ለ12ኛ ክፍል ፈተና ወደ አማራ ክልል የሄዱ መምህራን መንገድ በመዘጋቱ ችግር ገጠማቸው

ጎንደር ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Visit Amhara

አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ያቀኑ መምህራን በፀጥታ መደፈረስ ምክንያት መንገድ ዝግ በመሆኑ ወደ መኖሪያቸው መመለስ ባለመቻላቸው ችግር እንደገጠማቸው ተናገሩ።

በፈታኝነት ወደ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ እና እንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች ያቀኑ መምህራን፣ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፈተናው ከተጠናቀቀ አራት ቀናት ቢቆጠሩም ወደ መጡበት አካባቢ መመለስ ባለመቻላቸው ለችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ወደ ታሪካዊቷ ከተማ የተጓዝ አንድ መምህር በከተማው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መሃል ከተማ ከሚገኘው የሆቴል ክፍሉ ከወጣ ሦስት ቀናት መቆጠራቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ከሆቴል ከወጣሁ ሦስት ቀን አለፈኝ። የከባድ መሳሪያ ተኮሱ ይሰማል ። በከተማዋ ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም” የሚለው ይህ መምህር፣ የሆቴሉ ሠራተኞችም ወደ ሥራ እየገቡ ስላልሆነ ምግብ ማግኘት እጅግ ከባድ እንደሆነ ይናገራል።

“ምግብ ካገኘን ሦስት ቀን አልፎናል። ባለፈው ሳምንት የገዛነውን ቆሎ ነው እየቆጠብን እየበላን ያለነው። ከሆቴሉ እያገኘን ያለነው ውሃ ብቻ ነው” በማለት ይህ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ መምህር ያለበትን ሁኔታ ለቢቢሲ ገልጿል።

በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለ ግጭት ባለፈው ሳምንት ተባብሶ ከክልሉ አቅም ውጪ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት መጠየቁ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።

በክልሉ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል፣ የኢንትርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፣ አንዳንድ አካባቢዎችም በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጎንደር ያለ ሌላ መምህር የፋኖ ታጣቂዎች እና የአገር መከላከያ የከተማዋን የተለያዩ አካባቢ በመያዝ እየተዋጉ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ቢቢሲ ይህን መምህር ማክሰኞ ረፋድ ላይ በስልክ በሚያነጋግርበት ወቅት የከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በስኬት መጠናቀቁን ባለፈው አርብ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ይፋ ሲያደርጉ ጎንደር ላይ ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት እና አንድ ፈታኝ መምህር በታጣቂዎች መገደላቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ሌላኛው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን ወደ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ያቀኑት መምህር በተመሳሳይ በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለስ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

እንደ ጎንደር ከተማ ሁሉ በሌላኛው የአማራ ክልል ከተማ በደብረ ማርቆስ ግጭት ባይኖርም የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ዝግ መሆናቸውን በደብረ ማርቆስ ከተማ ያሉት መምህር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“መንግድ ዝግ ነው፤ ከተማው ከሞላ ጎደል ሰላም ነው። የደረሰብን ጉዳት የለም። ዋናው ችግራችን ወደ መጣንበት ለመመለስ አለመቻላችን ነው” ብለዋል።

አሁን ላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት በከተማዋ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የሚገልጹት እኚህ መምህር፤ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከዚህ በላይ ተባብሶ የበለጠ ችግር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን እንዲፈትኑ አማራ ክልል ተመድበው በተፈጠረው ችግር ምክንያት ወደ ቀያቸው መመለስ ያልቻሉ መምህራንን ጉዳይ በተመለከተ የትምህር ሚኒስቴርን ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት እስካሁን አልተሳካም።

ፈተና ለመፈተን ወደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተልከው ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ፈተናው አርብ ከተጠናቀቀ በኋላ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ መምህራን ቅዳሜ ዕለት ከባሕር ዳር መውጣታቸውን አስረድተዋል።

የ12ኛ ክፍል ፈተና ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ተጠናቋል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Education

የምስሉ መግለጫ, የ12ኛ ክፍል ፈተና ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ተጠናቋል።

“ፈታኞች እስከ ቅዳሜ ምሽት ድረስ ከባሕር ዳር ሲወጡ እንደነበረ ሰምቻለሁ። እዚያ የቀሩ መምህራንም አሉ። እኛ እንደወጣን ነው መንገዱ የተዘጋጋው” ብለዋል።

እኚህ መምህር ወሎ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ወደ አካባቢው አቅንተው የነበሩ መምህራን እሁድ ዕለት በአፋር በኩል አድርገው አዳማ ስለመግባታቸው እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ጨምረውም ለፈተና ወደ እንጅባራ የተጓዙ ባልደረባቸው ግን መውጫ አጥተው እዚያው እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፈተና እንዲፈትኑ ወደ ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ ተልከው በፀጥታ ችግር ምክንያት መውጫ አጥተው የቀሩ መምህራን ለገባንበት ችግር መፍትሄ ለመስጠት የሞከረ አካል የለም ሲሉ ቅሬታ እያሰሙ ነው።

“ከጎንደር ዩኒቨርሲቲም ሆነ ከትምህርት ሚኒስቴር ደውሎ ‘ምን ውስጥ ነው ያላችሁት’ ያለን የለም” ይላል ጎንደር የሚገኘው መምህር።

ይህ መምህር ጨምሮም ለሥራቸው ሙሉ የውሎ አበል እንዳልተከፈላቸው ይናገራል። “እስካሁን የተከፈለን የውሎ አበል የማኅበራዊ ሳይንስ ፈተና የፈተንበት ብቻ ነው። ችግር ውስጥ ነው ያለነው። ቀሪውን ገንዘብ ብናገኝ ኖሮ ወጪያችንን እንሸፍን ነበር። ይህን እንኳን ማድረግ አልቻሉም። አንድ ነገር ብንሆን ኃላፊነት የሚወስድ አካል ያለ እንኳን አይመስለኝም” በማለት መምህሩ ስላሉበት ሁኔታ በምሬት ለቢቢሲ ተናግረዋል።