የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፡ በአዲሱ የውድድር ዘመን ማን ዋንጫ ያነሳል? የትኞቹ ቡድኖችስ ይወርዳሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፊል ማክናልቲ ባለፈው ዓመት የውድድር ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት ግምቱን ሲያስቀምጥ ማንቸስተር ሲቲ ዋንጫ ይወስዳል፣ አርሰናል አምስተኛ፣ ዩናይትድ ደግሞ ስድስተኛ ይወጣል ብሎ ነበር።
ማን ይወርዳል ተብሎ ተጠይቆ ኖቲንግሃም፣ ፉልሃም እና ቦርንመዝ የሚል ግምት ነበር ያስቀመጠው።
ፊል፤ ማንቸስተር ሲቲ ዋንጫ ያነሳል ከሚለው ግምቱ ውጪ ብዙም አልተሳካለትም። ነገር ግን በዚህ ያልተሳነፈው የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ፊል አዲሱን የውድድር ዘመን በአዲስ ግምት ጀምሮታል።
“እርግጥ ነው ባለፈው ዓመት ሲቲ ዋንጫ ይበላል ብዬ ገምቻለሁ” የሚለው ፊል ይህን ማንም ሊገምተው እንደሚችል ያምናል።
ወደ ዘንድሮው ግምት ስናመራ ፊል አሁንም ዋንጫው ከማንቸስተር ሲቲ እጅ የሚወጣ አይደለም ባይ ነው።
ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቅቃል የሚለው ደግሞ ሊቨርፑልን ነው፣ ሦስተኛ አርሰናል፣ አራተኛ ማንቸስተር ዩናይት፣ ከዚያ ቀጥሎ አስተን ቪላ እና ቼልሲ በቅደም ተከተል አስቀምጧል።
ዎልቭስ፣ ሼፊልድ ዩናይትድ እና ሉተን ታውን ደግሞ ወደ ታችኛው ሊግ ወራጆች ናቸው የሚል ግምት አለው።
ማንቸስተር ሲቲ
የፔፕ ጉዋርዲዮላ ማንቸስተር ሲቲ በሰባት ዓመት ስድስት ዋንጫ ሊበላ እየተሰናዳ ይመስላል ባይ ነው ፊል።
ሦስት ጊዜ በተከታታይ ዋንጫ በማንሳት የጎረቤታቸው ማንቸስተር ዩናይትድ ክብረ-ወሰንን የተጋሩት ሲቲዎች አራተኛውን ክብር ከመጨመር ወደኋላ የሚሉ አይደሉም።
የመሐል ሜዳ ሞተሩ ኢካይ ጉንዶጋን እና ሪያድ ማህሬዝን የሸጡት ሲቲዎች፣ ክሮኤሽያዎቹ ማቴዎ ኮቫቺች እና ጃስኮ ግቫርዲዮልን አስፈርመዋል።
አስፈሪው አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ እና ድንቁ አማካይ ኬቪን ዴ ብሩይነ አሁንም ለሲቲ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ እሙን ነው።
ሊቨርፑል
ቀያዮቹ ባለፈው የውድድር ዘመን አምስተኛ ደረጃ ይዘው ነው ያጠናቀቁት። ይህ ማለት በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አይሳተፉም ማለት ነው።
ባለፈው ዓመት የኤፍ ኤ ዋንጫ እና ካራባዎ ዋንጫን በልተው በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ዝቅተኛ ውጤት ያመጡት የየርገን ክሎፕ ልጆች ዘንድሮ ተነቃቅተው ሊመጡ ይችላሉ።
አምበሉ ጆርዳን ሄንደርሰን እና ብራዚላዊው አማካይ ፋቢንሆ ወደ ሳዑዲ ፕሮ ሊግ አቅንተዋል። ቢሆንም ሊቨርፑል ማክ አሊስተር እና ዶሚኒክ ስዞቦስዝላይን አስፈርሟል።
ፊል እንደሚለው ሊቨፑርል በሚመጣው የውድድር ዘመን በሞሐመድ ሳላህ፣ ኮዲ ጋክፖ እና ሉዊስ ዲያዝ ታግዘው ውጤታማ ጊዜ ያሳልፋሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርሰናል
እርግጥ ነው አርሰናል ባለፈው ዓመት እጅግ ድንቅ ነበረ። ግና ምን ያደርጋል ባለቀ ሰዓት ዋንጫውን አሳልፈው ለማንቸስተር ሲቲ ሰጡ።
የማይክል አርቴታ ልጆች ሜዳ ላይ ማራኪ ጨዋታ ያሳያሉ። በክረምቱ የዝውውር መስኮትም ጥሩ አቋም ያላቸው ተጫዋቾች አስፈርመዋል።
ዴክለን ራይስን 105 ሚሊዮን ፓውንድ በሚያወጣ ዋጋ፤ ካይ ሃቨርትዝን ደግሞ በ65 ሚሊዮን ፓውንድ አምጥተዋል። አልፎም ጁሪዬን ቲምበርን ከአያክስ አስፈርመው ቡድናቸውን አጠናክረዋል።
ከ2016/17 የውድድር ዘመን በኋላ ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ወድድር የተመለሱት አርሰናሎች በቡካዮ ሳካ እና ማርቲን ኦዴጋርድ ታግዘው መልካም ውጤት እንደሚያሳዩ ፊል ያምናል።
ማንቸስተር ዩናይትድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው የውድድር ዘመን ሦስተኛ የወጡት ማንቸስተር ዩናይትዶች በኤሪክ ቴን ሃግ ታግዘው ለሁለተኛ ጊዜ መልሶ ጥገና ማድረግ ጀምረዋል።
ዩናይትድ በቴን ሃግ ዘመን የካራባዎ ዋንጫ በመብላት ከ2017 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫን ወደ ቁም ሳጥናቸው አምጥተዋል።
ከዚህም አልፎ ለኤፍ ኤ ዋንጫ ፍፃሜ መብቃት የቻሉት ቀያዮቹ ሰይጣኖች ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድርም ተመልሰዋል።
ዴቪድ ዴ ሂያ በአንድሬ ኦናና ተለውጧል። ኦናና ለኤሪክ ቴን ሃግ አጨዋወት የሚመጥን በረኛ ነው። አያክስ እያሉ አንድ ላይ ሠርተዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ፤ ሜሰን ማውንትን ከቼልሲ እንዲሁም ራስመር ሆይለንድን ከጣሊያኑ አታላንታ አስፈርሟል።
ፊል እንደሚለው ዩናይትድ የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ ባያነሳም መሻሻሉን ግን ይቀጥልበታል።
የፊል ማክነልቲ ጠቅላላ ግምት
- ዋንጫ - ማንቸስተር ሲቲ
- ሁለተኛ - ሊቨርፑል
- ሦስተኛ - አርሰናል
- አራተኛ - ማንቸስተር ዩናይትድ
- አምስተኛ - አስተን ቪላ
- ስድስተኛ - ቼልሲ
- ወራጆች - ዎልቭስ፣ ሼፊልድ ዩናይትድ፣ ሉቶን ታውን












