“አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት እየተፈጠረ ነው” የአማራ ክልል መንግሥት

የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ የተከሰተውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር እየተወሰደ ባለ እርምጃ ችግር አጋጥሟቸው የነበሩ አካባቢዎች ውስጥ አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት እየተመለሱ ነው ሲል ገለጸ።
ለወራት ሲካሄድ የነበረው ግጭት ባለፈው ሳምንት ተባብሶ በበርካታ አካባቢዎች ውስጥ አለመረጋጋት መፈጠሩን ተከትሎ የክልሉ መስተዳደር ቀውሱን በመደበኛ የሕግ ማስከበር እርምጃ ሊቆጣጠረው ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ማሳወቁ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ውስጥ ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር ጣልቃ እንዲገባ በቀረበለት ጥያቄ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አሳውቋል።
ባለፉት ቀናት የክልሉን ዋና ከተማ ባሕር ዳርን ጨምሮ በበርካታ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይሎች ተከታታይ ግጭቶችን ሲያካሂዱ የቆዩ ሲሆን፣ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ድረስም ነዋሪዎች የተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ የፋኖ ቡድን አባላት እንቅስቃሴ በተለይ በክልሉ ያሉ ከተሞችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል የገለጸ ሲሆን፣ የክልሉን መንግሥት በመጣል የፌደራል መንግሥቱንም የማናጋት ዓላማ እንደነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ መግለጹ ይታወሳል።
ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የተካሄዱ ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦችን ተከትሎ ታጣቂዎቹ ከወረዳ እና ከዞን ከተሞችን በተጨማሪ በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር እንዲሁም በሌሎች ትላልቅ የክልሉ ከተሞች ውስጥ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተለይ በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላ እና ደብረ ብርሃን ከተሞች ማክሰኞን ጨምሮ ባለፉት ቀናት ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ከባድ የሚባሉ ግጭቶች መካሄዳቸውን ቢቢሲ ከተመያዩ ምንጮች ለመረዳት ችሏል።
የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይም “መንግሥትን በመገዳደር ነፍጥ በመዘዘው ኃይል ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ግዴታውን ተጠቅሞ” እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ገልጿል።
የክልሉ መንግሥት “ጽንፈኛ እና በዘራፊ የሥልጣን ጥመኛ ቡድኖች” ያላቸው ታጣቂዎች ቀሰቀሱት ያለው ሁከት እና ብጥብጥን ለመቆጣጠር የአገር መከላከያ ሠራዊት በወሰደው ተመጣጣኝ እርምጃ ችግሩ የተከሰተባቸው “አብዛኞቹ ከተሞች ወደ አንፃራዊ ሰላም እየተመለሱ ነው” ብሏል።
በዚህም መሠረት ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር አካባቢዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መፈጠሩን እና ነዋሪው ወደ መደበኛ ሕይወቱ መመለሱን ገልጿል።
ጨምሮም የክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳርን እና ጎንደር ከተማን ከታጣቂዎች ነጻ ለማድረግ ከሰኞ ምሽት ጀምሮ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመልክቷል።
ቢቢሲ ማክሰኞ እኩለ ቀን ላይ ያናጋራቸው የባሕር ዳር እና የጎንደር ከተሞች ነዋሪዎች እንዳሉት ከሰኞ ከሰዓት ጀምሮ የከባድ መሳሪያ ድምጽ እንደሚሰማ ገልጸው፣ ተኩሱም ከከተሞቹ ማዕከላዊ ክፍል ወጣ ብለው በሚገኙ የአካባቢዎች ውስጥ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ የኢንተርኔት አግልግሎት ከመቋረጡ በተጨማሪ የመንገድ እና የአየር ትራንስፖርቶች ተስተጓጉለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንግድ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ወደ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ያደርጋቸው የነበሩ በረራዎች የተቋረጡ ሲሆን፣ ዛሬ ማክሰኞ ደግሞ በረራ ከተሰረሰባቸው ከተሞች መካከል ባሕር ዳርም ተካታለች።
ይህ የአማራ ክልልን ያወከው ቀውስ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ የተለያዩ ወገኖች የጠየቁ ሲሆን፣ መንግሥትም ለውይይት እና ለድርድር በሩ ክፍት መሆኑን ገልጾ፣ ሕግ የማስከበር እርምጃውን እንደሚቀጥል አሳውቋል።
በአማራ ክልል ያጋጠመው አለመረጋጋት በክልሉ የለውን እንቅስቃሴ ያስተጓጎለው ሲሆን በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱም መረጃዎች ያመለክታሉ።
አስካሁን በሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተገለጸ አሃዝ ባይኖርም፣ ቢቢሲ ባሕር ዳር ከሚገኙ የሆስፒታል ምንጮች እንደተራደው ጥቂት የማይባሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።












