የተመድ የባለሙያዎች ቡድን መንግሥት በአማራ ክልል የሚወስደው እርምጃ ተመጣጣኝ እንዲሆን አሳሰበ

የፎቶው ባለመብት, Eystone/EHRC
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን ዓለም አቀፍ ኮሚሽን በአማራ ክልል ከተጣለው አስቸኳይ ጊዜ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወስደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ተመጣጣኝ እንዲሆን አሳሰበ።
ኮሚሽኑ በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ በተለይ ደግሞ በአማራ ክልል እየተባባሰ ነው ያለው የፀጥታ መደፍረስ አሳስቦኛል ያለ ሲሆን፣ የመንግሥት ሕግ የማስከበር እርምጃ ተመጣጣኝ እንዲሆን ጠይቋል።
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስታውሶ፣ ከዚህ ቀደም ተፈጻሚ ሆነው በነበሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸሙ ነበር ብሏል።
በመሆኑ የባለሙያዎች ቡድኑ በሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 4 መሠረት መንግሥት ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያስፈጽም የሚወሰዱ አርምጃዎች የአስፈላጊነትን፣ የተመጣጣኝነትን እና አንድ ወገንን ለይቶ ያለማጥቃት መርሆን መከተል አለበት ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን በዚህ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ እና ግጭት አቁመው ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንዲሰሩ ጠይቋል።
ይህ የባለሙያዎች ቡድን የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በአገሪቱ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በገለልተኛነት እንዲመረምር በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ኃላፊነት እንደተሰጠው ይታወሳል።
ኮሚሽኑ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ምርመራውን አድርጎ ግኝቱን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አውጥቶ ነበር።
ሁለት ዓመት በዘለቀው ደም አፋሳሽ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ ከሕግ ውጭ የሆነ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ይፋ አድርጎ ነበር።
ኮሚሽኑ እነዚህ የተፈጸሙ ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደሆኑም ያምናል ብሎ ነበር።
ይህ የኮሚሽኑ ሪፖርት የኢትዮጵያን መንግሥት ያስቆጣ ሲሆን፣ የሪፖርቱ መውጣትን ተከትሎም የቀረበው ድምዳሜ ሙያዊ ግዴታዎችን ያላሟላ እና መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን የካደ ነው በሚል የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞውን ገልጾ ነበር።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት የጦርነቱን ማብቃት ተከትሎ የባለሙያዎቹ ቡድን አስፈላጊነት ማብቃት አለበት በማለት በተደጋጋሚ መጠየቁ ተዘግቧል።
ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን ከተቋቋመ በኋላ የሥራ ጊዜው በአንድ ዓመት ተራዝሞ እስከ ሚቀጥለው ዓመት ታኅሥሣ 2016 ድረስ በሥራ እንዲቆይ ተወስኗል።












