በአማራ ክልል በታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በቀጠለው ግጭት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

ባሕር ዳር

የፎቶው ባለመብት, Bahir Dar communication

የምስሉ መግለጫ, ባሕር ዳር

በአማራ ክልል በታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በቀጠለው ግጭት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጮች እና ነዋሪዎች ገለጹ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል ሐኪም የሆኑ ግለሰብ ግጭቱ ከጀመረ አንስቶ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታሉ እንደገቡ ተናግረዋል።

“አሁን በቁጥር ደረጃ የደረሰውን ጉዳት ለመግለጽ ይቸግራል። በርከት ያለ አስክሬን ነው ወደ ሆስፒታሉ እየገባ ያለው” ብለዋል ሐኪሙ።

በርካታ ሰላማዊ ሰዎች የግጭቱ ሰለባ እየሆኑ ነው ያሉት እኝህ ሐኪም፣ ከሆስፒታሉ ውጭ፣ ትናንት አባይ ማዶ አካባቢ በሚገኝ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ሲያስቀድሱ የነበሩ ግለሰብ በተባራሪ ጥይት ተመትተው መመልከታቸውንም ገልጸዋል።

ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሌላ የሆስፒታሉ ሐኪም፣ በከተማዋ ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታሉ የገቡት ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህ መካከል በሕክምና ላይ እያሉ ሕይወታቸው ያለፈ እና ሕይወታቸው አልፎ የመጡ እንዳሉ ተናግረዋል።

እኝህ ሐኪም እንደሚሉት በግጭቱ የ5 ወር ሕጻንን ጨምሮ አረጋውያን እንዲሁም ወጣቶች የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ ገብተዋል።

“ሕጻኑ በእናቱ እቅፍ እንዳለ በተባራሪ ጥይት መመታቱን ሰምቻለሁ” ብለዋል ሐኪሙ።

በከተማዋ የትራንስፖርትም ሆነ የአምቡላንስ አገልግሎት ባለመኖሩ የተጎዱ ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ የሚገቡት በቃሬዛ እንደሆነም የሕክምና ባለሙያቹ ጨምረው ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በፀጥታው ችግር ምክንያት ደም ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችም ደም ማጓጓዝ አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል።

ደብረ ብርሃን እና ጎንደርን ጨምሮ ግጭት እየተካሄደባቸው ባሉ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው እና ለጉዳት መዳረጋቸውም እየተዘገበ ነው።

የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ህልውና አብቅቶ ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲካተቱ መወሰኑን ተከትሎ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን መፍረስን በመቃውም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ግጭት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ክልሉን ቀውስ ውስጥ ከትቶታል።

በፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሲካሄድ የቆየው ግጭት እና የተኩስ ልውውጥ ከክልሉ አቅም በላይ ሆኖ የፌደራል መንግሥቱን ድጋፍ በመጠየቁ፣ ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።

የአማራ ክልል ትላልቅ ከተሞች የትናንት እና የዛሬ ውሎ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በክልሉ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ደብረ ብርሃን ፋኖ በሚባሉ ታጣቂዎች እና በመከላከያ መካከል ያለው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉን ዛሬ ረፋዱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት የራዲዮ ሥርጭት መቋረጡንም ነዋሪዎቹ አክለዋል።

በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 14፣ 16 እና 13 አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በተለይ በባህርዳር ቀበሌ 14 አካባቢ ሰኞ ሌሊት ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም. ሌሊት ጀምሮ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ሲሰሙ እንዳደሩ እና ረፋዱንም መቀጠሉን ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት በጎንደር፣ ላሊበላ፣ ደብረ ብርሃን እና በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር እና በክልሉ ውስጥ ያሉ ዋና መንገዶች መዘጋታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ያናጋራቸው ነዋሪዎች መግለጻቸውን ትናንት ዘግቧል።

