በአማራ ክልል የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን እና ንብረት መውደሙን መንግሥት ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Gove. communication/fb
በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለቀናት በዘለቀው ግጭት በአማራ ክልል ከተሞች እና የተለያዩ አካባቢዎች እስካሁን በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ የሆስፒታል ምንጮችን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል።
በአማራ ክልል ለወራት የቆየው ተቃውሞ እና ግጭት ባለፈው ሳምንት ተባብሶ ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት በመጠየቁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት በክልሉ ውስጥ እንዲሰማራ ተደርጓል።
ባለፉት ቀናት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች “የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ በርካታ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ በሰጠው መግለጫ አሳውቆ፣ የደረሰ ጉዳት በዝርዝር ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ገልጿል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል የተፈጠረውን “ግጭት ለማባባስ የከተማ ውስጥ ግዳጅ በመውሰድ የሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነበር” ያላቸውን 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አመልክቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያው በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉ 23 ሰዎችን ፎቶ እና ስም ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ከመካከላቸውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የምክር ቤት አባል ዶክትር ካሳ ተሻገር እና ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ይገኙበታል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በሚል ፎቶግራፋቸው እና ስማቸው ከተዘረዘሩት 23 ሰዎች መካከል ሁለቱ ሴቶች ናቸው።
እነዚህን በቁጥጥር ስር የሚገኙት ተጠርጣሪዎች ላይ አስፈላጊው ማስረጃ ተሰብስቦ ወደ ፍትሕ እንደሚቀርቡ ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል።
ምንም እንኳን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የጅምላ እስር እየተከናወነ ነው ሲባል የቆየ ቢሆንም፣ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በሰጠው መግለጫ፣ በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 23 ግለሰቦች ውጪ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች የሉም በማለት እየተሰራጨ ያለው መረጃ የተሳሳተ ነው ብሏል።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግ በኋላ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ታጣቂዎች ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች ተሰማርቶ የክልሉን ዋና ከተማን ጨምሮ ሌሎች ትልልቅ ከተሞችን ነጻ ማድረጉን እና የሰዓት እላፊ እና ሌሎችም ገደቦችን በስድስት ከተሞች ላይ ተጥሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠ ቅላይ መምሪያ እንዳለው የመጀመሪያ ዙር ዕቅዱ ትኩረት “በዘራፊው ቡድን ተይዘው የነበሩ የአማራ ክልል ከተሞችን ነጻ ማድረግ እና ክልሉን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ እንደነበር” ገልጾ ይህም በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ መግባቱንም አስታውቋል።
ታጣቂው ቡድን “ከተሞችን ለቆ ቅርሶች እና የሃይማኖት ተቋማት አካባቢ ለመመሸግ እና በተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረስ ወደእነዚህ ሥፍራዎች ሸሽቷል” ብሏል መምሪያው።
ባለፈው አንድ ሳምንት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲካሄድ በቆየው ግጭት የተፈጠረው ቀውስ ከሐሙስ ጀምሮ እየተረጋጋ መሆኑን እና ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እየተመለሱ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲገቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል የተከሰተው ተቃውሞ እየተጠናከረ ሄዶ፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የአማራ ክልል መንግሥት ጥያቄን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አርብ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት መታወጁ ይታወሳል።












