ሳሙዔል ኤቶ ተገቢ ያልሆነ ተግባር ፈጽሟል በሚል በካፍ ምርመራ ተከፈተበት

ሳሙዔል ኤቶ

የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል የሆነው ካፍ ካሜሩናዊው ሳሙዔል ኤቶ አላግባብ ተግባር ፈጽሟል ሲል ምርመራ ከፈተበት።

የካሜሩን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆነው ኤቶ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ 2021 ነው የተሾመው።

የቀድሞው የባርሴሎና እና የኢንተር ሚላን አጥቂ የአገሩን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያስተዳድርበት መንገድ ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ ምርምራ ተከፍቶበታል።

ባለፈው ወር የተወሰኑ የካሜሩን ክለቦች የ42 ዓመቱ ኤቶ ሥልጣን እንዲለቅ ጠይቀው የአገሪቱ ስፖርት ሚኒስትር ጣልቃ እንዲገቡ ተማፅነዋል።

ክለቦቹ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ፊፋ ፕሬዝዳንት የሆኑት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም ጣልቃ እንዲገቡ ጥያቄ አቅርበዋል።

ቢቢሲ፤ ፌካፉት በመባል የሚታወቀው የካሜሩን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

ካፍ ባወጣው መግለጫ “ከበርካታ የካሜሩን እግር ኳስ አካላት የጽሑፍ ማሳሰቢያ ደርሶኛል” ብሎ “በካፍ ሕግ መሠረት እኚህን ጥያቄዎች ማስተናገድ እንደሚጀምር” ገልጧል።

መግለጫው አክሎ የቀረቡት ቅሬታዎች “ክብደት ያላቸው” ቢሆኑም “ኤቶ ምርምራ ተደርጎበት ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ ንፁህ ሰው ነው” ብሏል።

ሳሙኤል ኤቶ በተጫዋች ዘመኑ ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል።

በአውሮፓ ትላልቅ ክለቦች የተጫወተው ሳሙዔል ኤቶ አራት ጊዜ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል።

ሦስት ጊዜ ደግሞ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ማንሳት ችሏል።

ለማይበገሩት አናብስት 115 ጊዜ የተሰለፈው ኤቶ ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አንስቷል።

ኤቶ ኳታር ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጨ ወቅት አንድ ግለሰብ መትቷል ተብሎ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር አይዘነጋም።