ወታደራዊ አውሮፕላኖች በባሕር ዳር ሰማይ ላይ መታየታቸውን እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በከተማዋ ውስጥ መቋረጡን አንድ ነዋሪን ጠቅሶ አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል። ሌላ ነዋሪም ታንኮች ወደ ከተማዋ እየገቡ መሆናቸውን ለዜና ወኪሉ ገልጿል።

ነዋሪው ጨምሮም በባሕር ዳር ነገሮች እየተባባሱ በመሄድ ላይ መሆናቸውን አመልክቶ “ከባድ የተኩስ ልውውጥ ይሰማል” ብሏል።

ግጭቱ ከአዲስ አበባ 130 ኪሎሜትር በምትርቀው የኢንደስትሪ ከተማዋዋ ደብረ ብርሃን ሰማይ ላይም ድሮን ሲበር መመልከታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ አንድ የደብረ ብርሃን ከተማ ባለሥልጣን ለኤፒ ትናንት እንደተናገሩት “ከተማዋ የጦር አውድማ ሆናለች። በየደቂቃው የተኩስ ልውውጥ ይካሄዳል” ብለው ነበር።

በጎንደር ከተማም ፒያሳ በሚባለው አካባቢ እና በከተማዋ ሰሜናዊ አቅጣጫ ከፍተኛ ተኩስ ዛሬም ሲሰማ ማርፈዱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ በግጭቱ ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን ገልጸው፣ ግጭቱ በመባባሱ የከፋ እልቂት ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

ባለፉት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ግጭት እና የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉን ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ አረጋግጠው፣ የከተማዋ የተለያዩ ከፍሎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ ብለዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር ለማስገባት በከፈቱት ዘመቻ ሰኞ ዕለት ከባድ ውጊያ እንደነበር ኤፔ ነዋሪዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።

“የተኩስ ድምጽ ሰምተናል እንዲሁም ጭስ ይታየናል” ያሉ አንድ የጎንደር ነዋሪ፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት በከተማዋ ዋነኛ የፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙም ጨምረው ገልጸዋል።

የታጣቂ ቡድኑ ደጋፊዎች ታጣቂ ቡድኑ ተጨማሪ ከተሞችንና መንደሮችን መቆጣጠራቸውን የገለጹ ሲሆን ቢቢሲ ግን ይህንን በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ወደተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የሚያደርጋቸው በረራዎች የተስተጓጎሉበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገ ረቡዕ፣ ሐሙስ እና ዓርብ ወደ ደሴ (ኮምቦልቻ)፣ ጎንደር፣ ላሊበላ እና ባሕር ዳር የሚደረጉ በረራዎች የተሰረዙ መሆናቸውን ማክሰኞ ረፋድ ላይ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአዲስ አበባ በርካታ ሰዎች መታሰራቸው የተዘገበ ሲሆን የአልፋ ሚዲያ መሥራች ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ከታሰሩ መካከል ይገኙበታል። ጋዜጠኛ በቃሉ ባለፈው ዓመትም በትግራዩ ጦርነት ወቅት ታስሮ ነበር።

ባለፈው አርብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በፀጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተይዘው መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወቃል።

ባሕር ዳር ባለፈው ቅዳሜ
የምስሉ መግለጫ, ባሕር ዳር ባለፈው ቅዳሜ

የሰላም ጥሪዎች ፣ “ለሰላም እጦቱ ምንጩ . . . አቋምም ሆነ አቅም የሌለው የብልፅግና አመራር ነው”

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአማራ ክልል ያለው ግጭት በሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ እና የሲቪል ተቋማት በተለያየ ጊዜ ባወጡት መግለጫ በባለፈው የትግራዩ ጦርነት የደረሰውን ኪሳራ በማውሳት ግጭቱ በንግግር እንዲፈታ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በአማራ ክልል የተባባሰውን ሁኔታ በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 02/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ “ለሰላም እጦቱ እና አለመረጋጋት ምንጩ በጠራ የፖለቲካ መስመር ላይ መቆም ያልቻለው፤ አቋምም ሆነ አቅም የሌለው የብልፅግና አመራር ነው” ሲል ወቅሷል።

