የአንዳንድ የአማራ ክልል ከተሞች የሐሙስ ውሎ ከቀናት ግጭት በኋላ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለሳምንት ያህል ሲካሄድ በቆየው ግጭት የተፈጠረው ቀውስ እየተረጋጋ መሆኑን እና ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እየተመለሱ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ስድስት ከተሞችን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን አሳውቆ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን ተከትሎ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 04/2015 ዓ.ም. የክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር እየተረጋጋች መሆኗን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በከተማዋ ሐሙስ ዕለት የተኩስ ድምጽ አለመሰማቱን ነዋሪዎቹ ገልጸው፣ ነገር ግን ከተማዋ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ አለመመለሷን በመጥቀስ፣ የንግድ እና የተለያዩ ቋማት በአብዛኛው ባለመከፈታቸው ከተማዋ ጭር ብላ ውላለች።
በተለይም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ መኪኖች እና ባጃጆች ወደ ሥራ ባለመመለሳቸው የነዋሪው እንቅስቃሴ ተገትቶ መዋሉን ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ዛሬ [ሐሙስ] የትራንስፖርት አገልግሎት አሊያም ተሽከርካሪዎች እንደወትሮው በከተማዋ ሲንቀሳቀሱ ባይታዩም ግጭት አሊያም ውጊያ ግን እንዳልተስተዋለ ነዋሪዎች ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ለቀናት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ወደ ባሕር ዳር መጀመሩን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ነገር ግን ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ ከተማ የሚወስድ ትራንስፖርት ስለሌለ ተሳፋሪዎች በእግራቸው ለመጓዝ ተገደዋል።
በዛሬው ዕለት በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የተወሰኑ መንገዶች እንደተዘጉ በመሆናቸው ለትራንስፖርት አስቸጋሪ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። በዚህም ሳቢያ ከተማዋ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ ባትመለስም አንዳንድ ነዋሪዎች በእግራቸው ሲንቀሳቀሱ መዋላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ተስፋሁን የተባለ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እንደተናገረው “ከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሰው የለም፣ ከተማዋ ጸጥ ብላለች።”
ጨምሮም በከተማዋ ውስጥ የተኩስ ድምጽ እንዳልተሰማ ጠቅሶ “የመከላከያ ሠራዊት አባላት በከተማዋ ውስጥ እየተዘዋወሩ ሲሆን፣ ወታደሮቹ ቤት ለቤት በመሄድ ተጠርጣሪዎችን እየፈለጉ ነው” ሲል ተናግሯል።
በጎንደር እና በላሊበላ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎችም የፋኖ ታጣቂዎች በማፈግፈጋቸው ሐሙስ ዕለት በከተሞቹ ያለው ሁኔታ ከባሕር ዳር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደው ግጭት በባሕር ዳር እና በጎንደር ከተሞች በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ የገለጹ ሲሆን፣ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆነው ተስፋሁን ለኤኤፍፒ እንደገለጸው በከተማዋ በተባራሪ ጥይት የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቀብር ረቡዕ ምሽት በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ተቀብረዋል።
ጎንደር - ላሊበላ - ኮምቦልቻ
ከባሕር ዳር በስተሰሜን በምትገኘው የክልሉ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ጎንደር ውስጥ የመንግሥት ኃይሎች በተለያዩ ነገሮች የተዘጉ አንዳንድ መንገዶችን ሲከፈቱ እንደነበር ነዋሪዎች ጠቁመዋል።
ጎንደር ስላለው ሁኔታ የጠይቅናቸው አንድ ነዋሪ “አሁን ሰላም ነው” ብለው፣ ሰዎች በእግር ይንቀሳቀሱ እንጂ፣ ተሽከርካሪ የለም ብለዋል። ነዋሪው ጨምረውም ሱቆች እና ወፍጮ ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ እንዳሉ ጠቅሰው ከረቡዕ ጀምሮ ተኩስ ድምፅ እንዳልተሰማ ይናገራሉ።
አሁን ሰላም ይስፈን እንጂ ባለፉት ጥቂት ቀናት ግን ከባድ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር አስታውሰዋል። አንድ ሌላ የጎንደር ነዋሪ ደግሞ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲከፈቱ ቢታዘዙም ሁሉም ሙሉ በሙሉ እንዳልተከፈቱ ገልጸዋል።
