በጎንደር በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው እና ሆስፒታሉ የመድኃኒት እና የኦክሲጂን እጥረት እንዳጋጠመው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአማራ ክልል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት በጎንደር ሆስፒታል ውስጥ የደም፣ ኦክስጂን እና የተወሰኑ መድኃኒቶች እጥረት ማጋጠሙን የሆስፒታሉ ምንጮች ለቢቢሲ ገለፁ።
በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ባለፉት ቀናት ከፍተኛ ግጭት እና የተኩስ ልውውጥ ከገጠማቸው የአማራ ክልል ከተሞች መካከል የጎንደር ከተማ አንዷ ስትሆን፣ በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በከተማዋ እና በዙሪያዋ ባለፉት ቀናት በነበረው ግጭት አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ ወደ 20 የሚደርሱ ሰዎች እንደሞቱ እና ከ200 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ጎንደር ሆስፒታል መምጣታቸውን የሆስፒታሉ የሕክምና ባለሙያዎቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ወደ ጎንደር ሆስፒታል በጥይት ተመትተው ከመጡ ሰዎች መካከል የ16 ዓመት ታዳጊ እንደሚገኝበት እና ተጎድተው ከመጡት መካከል በእድሜ ትልቅ የሆኑት ደግሞ የ50 ዓመት ሴት መሆናቸውን አንድ ዶክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ በኋላ የሞቱ ሰዎች አብዛኛዎቹ “ሰላማዊ ሰዎች እና ተዋጊዎች” መሆናቸውን የሕክምና ባለሙያዎቹ ጠቅሰው፣ እስካሁን ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ የመጡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት አለመኖራቸውን ተናግረዋል።
በግጭቱ የተነሳ በከተማዋ ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው በሆስፒታሉ ውስጥ ለሚገኙ ህሙማን እጅግ አስፈላጊ የሆኑት የደም፣ የኦክስጂንእና የመድኃኒት አቅርቦቶች እጥረት ማጋጠሙን የጎንደር ሆስፒታል ምንጮች ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሆስፒታሉ ባጋጠመው የኦክስጂን እጥረት ምክንያት ምንም ዓይነት ቀዶ ሕክምና ማከናወን አለመቻሉን የሆስፒታሉ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።
የቢቢሲ ምንጮች ጨምረውም ለቀናት በከተማዋ ባጋጠመው አለመረጋጋት የተነሳ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ በሆስፒታሉ ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን የሚቀርብ ምግብ እጥረት ማጋጠሙንም ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች እንዳሉት በከተማዋ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ግጭት የተጎዱ ሰዎችን ወደ ሆስፒታል ለማድረስ ምንም ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ የተጎዱ ሰዎች በቃሬዛ መምጣታቸውን አመልክተዋል።
ለወራት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተቃውሞ እና በግጭት የቆየው ውጥረት ባለፈው ሳምንት ወደለየለት ግጭት ከተሸጋገረ በኋላ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ አለመረጋጋት ተከስቷል።
በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለቀናት የዘለቀው ግጭት ከአቅሙ በላይ የሆነበት የክልሉ መንግሥት የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቆ፣ ባለፈው አርብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።
ይህንንም ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የፋኖ አባላት ወደ ተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ተሰማርተው ባለፉት ቀናት ከባድ ግጭቶች መከሰታቸውን የባሕር ዳር እና የጎንደር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከአንድ ሳምንት በላይ በክልሉ የተለያዪ አካባቢዎች ሲካሄድ በቆየው ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳትን በሚመለከት ከፌደራል መንግሥቱ እና ከክልሉ መንግሥት እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ቢቢሲ በባሕር ዳር እና በጎንደር ከተሞች የሚገኙ የሆስፒታል ምንጮችን እና ነዋሪዎችን በማናገር ለመረዳት እንደቻለው ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, FB
ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ከ650 በላይ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው እና ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 03/2015 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት በቀበሌ 4፣ 11፣ 12 እና 18 በነበረው ግጭት በጥይት ተመትተው የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን እና ወደ ሆስፒታል ሳይሄዱ በአካባቢያቸው ቀብራቸው መፈጸሙን ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ጨምረውም ከማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት በከተማዋ መታየት እንደጀመረ እና ዛሬ ረቡዕ ረፋድ 4 ሰዓት አካባቢ ፒያሳ ቀበሌ 18 አካባቢ ከተሰማው የተኩስ ልውውጥ ውጪ የጥይት ድምጽ መሰማት ቀንሷል ብለዋል።
በጎንደር ከተማ በተለይ ሰኞ ዕለት በከባድ መሳርያ የታገዘ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በተለይ በተለምዶ ፒያሳ ተብሎ በሚታወቀው የከተማዋ ክፍል ቀበሌ 3፣ 4፣ 11፣ 12፣ 13፣ 14 ይህ መስተዋሉን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የሆስፒታል ምንጮች ጨምረውም በከተማዋ ውስጥ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ምንም እንኳ ምንም ጉዳት ባይደርስም ሰኞ ዕለት ሆስፒታሉ በመሳርያ ተመትቶ ነበር ብለዋል።
ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ በከተማዋ አንጻራዊ መረጋጋት መፈጠሩን የሚናገሩት የህክምና ባለሙያዎች በሆስፒታሉ ዙርያ የመከላከያ ሠራዊት እንደሚገኝ ጨምረው ተናግረዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ማክሰኞ ምሽት ባወጣው እና በኋላ ላይ ባነሳው መግለጫ ላይም መንግሥት ሕግ የማስከበር ግዴታውን ተጠቅሞ እየወሰደ ባለው እርምጃ ችግሩ የተከሰተባቸው “አብዛኞቹ ከተሞች ወደ አንፃራዊ ሰላም እየተመለሱ ነው” ብሎ ነበር።
ጨምሮም ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር አካባቢዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መፈጠሩን እና ነዋሪው ወደ መደበኛ ሕይወቱ መመለሱን እና የክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳርን እና ጎንደር ከተማን ከታጣቂዎች ነጻ ለማድረግ ከሰኞ ምሽት ጀምሮ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ አንዳለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች አቋርጦት የነበረውን በረራ ከነገ ሐሙስ ነሐሴ 04/2015 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ተከተታይ ቀናት፤ ወደ ኮምቦልቻ፣ ጎንደር፣ ላሊበላ እና ባሕር ዳር የሚደረጉ በረራዎችን መሰረዙን በትናንትናው ዕለት ማስታወቁ ይታወሳል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲገቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል የተከሰተው ተቃውሞ እየተጠናከረ ሄዶ፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ለወራት የቆየው እና ባለፈው ሳምንት ተባብሶ ከክልሉ አቅም ውጪ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት የተጠየቀበት የፀጥታ መደፍረስ፤ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለ ግጭት መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም ሳቢያ በክልሉ አብዛኛው ክፍሎች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት እና ፍጥጫ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል፣ የኢንትርኔት አገለግሎት ተቋርጧል፣ አንዳንድ አካባቢዎችም በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተገልጿል።
በዚህም ሳቢያ የአማራ ክልል መንግሥት ጥያቄን ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው አርብ በአማራ ክልል ላይ ለስድስር ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ፣ አዋጁን የሚያስፈጽመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አቋቁሟል።