ፓርቲው በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ያጋጠመው ሁኔታ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ የተከማቹ አገራዊ የፖለቲካ ትኩሳቶች ከጫፍ ላይ ሲደርሱ የተፈጠረ ነው በማለት ድንገተኛ ክስተት አለመሆኑን አመልክቷል።

ለዚህም በአማራ ክልል ለዓመታት የታመቀ ብሶት፣ የመጠቃት ስሜት እና ተስፋ መቁረጥ ገደቡን አልፎ ክልሉን አሁን ላለበት ሁኔታ እንዳበቃ እና በደሎች ቅሬታዎች እንዲሁም ስጋቶች ተገቢውን መልስ በወቅቱ ባለማግኘታቸው አሁን ለተፈጠረው ሁኔታ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

ኢዜማ ችግሩን በተመለከተ ምክንያት እና ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን ወገኖች በዝርዝር የጠቀሰ ሲሆን፣ በዋናነት በመንግሥት ውስጥ እና ከመንግሥት ውጪ ያሉ “ፅንፈኛ ዘውጌ ፖለቲከኞች ተናበው ግጭት እየጠመቁ ናቸው” በማለት በተለይ የመንግሥት የአስተዳደር ድክመት አሁን በአማራ ክልል ለተከሰተው አለመረጋጋት መነሻ ነው ሲል ማሳያዎችን ዘርዝሯል።

ፓርቲው አሁንም የመንግሥት ኃላፊዎች ከጊዜያዊ የሥልጣን ፍላጎት እና እሳት የማጥፋት ተግባራት በመታቀብ ዘላቂ አገራዊ የሰላም መንገዶችን እንዲፈልጉ፣ ታጣቂ ኃይሎችም ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ጥሪ አቅርቧል።

ለዚህም የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ግጭቱን ለማስቆምና ውይይት መደረግ እንዲጀመር የሚጠበቅባቸውን እንዲያከናውኑ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በአገሪቱ የሚካሄዱ ግጭቶች እንዳሳሰቡት በመግለጽ ግጭቶች ቆመው ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቅርቧል።

በአገሪቱ በሚገኙ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ያሉ የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ወደ ግጭት በማምራታቸው የአገሪቱን ደኅንነት እና ህልውና በመፈታተን ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

ኮሚሽኑ በአገሪቱ ምክክር እና ንግግሮች እንዲጀመሩ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመጥቀስ፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየታዩ ያሉ “ደም አፋሳሽ ግጭቶች የኮሚሽኑን ሥራ አዳጋች እያደረጉት ይገኛሉ” ብሏል።

በመሆኑም በመላው አገሪቱ የሚታዩ ግጭቶች “በአስቸኳይ ያለቅድመ ሁኔታ ቆመው የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አሉን የሚሏቸውን ልዩነቶች ወይም ጥያቄዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ” አስቸኳይ ጥሪ አቅርቧል።

ለዚህም የምክክር ኮሚሽኑ የሚመለከታቸውን ወገኖች በማቀራረብ፣ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየት እና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት በዚህ ዓመት ያከናወናቸውን ሥራዎች በተመለከተ ትናንት ሰኞ ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ ምክንያት የሆነውን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት መፍትሔ እንዲያገኝ ውይይት እና ድርድር ሊደረግ እንደሚችል አስታውቋል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅመው ዕዝን የሚያስተባብረው የደኅንነት ተቋሙ ሰኞ ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም. ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ፣ አስፈላጊውን ሁሉ ተግባር እያከናወነ መሆኑን አመልክቶ “ችግሩ በውይይት እና በድርድር የሚፈታበት መንገድ ዝግ ባለመሆኑ ተከታታይ ጥረቶች ይደረጋሉ” ብሏል።