወግኑ አገራት ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 አባላትን ካቀፈው የብሪክስ ጥምረት ፖሊሲዎችን ወግነው ከአሜሪካ ጥቅም የሚጻረሩ አገራት ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው አስጠነቀቁ።
"የብሪክሰ ጥምረት ፀረ-አሜሪካ ፖሊሲዎችን የሚደግፉ ማንኛውም አገራት ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ ይጠብቃቸዋል። በዚህ ፖሊሲ በልዩ ሁኔታ የሚቀር የለም" ሲሉ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስፍረዋል።
ትራምፕ ከብሪክስ ጥምረት ጋር በሚወግኑ አገራት ላይ ታሪፍ እጥላለሁ ያሉት፤ የጥምረቱ አባላት የአሜሪካን የታሪፍ ፖሊሲዎች ከመተቸት በተጨማሪ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ ) እንዲሁም ዋነኞቹ መገበያያ ገንዘቦች ላይ የወጡ ተመኖች ማሻሻያ እንዲደረጉ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።
ትራምፕ፤ ቻይና፣ ሩሲያ እና ሕንድን ጨምሮ የምዕራቡን ዓለም የበላይነት ለመገዳደር እና ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ እንዲሰፍን በሚል ተመሥርቷል የተባለውን ብሪክስን በተደጋጋሚ ሲነቅፉ ተደምጠዋል።
ብሪክስ ከመሥራቾቹ ከብራዚል፣ ከሩሲያ፣ ከሕንድ፣ ቻይና እና ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩትን አረብ ኤምሬቶች በአባልነት በመጨመር ጥምረቱን አስፍቷል።
የብሪክስ አባል አገራት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ይሸፍናሉ።
በብራዚሏ የሪዮ ዲጄኔሮ የሁለት ቀናት ጉባዔ እያደረጉ ያሉት የብሪክስ መሪዎች በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ጥምረቱ በዓለማችን እየተባባሱ ለመጡት የንግድ ግጭቶች እና የጂኦፖለቲካል ውጥረቶች የዲፕሎማሲ መድረከ እንዲሆን አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የብሪክስ አባል አገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች እሁድ ዕለት ባወጡት መግለጫ ታሪፍ ለዓለም አቀፍ ምጣኔ ሃብት ስጋት ሆኗል ሲሉ የተቹ ሲሆን፤ "በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ አና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እርግጠኛ አለመሆንን አስከትሏል" ብለዋል።
የዓለም አቀፉ የንግድ ምክር ቤቶች ምክትል ዋና ፀሐፊ አንድሪው ዊልሰን አገራት ከቻይና ጋር የንግድ ልውውጥ ማድረግ እናቆማለን ማለት የማይቻል እና ፈታኝ ነው ይላሉ።
"በዓለማችን ላይ በተለያዩ ዘርፎች ከቻይና ጋር አንሠራም የሚለውን ተግባራዊ ማድረግ በጣም ከባድ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"ቻይና በበርካታ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ ባትሪዎች፣ ብርቅዬ የምድር ማግኔቶች ከፍተኛ የበላይነት አላት። ከቻይና ምርቶች ውጪ ሌላ አማራጮች የሉም" ይላሉ።
በዚሁ የብራዚል የብሪክስ ጉባኤ ላይ መሪዎቹ በቅርቡ እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸሙትን ጥቃቶች አውግዘው፤ ጥቃቱ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።
ለአስራ ሁለት ቀናት በዘለቀው ግጭት እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ይታወሳል።
በዚህ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን እንዲሁም ሌሎች መሪዎቹ በአካል ተገኝተዋል።
የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ጉባኤ ላይ ያልተገኙ ቢሆንም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩያንግ ተሳትፈዋል።
በዩክሬን የጦር ወንጀሎች ተፈጽመዋል በሚል ከዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጉባኤውን የታደሙት በበይነ መረብ ነው።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከአሜሪካው ዶላር ጋር ተፎካካሪ መገበያያ ገንዘብ የብሪክስ አባል አገራት መጠቀም ቢጀምሩ 100 ፐርሰንት ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀው ነበር።
አሜሪካ በጣለችው ታሪፍ ላይ አገራት ስምምነት እንዲደርሱ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ሐምሌ 2/2017 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም ታሪፉ ሐምሌ 25 ተግባራዊ እንደሚሆን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ አሜሪካ የታሪፍ ስምምነቶችን የደረሰችው ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከቬትናም ጋር ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የተደረሰው ስምምነት አሜሪካ የምታስገባቸው ብረቶችን ያካተተ አይደለም።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ አገራት ሸቀጦች ላይ 10 በመቶ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል።
ትራምፕ ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ፖሊሲን ተከትለዋል ያሏቸውን "የለየላቸው አጥፊዎች" ብለው በጠሯቸው አገራት ላይ ደግሞ ከፍ ያለ ታሪፍን ጭነዋል።
ታሪፉ የተሰላው አሜሪካ ከአገራት ጋር ያላትን የንግድ ጉድለት (ትሬድ ዴፊሲትን) ለማጥበብ በሚል ሲሆን፣ ትራምፕ እነዚህ ታሪፎችን በመጠቀም የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ጉድለት በማስተካከል የአገሪቱን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲያብብ እና ሥራዎችን ለመፍጠር ተስፋ አድርገዋል።