ሐሙስ ከሰዓት ግን ሁኔታዎች በተነፃፃሪ ወደ ቀድሞው ይዘታቸው እየተመለሱ እንደሆነ ነዋሪው ጠቅሰው፣ በጎንደር ከተማ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና ታንኮች በተለይ ደግሞ አድማ በታኞች በስፋት ይታያሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ መልሶ እንደሚጀምር ካስተወቀባቸው ከተሞች መካከል የሆኑት በጎንደር እና በላሊበላ ከተሞች ሐሙስ ዕለት በረራ መልሶ እንዳልተጀመረ ነዋሪዎች መስማታቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ የላሊበላ እና የኮምቦልቻ ከተሞች ነዋሪዎችን የሐሙስ ውሎን በተመለከተ የጠየቀ ሲሆን፣ በላሊበላ ከተማ ከወትሮው የተለየ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልታየ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ኮምቦልቻም ሰላም መሆኗን እና መደበኛ እንቅስቃሴ እንደነበር ገልጸዋል።
ነገር ግን በሁለቱም ከተሞች የአውሮፕላን በረራ መጀመር እየተጠበቀ መሆኑን እና ስለመጀመሩ የሰሙት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። በላሊበላ በረራ ለመጀመር ቀናት ሊፈለግ እንደሚችል እንዲሁም በኮምቦልቻ አገልግሎቱ ዛሬ አርብ መልሶ ሊጀምር እንደሚችል ተጠቁሟል።
ደብረ ታቦር - ደጀን
በደብረ ታቦር ደግሞ የከተማዋ እንቅስቃሴ በጣም ቀዝቃዛ እንደነበር እና ነዋሪው በጊዜ ወደ ቤቱ እንሚከት ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪ ጠቅሰው፣ አሁን በከተማዋ ምንም ዓይነት የተኩስ ድምፅ ባይሰማም ከሦስት ሰው በላይ ሆኖ በከተማዋ ውስጥ መንቀሳቀስ እንደማይችል ገልጸዋል።
ጨምረውም የጦር መሣሪያም ሆነ ስለት ያለው ቁስ ይዞ መንቀሳቀስም ሆነ መገኘት አደጋ እንደሆነ ተናግረው፤ ይህን ይዞ የተገኘ ሰው እርምጃ ይወሰድበታል ይላሉ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ባወጣው መመሪያ መሠረት በስድስት የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ የሰዓት እላፊ ገደብ የተጣለ ሲሆን፣ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስም መከልከሉ ይታወቃል።
በደብረ ታቦር ከተማ ሆቴሎች እና ባንኮች ሐሙስ ዕለትም ዝግ እንደሆኑ የሚናገሩት ነዋሪ፣ ካለፉት ቀናት በተሻለ ነዋሪዎች ሕጉን አክብረው መንቀሳቀስ እንደጀመሩ ለቢቢሲ ያስረዳሉ። ከዚህ ቀደም ግን ሰዎች በፃነት መንቀሳቀስ አይችሉም ነበር ይላሉ።
በብቸና መስመር ወደ ሞጣ የሚያልፍ በርካታ የመከላከያ ኃይል እንደተመለከቱ የሚገልጹት ነዋሪው ረቡዕ ተጨማሪ መከላከያ ኃይል ወደ ከተማዋ አንደገባ ተናግረዋል።
ብቸና ላይ ከባድ ውጊያ እንደነበር የሚጠርጥሩት ነዋሪው ሥፍራው ከደጀን ከ35 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ቢሆንም የተኩስ ድምፅ ግን ይሰማ እንደነበር ይናገራሉ።
በከተማዋ አለመረጋጋት መፈጠሩን ተከትሎ አገልግሎቶች መስተጓጎላቸውን የሚገልጹት ነዋሪው፣ በደጀን የውሃ እና የመብራት አገልግሎት ከተቋረጠ ቀናት እንደተቆሩ ገልጸዋል።
ዛሬ ሐሙስ በደብረ ታቦር እና በደጀን ያለው ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸው፣ ነገር ግን አሁንም ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ በመሆናቸው ሱቆች ተዘግተው እንዳሉ ይጠቅሳሉ።
በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት የንግድ ቤቶች ዝግ ሆነው በመቆየታቸው የተነሳ በደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ እንዳሉ ደጋግመው የሚገልጹት ነዋሪ፣ 800 መቶ ብር የነበረ የምግብ ዘይት 1500 ብር ድረስ እየተሸጠ እንዳለ ይናገራሉ። ይሄም ቢሆን ሱቆች አሁንም ዝግ ስለሆኑ በሰው በሰው እንጂ እንዲሁ እንደማይገኝ ይናገራሉ።
ለወራት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ሲካሄድ የነበረው ተቃውሞ እና የታጣቂዎች ግጭት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ተባብሶ በበርካታ ቦታዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች እና ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ገብተው ከሳምንት በላይ መቆየታቸው ይታወሳል።
በዚህም ሳቢያ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ጉዳት፣ የትራንስፖርት እና መደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል እንዲሁም የቀውሱ አካባቢም እየሰፋ በርካታ ቦታዎችን አዳርሷል።
በዚህም ሳቢያ ክልሉ የተፈጠረውን ችግር በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም በማይችልበት ሁኔታ ላይ መድረሱን በመግለጽ የአማራ ክልል መንግሥት የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በመጠየቁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።
ረቡዕ ዕለትም የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ሸዋ ሮቢት ስድስት የአማራ ክልል ከተሞችን ከታጣቂዎች ነጻ የማድረጉ አስታውቆ፣ በከተሞቹ ላይ ሠዓት እላፊ ገደብ መጣሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ገልጿል።












