በጠ/ሚ ኔታኒያሁ ትዕዛዝ ከ200 በላይ እስራኤላውያን ከባሕር ዳር እና ጎንደር ወጡ

ከባሕር ዳር እና ከጎንደር ወጥተው ወደ አዲስ አበባ ከተወሰዱት መካከል

የፎቶው ባለመብት, The Prime Minister of Israel/fb

የምስሉ መግለጫ, ከባሕር ዳር እና ከጎንደር ወጥተው ወደ አዲስ አበባ ከተወሰዱት መካከል

አስራኤል ከሁለት መቶ የሚበልጡ ዜጎቿን ባለፉት ቀናት ግጭት ከተካሄደባቸው የአማራ ክልል ከተሞች ከባሕር ዳር እና ከጎንደር ማስወጣቷን አስታወቀች።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄዱ ግጭቶች ምክንያት የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች ለቀናት ተቋርጠው ቆይተዋል።

በርካታ ቤተ እስራኤላውያን በሚገኙበት የአማራ ክልል ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ የእስራኤል የደኅንነት ምክር ቤት እና የአይሁዳውያን ተቋም ዜጎቻቸውን በማስወጣቱ ሂደት መሳታፋቸው ተገልጿል።

በዚህም አማካይነት ከጎንደር ከተማ 174 ከባሕር ዳር ደግሞ 30 ቤተ እስራኤላውያን የአገሪቱ ዜጎች ሐሙስ ነሐሴ 04/2015 ዓ.ም. እንዲወጡ መደረጋቸውን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ለሳምንት ያህል በአማራ ክልል የሚገኙ ትላልቅ ከተሞችን ጨምሮ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች ሲካሄዱ የነበረ ሲሆን፣ የፌደራል መንግሥቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሉ ላይ መደንገጉ ይታወቃል።

ይህንንም ተከትሎ አገራት ዜጎቻቸው ወደ አማራ ክልል እንዳይጓዙ እንዲሁም በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ዜጎቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና መውጣት የሚቻልበት ሁኔታ እስኪፈጠር ባሉበት እንዲቆዩ አሳስበው ነበር።

የግጭቱን መባባስ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አማራ ክልል ከተሞች ያደርጋቸው የነበሩ በረራዎችን ማቋረጡን ማሳወቁ ይታወቃል።

ረቡዕ ዕለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚው አካል የፌደራሉ መንግሥት ኃይሎች ስድስት ከተሞችን ከታጣቂዎች በማስለቀቅ መቆጣጠራቸውን ከገለጸ በኋላ ከተሞቹ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ እና ሁሉም አገለግግሎቶች እንደሚጀምሩ አሳውቆ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያቋረጣቸውን በረራዎች ለሐሙስ ቀስበቀስ መጀመሩ የታወቀ ሲሆን፣ የእስራኤል መንግሥትም ዜጎቹን ማስወጣቱን የገለጸው በረራ መጀመሩን ተከትሎ ነው።

ዜጎቻቸውን ለማስወጣት የሚያስችል ተልዕኮ ለማስተባበር የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ከቀናት በፊት ከተለያዩ የአገሪቱ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

በዚህ ተልዕኮም 204 የሚሆኑትን እስራኤላውያን ከባሕር ዳር እና ከጎንደር ከመውጣታቸው በፊት በኢትዮጵያ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ እና ኢየሩሳሌም የሚገኘው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከአብዛኞቹ ዜጎቻቸው ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ ለ24 ሰዓታት ቆይተዋል።

ከዚያም በኋላ ረቡዕ ምሽት እስራኤላውያኑ ካሉባቸው ከተሞች እንዲወጡ ለማስቻል በተመቻቹላቸው የመሰባሰቢያ ቦታዎች ላይ እንዲገኙ ከተደርገ በኋላ ወደ ጎንደር እና ባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያዎች ተወስደዋል።

በአየር ማረፊያዎቹም ቀድመው በተዘጋጁ ልዩ በረራዎች አማካይነት እንዲጓጓዙ ተደርገው ወደ አዲስ አበባ ሐሙስ ዕለት የተወሰዱ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዳለው ዜጎቹ ወደ አስራኤል ለመመለስ አስኪወስኑ ድረስ በአዲስ አበባ ውስጥ ይቆያሉ።

ይህ እስራኤላውያኑን የማስወጣት ተልዕኮ በእስራኤል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ባለ የመከታተያ ክፍል (ሲችዌሽን ሩም) እገዛ የተደረገለት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ዲፕሎማቶች፣ የአይሁዳውያን ተቋም ሠራተኞች እና አማርኛ የሚችሉ የእስራኤል ሠራዊት አባላት በቡድኑ ውስጥ ተካተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በዚህ ዜጎቻቸውን በማስወጣቱ ተግባር ላይ የተሳተፉትን አመስግነው፣ “እስራኤል ዜጎቿን ባሉበት ቦታ ሁሉ ጥበቃ ታደርጋለች። ባለፉት ቀናትም ግጭት ባለበት የኢትዮጵያ አካባቢ ዜጎቻቻን ነበሩ። ከዚያ እንዲወጡ እንዲደረግ አዝዣለሁ” በማለት አገራቸው ዜጎቿን በደስታ እንደምትቀበል ገልጸዋል።

የእስራኤል ጉዳይ መሥሪያ ቤትም ከዚህ በፊት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ዜጎቹ ድጋፍ በሚፈልጉበት ጊዜ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚቻለውን አስፈላጊ ነገር ሁሉ እንደሚያደርግ አሳውቋል።

በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል ውስጥ በርካታ ቤተ እስራኤላውያን የሚገኙ ሲሆን፣ የእስራኤል መንግሥትም እነዚህን ዜጎች በተለያዩ ሁኔታዎች ወደ እስራኤል በመውሰድ በአገሩ ውስጥ ከወገኖቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ሲያደርግ ቆይቷል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ቤተ እስራኤላውያን አይሁዶች እንዳሉ ከታወቀ በኋላ ወደ እስራኤል ለመውሰድ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በዚህም የመጀመሪያዎቹ በምስጢር የተካሄዱት የሰለሞን እና የሙሴ ዘመቻዎች አማካይነት በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ለመውሰድ ችለዋል።

ከዚያም በኋላ በሕጋዊ ሂደት በርካቶች ወደ እስራኤል እየተጓዙ ሲሆን አሁንም ሌሎች በርካቶች በሂደት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።