የዓለም ጤና ድርጅት በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት አሳስቦኛል አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት ድርጅታቸውን እንዳሳሰበው ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ በተከሰተው ግጭት መንገዶች መዘጋታቸው እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ የሰብዓዊ እርዳታን ማድረስ እና ግንኙነትን ለማስቀጠል ከባድ ያደርጉታል ብለዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በትዊተር ገጻቸው ይህን ያሉት በአማራ ክልል በታጣቂዎች እና በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች መካከል የተከሰተው ግጭት በተስፋፋበት ወቅት ነው።
በክልሉ አብዛኛው ክፍሎች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል፣ የኢንትርኔት አገለግሎት ተቋርጧል፣ አንዳንድ አካባቢዎችም በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተገልጿል።
በክልሉ ያለው ግጭት ተባብሶ ክልሉ ከአቅሜ በላይ ነው በማለቱ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው አርብ በአማራ ክልል ላይ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ፣ አዋጁን የሚያስፈጽመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አቋቁሟል።
ይህ ዕዝ ሕግ የማስከበር ሥራውን በማከናወን ክልሉን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው በአጭር ጊዜ እንዲመለስ እንደሚያደርግ ይገልጻል።
ይሁን እንጂ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ግጭቶች በሰዎች ጤና ላይ በፍጥነት አሉታዊ ተጽእኖ ከማሳደራቸው በተጨማሪ በጤና ስርዓቱ ላይ ረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ጉዳት ያስከትላሉ ይላሉ።
ዶ/ር ቴድሮስ ሰዎች የጤና ድጋፍ እንዳይቋረጥባቸው እና የዓለም ጤና ድርጅት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ በክልሉ የጤና ስርዓቱ ጥበቃ እንዲደረግለት ጠይቀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም “ከምንም በላይ ለሰላም ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት በአማራ ክልል ጨምሮ በጤና ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎ ነበር።
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን በሚያስተናግደው ክልል የመድሃኒት እና የህክምና ቁሳ ቁስ ግብዓት እጥረት ከሰላም እጦት ጋር ተደማምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንቅስቃሴን ገድበው ቆይተዋል።












